የክለቦች የውድድር ዘመን ቅድመ ዳሰሳ | ኢትዮጵያ ቡና

ኢትዮጵያ ቡና ራሱን በአዲስ መልክ አደራጅቶ ለሊጉ ፍልሚያ ያዘጋጀበትን መንገድ በቀጣዩ ፅሁፋችን ተመልክተነዋል።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከጀመረ አንስቶ በተሳታፊነት ከቆዩ ሁለት ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ኢትዮጵያ ቡና 25ኛ የውድድር ዓመቱን ለመጀመር ዝግጅቱን አጠናቋል። አንድ ጊዜ ቻምፒዮን መሆን የቻሉት ቡናዎች ያለፈው ዓመት ጉዟቸው እንዳሰቡት ስኬታማ አልነበረም። የመጀመሪያ ድሉን ለማሳካት አምስት ሳምንታት የፈጀበት ኢትዮጵያ ቡና ራሱን በደረጃ ሰንጠረዡ የመጨረሻው ክፍል ለማግኘት ተገዶ የነበረ ቢሆንም አራት ተከታታይ ድሎች በማስመዝገብ እና ቀስ በቀስ ነጥቦችን በመሰብሰብ ወደ ላይ ከፍ ማለት ችሏል። በዚህ ሂደት ውድድሩን እስከ ሦስተኛ ደረጃ ይዞ የመጨረስ ዕድሉ እንዳለው ምልክት የሰጠባቸው የጨዋታ ቀናት ታይተዋል። ነገር ግን በየመሀሉ በሚያሳየው የውጤት መዋዠቅ ቀጥሎ እንደመጀመሪያው ሁሉ በመጨረሻም ከአምስት ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ ድል ማድረጉን ተከትሎ በ42 ነጥቦች 6ኛ ደረጃ ላይ እንዲጨርስ ሆኗል።

ይህን ውጤት ክለቡ ፈፅሞ ለመቀበል የማይፈልገው መሆኑ መታየት የጀመረው ውድድሩ ተጠናቆ ቀናቶች ካለፉ በኋላ ነበር። በዚህም ከ2011 መጨረሻ ጀምሮ በአሰልጣኝነት የቆዩት አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ የጨረሱበት ደረጃ ከክለቡ ጋር ከነበራቸው ስምምነት ጋር ባለመጣጣሙ የአንድ ዓመት ውል እየቀራቸው እንዲለያዩ ተወስኗል። ‘ቀጣዩ የቡናማዎቹ አለቃ ማን ይሆናል ?’ የሚለው ጉዳይ ሲያነጋግር ከቆየ በኋላ ክለቡ ሐምሌ አጋማሽ አሰልጣኝ ተመስገን ዳናን መሾሙን ይፋ አድርጓል። በመቀጠል ደግሞ በረዳት አሰልጣኝነት አሰልጣኝ ዮሴፍ ተስፋዬ እና ነፃነት ክብሬ ሲሾሙ የቀድሞው የቡድኑ ታሪካዊ ተጫዋች ታፈሰ ተስፋዬ በምክትል ቡድን መሪነት ቦታ ተሰይሟል።
በኢትዮጵያ ቡና የጀመረው ለውጥ ስር ነቀል መሆኑ የታወቀው ግን ከአሰልጣኝ ለውጡ በኋላ ከቡድኑ ቁልፍ ተጫዋቾች ጋር መለያየት ሲጀምር ነበር። በጥቅሉ ብንመለከተው እንኳን አምና ከአንድ ሺህ ደቂቃዎች በላይ ሜዳ ላይ ከቆዩ የቡድኑ 15 ተጫዋቾች ውስጥ ወደ ደቡብ አፍሪካ ያቀናው አቡበከር ናስርን ጨምሮ አስሩ ተጫዋቾች በዘንድሮው ስብስብ ውስጥ አይገኙም። ይህንን ተከትሎ በጊዜ ወደ ገበያ የወጣው ኢትዮጵያ ቡና ምንአልባትም በታሪኩ ከፍተኛውን ዝውውር የፈፀመበትን ክረምት አሳልፏል። በዚህም ዘጠኝ ነባር ተጫዋቾችን ይዞ ሲቀጥል ቀሪ ስብስቡን በ13 አዲስ ቅጥሮች እና አምስት ታዳጊዎች አተሰይሟል።

