ዛሬ የተጀመረው የዘንድሮው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ነገ በሁለት ጨዋታዎች ሲቀጥል የተጋጣሚ ቡድኖችን የተመለከቱ መረጃዎችን እንደሚከተለው አሰናድተናል።
ኢትዮጵያ መድን ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ
ኢትዮጵያ መድን ከከፍተኛ ሊግ ማደጉን ተከትሎ በፕሪምየር ሊጉ ከስምንት ዓመታት በኋላ በሚያደርገው የመጀመሪያ ጨዋታ ከቻምፒዮኖቹ ጋር ይገናኛል። አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌን በመቅጠር ከነባር ስብስቡ ብዙሀኑን አስቀርቶና ተጨማሪ ዝውውሮችን ፈፅሞ አዳማ ላይ ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል። በአንፃሩ የ2014 ቻምፒዮኖቹ ቅዱስ ጊዮርጊሶች አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታን በዋና አሰልጣኝነት በመሾም በክረምቱ በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ካደረጉት ተሳትፎ መልስ ቢሾፍቱ ላይ በክቡር ይድነቃቸው ተሰማ አካዳሚ ከትመው ሲዘጋጁ ሰንብተዋል።
በነገው ጨዋታ ኢትዮጵያ መድን የኋላ መስመሩ ላይ ሊያገኘው የሚችለው የመሀል ተከላካይ ተመስገን ተስፋዬን ብቻ ሲሆን ቀሪዎቹ ተጫዋቾቹ ባለማገገማቸው ክፍተቱን በማሸጋሸግ ለመድፈን እንደሚሞክር ይጠበቃል። በሌላ ዜና ክለቡ ሦስት የውጪ ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾችን ያስፈረመ ቢሆንም ከሥራ እና ከመኖሪያ ፍቃድ ጋር በተገናኘ ለነገው ጨዋታ እንደማይደርሱ ተሰምቷል። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል አቤል ያለው ጉዳት ላይ የሚገኝ ሊሆን ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ ከብሔራዊ ቡድን ግልጋሎት መልስ ከቡድኑ ጋር ባህር ዳር ደርሷል። ከዚህ ውጪ ዛሬ ቡድኑን የተቀላቀለው አማኑኤል ገብረሚካኤል የነገው ጨዋታ ስብስብ ውስጥ እንደሚካተት ይገመታል።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 23 ጊዜ የመገናኘት ታሪክ ሲኖራቸው 16 ጊዜ ያሸነፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ 38 ጎሎች ፣ 2 ጊዜ ያሸነፈው መድን ደግሞ 12 ግቦችን አስቆጥረው አምስት ጊዜ ነጥብ ተጋርተዋል። ኢትዮጵያ መድን በዚህ ግንኙነት የመጨረሻውን ድል 1996 ላይ ሲያስመዘግብ የመጨረሻው የ2006 ጨዋታቸው ደግሞ በቅዱስ ጊዮርጊስ 2-1 አሸናፊነት የተጠናቀቀ ነበር።
የነገውን የመድን እና የጊዮርጊስ ጨዋታው በዋና ዳኝነት የሚመሩት ማኑሄ ወልደፃዲቅ ሲሆኑ ረዳቶች አበራ አብርደው እና ሲራጅ ኑርበገን ፣ አራተኛ ዳኛ ደግሞ ኢያሱ ፈንቴ በመሆን ተመድበዋል።
ኢትዮጵያ መድንን በተመለከተ ያዘጋጀነውን የውድድር ዘመን ዳሰሳ ለማንበብ ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ :
ቅዱስ ጊዮርጊስን የተመለከተ በዘጋጀነውን የውድድር ዘመን ዳሰሳ ለማንበብ ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ :
ድሬዳዋ ከተማ ከ ሲዳማ ቡና
ነገ 12:00 ላይ የሚደረገው ሁለተኛ ጨዋታ ድሬዳዋ እና ሲዳማን ያገናኛል። እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ ዓምናም ላለመውረድ በነበረው ትግል ውስጥ ተሳታፊ የነበሩት ድሬዳዋ ከተማዎች ኃላፊነቱን ለአሰልጣኝ ዮርዳኖስ አባይ በመስጠት አስር ተጫዋቾችን አስፈርመው ለአዲሱ የውድድር ዓመት ቀርበዋል። ከአሰልጣኝ ወንድምአገኝ ጋር ለመቀጠል የወሰኑት ሲዳማ ቡናዎችም ከአምናው በተሻለ ለመፎካከር ይረዱናል ያሏቸውን 11 ዝውውሮች ፈፅመው ሀዋሳ ላይ ሲያደርጉት ከነበረው ውድድር መልስ ለውድድሩ ጅማሮ ደርሰዋል።
የድሬዳዋ ከተማዎቹ ዳንኤል ተሾመ እና አቤል ከበደ በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታው ውጪ ሲሆኑ መጠነኛ ጉዳት ያለበት አቤል አሰበም የመሰለፉ ነገር እርግጥ አልሆነም። በሲዳማ በኩል ግን የተሰማ የጉዳት ዜና የለም።
ድሬዳዋ ከተማ እና ሲዳማ ቡና እስካሁን በሊጉ 18 ጊዜ ተገናኝተዋል። ከእነዚህ ግንኙነቶች ሲዳማ ቡና ዘጠኙን በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን ሁለት ጊዜ ደግሞ ድሬዳዋ ከተማ ረቷል ፤ ቀሪዎቹ ሰባት የእርስ በርስ ግንኙነቶች በአቻ ውጤት የተፈፀሙ ነበሩ። በጨዋታዎቹ ሲዳማ ቡና 20 ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ 8 ግቦችን አስቆጥረዋል።
ለዚህ ጨዋታ ኤፍሬም ደበሌ በመሀል ዳኝነት ሲመደቡ
ሰለሞን ተስፋዬ እና ለዓለም ዋሲሁን ረዳቶች እንዲሁም ባህሩ ተካ አራተኛ ዳኛ ሆነዋል።
ድሬዳዋ ከተማን በተመለከተ ያዘጋጀነውን የውድድር ዘመን ዳሰሳ ለማንበብ ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ :
ሲዳማ ቡናን በተመለከተ ያዘጋጀነውን የውድድር ዘመን ዳሰሳ ለማንበብ ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ :