ሉቺያኖ ቫሳሎ – የታላቁ ተጫዋች ረጅም የህይወት ጉዞ

ኢትዮጵያ ብቸኛ የአፍሪካ ዋንጫ ድሏን ካጣጣመች እነሆ 60 ዓመታት ያህል ተቆጠሩ። አገሪቱ ወርቃማ የእግርኳስ ዘመኗን የሚደግምላት ትውልድ ሳታገኝ ጀብድ የፈጸሙላት ጀግኖቿንም በወጉ ሳታከብር ግማሽ ክፍለ ዘመን ተሻገረች። በኢትዮጵያ እግርኳስ ኗሪ ታሪክ ሰርተው የመረሳት ሰለባ ከሆኑ ባለውለተኞች መካከል ሉቺያኖ ቫሳሎ ቀዳሚው ነው። ዳሚያኖ ቤንዞኒ በሉቺያኖ ቫሳሎ ግለ-ታሪክ ዙሪያ ከተጻፈውና  “ STELLA d`AFRICA“ ከተሰኘው መጽሃፍ ቀንጭቦ በየሦስት ወሩ አንዴ በሚታተመው የ” The Blizzard ” መጽሄት ድረ ገፅ ላይ ያቀረበውን የዚህን ታላቅ የኢትዮጵያ እግርኳስ ትዕምርት ረጅም የህይወት ጉዞ የሚያስቃኝ ጽሁፍ ከአራት ዓመታት በፊት ሚልኪያስ አበራ ወደ አማርኛ መልሶት በዚሁ አምድ ሥር ማቅረባችን ይታወሳል። ይህ ጽሁፍ መጠነኛ አርትዖት ተደርጎበት በድጋሚ ቀርቧል፡፡


በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ ውስጥ ብቸኛው እና ትልቁ ድል ሲገኝ የቡድኑ መሪ – በኤርትራ የተወለደው፣ ባለ ቅይጥ ዜግነቱ፣ በጣሊያንኛ ስም የሚጠራው የያኔው ታላቁ ተጫዋች ሉቺያኖ ቫሳሎ ነበር፡፡ የዚህ ታላቅ ሰው ታሪክ አንድም በታላቅ ስኬትና ጀብድ የሚነሳ በሌላ በኩል ደግሞ በመገለል፣ ጭቆና እና ስደት የተከበበ ነው፡፡

በአስመራ ሲኒማ ኢምፔሮ የፋሽስት ኢጣልያ የስነ-ህንፃ ውርስ እንደሆነው ሁሉ ሉቺያኖ ቫሳሎ ደግሞ ከባዱን የማንነት ክፍፍል ጥያቄ የሚወክል ኮከብ ነበር፡፡ ሉቺያኖ የተወለደው ከጣሊያናዊ የቱስካን ወታደር አባት ቪቶሪዮ ቫሳሎ እና ከኤርትራዊት እናቱ መብራቅ አብርሃም ነበር፡፡ ቫሳሎ በኤርትራ ይኖሩ ከነበሩት በርካታ ቅይጥ ማንነት ካላቸው ዜጎችም አንዱ ነበር፡፡

ከምንም ነገር ቀልድና ጨዋታ በመፍጠር የሚታወቀው ሉቺያኖ በአስመራ ጭርንቁስ መንደሮች እግርኳስን መጫወት ጀመረ፡፡ በአርነት (ነፃነት) ጎዳና ለሲኒማ ኢምፔሮ ቅርብ የሆነውና በአስመራ ከሚገኙ ኃይማኖታዊ ትምህርት ቤቶች አንዱ የነበረው ኮሌጂዮ ላቬላ የሉቺያኖ የእግርኳስ ህይወት በጥሩ ሁኔታ እንዲጀምር ጥርጊያውን ከፍቷል፡፡ ይህ የካቶሊክ ካቴድራል ትምህርት ቤት ስቴላ አስመሪና (የአስመራ ኮከብ) ተብሎ የሚጠራ የእግርኳስ ቡድን ነበረው፡፡ ጥቁርና ነጩ የቡድኑ መለያ በጣልያን- ኤርትራዊ (ኢታሎ-ኤርትራ) ጥንድ-ማንነት ላይ የተመሠረተው ቡድን መገለጫ ሆነ፡፡ በወቅቱ ክለቡ የተቋቋመበት ዋነኛ ምክንያት የቤተክርስቲያኗ አስተዳደሮች በከተማዋ በሚኖሩ ክልስ ታዳጊዎች አዕምሮ ውስጥ የሰፈነውን አሉታዊ የስነ-ልቦና ተጽዕኖ ለማስወገድ እንዲያስችል ታስቦ ነበር፡፡ በጊዜው ከጣልያናውያን አባቶች የሚወለዱ ልጆች በአባቶቻቸው ያለመፈለግ ችግር ይገጥማቸዋል፡፡ በኤርትራውያኑ ዘንድም ቢሆን የጨቋኙና ቅኝ ገዢው ዘር በመሆናቸው የመገለል እና የመነጠል ጫና ይደርስባቸዋል፡፡