በዋናነት አቡበከር ናስርን ካጣ በኋላ ሁነኛ ግብ አስቆጣሪ ያልነበረው ኢትዮጵያ ቡና በሊጉ ጥሩ አቅም እንዳላቸው ያሳዩት መስፍን ታፈሰ ፣ ብሩክ በየነ ፣ ጫላ ተሺታ እና መሐመድኑር ናስርን በእጁ አስገብቷል። በተጨማሪ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ጥሩ ተስፋ ያሳዩት በክልሎች ሻምፒዮና በሻኪሶ ከተማ ደምቆ የታየው አንተነህ ተፈራ እና ወጣቱ ከድር ዓሊ የፊት መስመሩን ይበልጥ ያጠናክራሉ ተብሎ ይጠበቃል። አማካይ ክፍል ላይም ያለፉት ሁለት ዓመታት በተደጋጋሚ ቀዳሚ ምርጫ ከነበሩ ተጫዋቾች ውስጥ አማኑኤል ዮሐንስ እና ሮቤል ተክለሚካኤልን ያስቀሩት ቡናዎች አብዱልሀፊስ ቶፊቅ ፣ አብዱልከሪም ወርቁ እና ሔኖክ ድልቢን አምጥተዋል። ከግለሰባዊ ስህተቶች መነሻነት ግቦች ሲቆጠሩበት ይታይ የነበረው ቡና በዘንድሮው ስብስቡ በመሀል ተከላካይነት ወልደአማኑኤል ጌቱ ፣ ራምኬል ጀምስ እና ጋናዊው ኩዋኩ ዱሀን ሲያካትት ኃይለሚካኤል አደፍርስ እና ዘነበ ከድር ደግሞ አዲሶቹ የቡድኑ የመስመር ተከላካዮች ሆነዋል።

በእርግጥም የዘንድሮው የኢትዮጵያ ቡና ስብስብ ባለፉት ዓመታት ከነበሩት የተሻለ ጥራት እንዳገኘ መናገር ይቻላል። ክለቡ በግብ ጠባቂ ቦታ ላይ አንድ ተጫዋች ለማስፈረም ከሀገር ውጪ እያማተረ መሆኑ ከሰሞኑ የተሰማ ሲሆን ተሳክቶለት ጥሩ የግብ ዘብ ካስፈረመ ደግሞ ለአሰልጣኝ ተመስገን ዳና በየመጫወቻ ቦታው ላይ ጥሩ ጥሩ አማራጮች የሚፈጠሩ ይሆናል። አሰልጣኙም ክለባቸው የፈፀማቸው ዝውውሮች ታቅደው የተደረጉ ስለመሆናቸው እና ከግምት ስለገቡ ነገሮች ሲያስረዱ “መጀመሪያም ዝውውሩ ታስቦበት የተደረገ ነው፡፡ አንደኛ የኢትዮጵያ ቡናን የጨዋታ ባህል ማስቀጠል የሚችል ተሰጥዖ ያላቸው ልጆችን ማሰብ ነው፡፡ ከዛ ውጪ በተቻለ መጠን በዕድሜ ወጣቶች እንዲሆኑ ነው የፈለግነው ፤ ለረጅም ጊዜ ክለቡን በወጥነት ማገልገል እንዲችሉ ዕድሜያቸው ጥሩ የሆኑ ልጆችን መሰብሰብ ነው። ሁለተኛው እና ሦስተኛው ዲሲፕሊን ነው ! በተለይ የኋላ ታሪካቸው ተጫዋቾቹ ከችሎታ እና ከአቅማቸው ባሻገር የዲሲፕሊን ታሪካቸው ምንድነው የሚለውን አጥንተንበት ነው ያመጣነው፡፡ ስለዚህ በአብዛኛው የዝውውር ግምገማችን ስኬታማ እንደነበር ነው የሚያሳየው። ምክንያቱም መጀመሪያ በጥናት የተደረገ ስለሆነ ነው።” ይላሉ። ከፈራሚዎቹ መካከል የተወሰኑት ከአሰልጣኙ ጋር በዕድሜ ዕርከን ቡድኖች አብረው የሰሩ መሆናቸውን ስናስብ ደግሞ ከብቃት ባለፈ በዲስፕሊን ዙሪያ ያላቸውን ሁኔታ ለመገምገም እንዳገዛቸው መናገር ይቻላል።

