ሦስት የውጪ ዜጋ ተጫዋቾች ኢትዮጵያ መድንን ተቀላቅለዋል

አዲስ አዳጊው ክለብ ኢትዮጵያ መድን የሦስት የውጪ ዜጋ ተጫዋቾችን ዝውውር ፈፅሟል፡፡

በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከስምንት ዓመታት በኋላ ብቅ ብሎ በዛሬው ዕለት ቅዱስ ጊዮርጊስ በመግጠም የውድድር ዘመኑን የሚጀመረው የአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌው ኢትዮጵያ መድን በርካታ የሀገር ውስጥ አዳዲስ ተጫዋቾችን ካስፈረመ በኋላ ፊቱን ወደ ውጪ ሀገር በማዞር ዝውውሩ ከመጠናቀቁ በፊት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን አስመዝግቧቸው የነበራቸውን ሦስት የውጪ ሀገር ተጫዋቾች ዝውውር አገባዷል፡፡

ጋናዊው የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቹ ሀቢብ መሀመድ የክለቡ አዲሱ ፈራሚ ተጫዋች ሆኗል፡፡ እግር ኳስን በሀገሩ ክለቦች አሻንቲ ጎልድ ፣ አሻንቲ ኮቶኮ እና ድሪምስ ኤፍ ሲ በመጫወት ግልጋሎት ከሰጠ በኋላ ያለፉትን አንድ የውድድር ዘመን በደቡብ አፍሪካው ሴኩንኩኔ ቆይታ የነበረው ይህ የመሀል ተከላካይ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ደግሞ መድንን ተቀላቅሏል፡፡

ሌላኛው ክለቡን የተቀላቀለው ጋናዊው የአማካይ ስፍራ ተጫዋች ኡማር በሽር ነው፡፡ በቁመት ዘለግ ያለው ይህ ተጫዋች በሀገሩ ጋና ክለቦች አሻንቲ ኮቶኮ እና ዋፋ በመጫወት አሳልፎ መዳረሻቸውን የሀገራችን ክለብ መድን ሆኗል፡፡

ሦስተኛው ፈራሚ ደግሞ በባህርዳር ሲደረግ በነበረው የአማራ ባንክ ጣና ዋንጫ ላይ ለቡል ኤፍ ሲ ሲጫወት የነበረው እና የውድድሩ ከፍተኛ ግብ አስቆጠቀሪ የነበረው ዩጋንዳዊው አጥቂ ሳይመን ፒተር ኦኬች ነው።