ይህን መሳይ ከነበረው የክለቡ ምልመላ እና የአዲሱ ቡድን ግንባታ በኋላ ኢትዮጵያ ቡና ዝግጅቱን ለአንድ ወር ከአራት ቀናት ያህል በሀዋሳ ከተማ ሲያደርግ ቆይቷል። በዚህ ጊዜ ውስጥ በቀን ሁለት ጊዜ በሚሰራባቸው ጊዜያት ጠዋት በአካል ብቃቱ ላይ ከሰዓት ደግሞ ቡድኑ ሊጫወት የፈለገውን ሀሳብ ተጫዋቾች ሊረዱ የሚችሉበት ሥልጠና ላይ ትኩረቱን አድርጓል። በተለይ ከዚህ ቀደም ቡድኑ ይታማበት የነበረውን የአካል ብቃት ችግር ከመቅረፍ አኳያ በሀገረ እንግሊዝ በእግርኳስ ትምህርት እና ሥልጠና የቆየው አሰልጣኝ ሚካኤል ኃይሉ ጋር መስራት መቻላቸው ጠቃሚ እንደነበር አሰልጣኝ ተመስገን ይናገራሉ። “እጅግ በጣም ትልቅ ጠቀሜታ ነበረው፡፡ ምክንያቱም በአብዛኛው የፊትነስ ሥራዎችን እርሱ ነው የሸፈናቸው። ሥራዎቹ ውጤታማ መሆናቸውን ልጆቹ ላይ ባየነው እንቅስቃሴ መረዳት ችለናል፡፡ ከዛ ውጪ ልጆቹ ከሥራ ውጪ የነበራቸው የመስራት ፍላጎት እንደ አንድ ማሳያ ልትወስደው ትችላለህ። ስለዚህ በአጠቃላይ የሚኪ መኖር እጅግ በጣም አስፈላጊ ነበር ፤ በተለይ የአካል ብቃት ስራው ላይ፡፡”

ቡና ሀዋሳ ላይ ቆይታ ባደረገበት ወቅት ከሀዋሳ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ የማድረግ ዕድሉ የነበረው ቢሆንም በሊጉ የመጀመሪያ ሳምንታት ከእነዚህ ቡድኖች ጋር የሚገናኝ በመሆኑ አለመጫወቱን መርጧል። “ከተመረጡ ወጣቶች ጋር በተለይ የከፍተኛ ሊግ ፣ ብሔራዊ ሊግ እንዲሁም የፕሪምየር ሊግ ተስፋ ካላቸው ልጆች ጋር ተመርጠው ከእነርሱ ጋር አንድ ሁለት ጨዋታዎችን አድርገናል ፤ ከሻሸመኔ ምርጥ ጋር ሌላም ጨዋታ አድርገናል፡ስለዚህ በእነዛ ጨዋታዎች ላይ ያየነው ነገር ጥሩ ነው፡፡” የሚሉት አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ሦስተኛ ደረጃ ይዘው በጨረሱበት የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫው ውድድር ላይ ተጨማሪ አራት ጨዋታዎችን አድርገዋል። እነዚህ ጨዋታዎች በተለይ በዋና ቡድኑ ውስጥ መካተት ያለባቸው ወጣት ተጫዋቾችን ከመለየት አንፃርም ጥሩ አስተዋፅኦ አድርጎላቸዋል።

በእግርኳስ ጥሩ ብቃት ላይ የሚገኙ ተጫዋቾችን መያዝ ለውጤታማነት ቁልፍ ቢሆንም ብቻውን ግን አስተማማኝ አይሆንም። ተጫዋቾቹ በነበሩባቸው ቡድኖች ውስጥ ካሳዩት አቋም አንፃር የኢትዮጵያ ቡና አሁን ያለው ስብስብ ጥንካሬ ባያጠራጥርም የውህደት ደረጃው በዛው ልክ መሆን እንዳለበት መናገር ይቻላል። በሌላ በኩል ላለፉት ዓመታት አብሮ የቆየውን ቡድን ካስተዋልን ደግሞ ለረጅም ጊዜ መቆየት በራሱ ለተፈላጊው ውጤት የሚያበቃ ውህደት ላይ ላያደርስ እንደሚችል ምስክር ነው። አሰልጣኝ ተመስገንም የተጫዋቾቹ ደረጃ በቶሎ ለማዋሀድ እንደሚረዳቸው በፅኑ ያምናሉ። “እንግዲህ እኛ እንደ ነብይ ሳይሆን እንደ ባለሙያ ነው የምናወራው። ልጆቹ ቴክኒካሊ በጣም የተሰጡ ናቸው ፤ ወጣቶች ናቸው ፣ ፍላጎት አላቸው። በየሥራዎቹ የምናይላቸው ለዚህ ምስክር ነው ስለዚህ ቶሎ ይግባባሉ የሚል ዕምነት አለን፡፡ ከተግባቡ ደግሞ ውጤታማ መሆን የማንችልበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ምናልባት በእግር ኳስ ሊፈጠር የሚችለው ነገር አይታወቅም። እኛ ግን ውጤታማ እንሆናለን ብለን እናስባለን፡፡”

ከሜዳ ላይ ታክቲካዊ ውህደት ባለፈ በሥነልቦናው በኩልም ያሁኑ ስብስብ እጅግ ጠንካራ መሆን ይጠበቅበታል። ምክንያቱ ደግሞ ዘንድሮ ጥሩ ስብስብ ከመያዙ አንፃር ብቻ ሳይሆን ለተከታታይ ዓመታት ውጤታማ እንዲሆን እና ሁለተኛውን ዋንጫ እንዲያናሳ ይጠበቅ የነበረ ከመሆኑ አንፃር ዘንድሮ ቡድኑ ቢያንስ በቶሎ ጥሩ ምልክቶችን የመስጠት ጫና ሊኖርበት እንደሚችል ይጠበቃል። ከዚህ አንፃር አዲሶቹ የቡና ተጫዋቾች ጠንካራ የሥነ ልቦና መሰረት ላይ መቀመጥ እንዳለባቸው ይታሰባል። አሰልጣኝ ተመስገን ግን ጫና ይኖራል በሚለው ሀሳብ አይስማሙም። ምክንያታቸውን ሲያስረዱም “ምንም የሚፈጥርብን ጫና የለም ምክንያቱም ቡድኑ ከአስራ ምናምን በላይ ተጫዋቾች አሰናብቷል፡፡ የግድ እነዛን የሚተኩ ተጫዋቾች ይመጣሉ። እነዚህ ተጫዋቾች ሲመጡ በኳሊቲም በዲሲፕሊንም በትክክል ለቡድኑ የሚመጥን መሆን አለባቸው የሚል ነገር ስለነበር መጥተዋል። ይሄ ተፈጥሯዊ ነገር ነው። ስለዚህ ምንም ያን ያህል ጫና አይኖረውም፡፡ ከእዛ ውጪ በሙከራም ያገኘናቸው ልጆች ሲቲ ካፑ ላይ ባሳዩት ነገር ተቀባይነት አግኝተው ለቡድኑ ፈርመዋል፡፡ እንደ አጠቃላይ የመጡት ልጆች ኢትዮጵያ ቡናን ለማገልገል የመጡ ናቸው የሚል አስተሳሰብ ብቻ ነው ያለን። ከእዛ የዘለለ ነገር የለንም ስለዚህ ጫናው አይኖርም፡፡” ይላሉ።

በአሰልጣኝ ተመስገን ዳና ስር ኢትዮጵያ ቡና በኳስ ቁጥጥር ላይ የተመሰረተ አቀራረቡን እንደሚቀጥል ይጠበቃል። አሰልጣኙ በወልቂጤ በነበራቸው ቡድን ከሰጡት ምልክት አንፃር ደግሞ ከኳስ ውጪ ከዚህ ቀደሙ በተሻለ ትጋት መልሶ ኳስ ለመንጠቅ የመሞከር ባህሪን በዘንድሮው ኢትዮጵያ ቡና ላይ ልንመለከት እንችላለን። በዝግጅት ወቅት በአካል ብቃት እና በሥነምግባር ላይ ትኩሩት መስጠታቸውን ስንመለከትም ቡድኑ በየጨዋታው በተሻለ ጉልበት ሽግግሮችን መሸፈን የሚችል አቅም ይዞ እንዲቀጥል ሊኖራቸው ከሚችለው ፍላጎት ጋር አብሮ የሚሄድ ነጥብ ነው።

ከኳስ ቁጥጥር ጋር በተያያዘ አዲሶቹ ስምንት ቁጥሮች አብዱልከሪም ወርቁ እና አብድልሀፊስ ቶፊቅ የጨዋታ ፍሰትን ከመምራት ጋር በተያያዘ ያላቸው ብቃት ቡድኑ የማጥቃት ደመነፍስ ያላቸው የመስመር ተከላካዮችን የያዘ በመሆኑ ከፍ ባለ ቁጥር የተጋጣሚ ሜዳ ላይ ልዩኑት ፈጣሪ ቅብብሎችን በማድረጉ ተሻሽሎ እንደሚቀርብ ይጠበቃል። ዘንድሮም እንደአምናው ተጋጣሚዎች ኳስ ከኋላ እንዳይጀምር የማድረግ ፈተናን ይዘው መምጣታቸው የማይቀር በመሆኑ ኳስ እነዚህ አማካዮች ጋር ከመድረሱ በፊት ከግብ ጠባቂ ጀምሮ በተከላካዮች የሚሰራጭበት አኳኋን ላይ ተገማችነቱን መቀነስ ከዋነኞቹ አንዱ የአሰልጣኝ ቡድን አባላቱ የቤት ሥራ ይመስላል። ፊት መስመር ላይ ያለው የቡድኑ አማራጭ በአቡበከር ናስር ላይ ጥገኛ የነበረውን ኢትዮጵያ ቡና ዘንድሮ በርካታ አማራጮችን ይሰጠዋል። በዕድሜ ወጣት ቢሆኑም በሊጉ የማይናቅ ልምድ ያላቸው አዲሶቹ አጥቂዎች ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ ለመግባት ብርቱ ፉክክር ማድረግ የሚጠበቅባቸው ሲሆን ከላይ ያነሳነው ጫና የመቋቋም አቅማቸውም በአዲሱ ክለባቸው በሚኖራቸው ቆይታ ይፈተናል።

ከፈተና አንፃር አሰልጣኝ ተመስገን ዳናም በመጀመሪያ ዓመታቸው ቢያንስ ጠንካራ ተፎካካሪ ቡድን ሰርቶ የማሳየት ኃላፊነት ያለባቸው በመሆኑ የአሰልጣኝነት ህይወታቸው ቀጣዩን ደረጃ የሚያሳዩቡት ሹመት ነው ማለት ይቻላል። ከዚህ ጋር በተያያዘ “በተፈጥሮ ፈተናዎችን የመጋፈጥ ፍላጎቱም ድፍረቱም አለኝ። በዚህ በኩል ምንም ችግር ይገጥመኛል የሚል ዕምነት የለኝም። ምክንያቱን ጫናዎች ጥሩ ያደርጉሀል እንጂ አይጎዱህም። ስለዚህ ጫና በእግርኳስ ተፈጥሯዊ ነው። የትኛውንም ቡድን ብትይዝ ጫና አለው የጫናው ዓይነት ይለያያል እንጂ በየቡድኖች ውስጥ ጫናን ታስተናግዳለህ፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ቡና ውስጥ ያለው ጫና የሚጠበቅ ነው ስራህን ሰርተህ ለማሳመን መሞከር ነው፡፡” የሚሉት አሰልጣኙ በሀዋሳ ከተማ እና በብሔራዊ ቡድን በዕድሜ እርከን ቡድኖች ያሳዩትን ብቃት በዋና አሰልጣኝነት የቅድመ ውድድር ዝግጅት አድርገው በራሳቸው መንገድ የሚሰሩትን ቡድን የሚያሳዩበት ዓመት ከፊታቸው ይጠብቃቸዋል።

ኢትዮጵያ ቡና የዘንድሮው የሊግ ውድድሩን በመጪው እሁድ ከወላይታ ድቻ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ይጀምራል።

የኢትዮጵያ ቡና የ2015 ሙሉ የቡድን ዝርዝር

ግብ ጠባቂዎች

1 በረከት አማረ
22 እስራኤል መስፍን

ተከላካዮች

2 አበበ ጥላሁን
3 ራምኬል ጀምስ
23 ገዛሀኝ ደሳለኝ
11 አስራት ቱንጆ
20 ኩዋኩ ዱሀ
29 ኃይለሚካኤል አደፍርስ
21 ወልደአማኑኤል ጌቱ
24. ዘነበ ከድር
28 ቃለአብ ፍቅሩ

አማካዮች

8 አማኑኤል ዮሐንስ
6 ሮቤል ተክለሚካኤል
5 አብዱልሀፊስ ቶፊቅ
14 አብዱልከሪም ወርቁ
27 ሔኖክ ድልቢ
26 ሱራፌል ሰይፈ
16 ኤርሚያስ ሹምበዛ
18 መላኩ አይሌው

አጥቂዎች

17 መስፍን ታፈሰ
19 አንተነህ ተፈራ
10 ብሩክ በየነ
7 ጫላ ተሺታ
9 መሐመድኑር ናስር
30 ከድር ዓሊ
13 አማኑኤል አድማሱ

የአሰልጣኝ ቡድን አባላት

ዋና አሰልጣኝ – ተመስገን ዳና
ምክትል አሰልጣኝ – ዮሴፍ ተስፋዬ
ምክትል አሰልጣኝ – ነፃነት ክብሬ
የቡድን መሪ – ሙሉጌታ አስፋው
ምክትል ቡድን መሪ – ታፈሰ ተስፋዬ
የቡድኑ ሀኪም – ይስሀቅ ሽፈራው
ፌዚዮቴራፒስት – ሠለሞን ኃይለማሪያም