ሉቺያኖ በስቴላ አስመሪና በግራ መስመር ተከላካይነት መጫወት ቢጀመርም ከቡድኑ ጋር ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ቆይታ አላደረገም፡፡ ጥቁርና ነጮቹ የተጫዋቹን ፍላጎት የማሟላት ድክመትን አሳዩ፡፡ ሉቺያኖም የሌሎች ክለቦችን ትኩረት አገኘ፡፡ የአገሪቱ የምድር ባቡር ሰራተኞች ጠርተው አወያዩት፡፡ ግሩፖ ስፖርቲቮ ፌሮቬሪ በኤርትራ የባቡር ድርጅት ክለብ ነበር፡፡ ድርጅቱ በባቡር መንገድ ጥገና ሰራተኝነትና በተጫዋችነት ሉቺያኖን ለመቅጠር ቢደራደርም የተጫዋቹ ልብ ግን ወደ ሰማያዊ ለባሾቹ ገጀረት አደላ፡፡

በከፍተኛ የኑሮ ውጣ ውረድ ውስጥ ያለፉ የኤርትራ ተወላጆችን የያዘው ይህ ቡድን የሉቺያኖ ማረፊያ ሆነ፡፡ የቡድኑ አባላት በከፍተኛ አንድነትና ጠንካራ የቡድን መንፈስ የተሳሰሩ ነበሩ፡፡ የተለያዩ የገንዘብ ማግኛ ዘዴዎችን በመጠቀምና በየሳምንቱ መጠነኛ መዋጮ በማሰባሰብ የቡድኑን የበጀት እጥረት ለመቀነስ ይጥሩ ነበር፡፡ ከቡድኑ ዋነኛ ሰዎች አንዱ ጸጋየ ባህረ ነበረ፡፡ ይህ ሰው በኤርትራ እግርኳስ ፌዴሬሽን ይሰራ የነበረና በኋላም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን በምክትል አሰልጣኝነት ያገለገለ ነው፡፡ ሉቺያኖ በገጀረት እ.ኤ.አ ከ1953 ዓ.ም -1958 ዓ.ም ባሳለፈው የስድስት አመታት ቆይታ ቡድኑ ወደ ከፍተኛው የሊግ እርከን እንዲያድግ አይነተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ወደ ከፍተኛው ዲቪዚዮን ባለፉበት አመትም ገጀረት ከጣልያን ቡድኖች አንዱ በነበረው ግሩፖ ስፖርቲቭ ቪስቲኒቲ ላይ የተቀዳጀው የ 4-0 ድል የሉቺያኖን የላቀ ችሎታ ያሳየ ነበር፡፡ በጨዋታው ሉቺያኖ ያሳየው ብቃት ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለመጫወት ያስቻለውን የመጀመሪያ ጥሪ አስገኘለት፡፡

በጣልያንኛ “ሎ ስፖርት ኤርትሪዮ – ክዌስቺኒ ዲ አይደንቲታ ኤድ ኦርጎግሊዮ” የሚል ርዕስ ይዞ የተጻፈ መጽሃፍ አለ፡፡ “የኤርትራ ስፖርት – የማንነትና የክብር ጥያቄ” በሚል በእንግሊዝኛ ተተርጉሞ ታትሟል፡፡ በመጽሃፉ ላይ ጣሊያናዊው አጥኚ ማርኮ ባጎዚ ስለዚህ ቡድን አመሠራረት “ባለ ብርቱካናማ መለያው ዲፖላቬሮ ሲሴሮ በኤርትራ ሻምፒዮና መሳተፍ የጀመረው አ.ኤ.አ. በ1937/38 የውድድር ዘመን ነው፡፡ ይህ ሻምፒዮና በጣልያን እግርኳስ የውድድር እርከን 4ኛ ዲቪዚዮን ውስጥ እንዲቀላቀል ተደርጎም ነበር፡፡” ብሏል፡፡

ፍራንቼስኮ ሲሴሮ ወደ ጣልያን የተጓዘው እ.ኤ.አ. በ1915 ነበር፡፡ ሲሴሮ በአስመራና በቀይ ባህሯ የወደብ ከተማ – ምጽዋ – መካከል እየተመላለሰ በበርካታ የንግድ ዘርፎች ይሳተፍ ጀመር፡፡ በእንጨትና መስታወት ስራዎች፣ ፋብሪካዎችን በማስተዳደር እንዲሁም በአስመራ አውራ ጎዳናዎች ትልልቅ ባዛሮችን በማዘጋጀት እውቅና ማግኘት ቻለ፡፡ በምጽዋ – ሊዶ – የተባለውን ሬስቶራንትና የፒያኖ ባር በመክፈት ታዋቂው የሙዚቃ አቀንቃኝ ሬናቶ ካሮሶኔ በኤርትራ ተቀባይነት እንዲያገኝ ትልቅ ተጽዕኖ ማሳረፉን ተያያዘው፡፡ ይህን የሲሴሮ ስኬታማ የኤርትራ ቆይታ ልጁ ሮቤርቶ “ማይ ታክሊ” በተባለው የጣልያን-ኤርትራ መጽሔት ላይ አውስቷል፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላም ክለቡ ቀዳሚ መጠሪያውን ከዲፖላቬሮ ሲሴሮ ወደ ግሩፖ ስፖርቲቮ አስመራ በመቀየር የመለያ ቀለሙንም ወደ ቀይና ሰማያዊ ለወጠ፡፡ በእርግጥ ከዓመታት በኋላም በድጋሚ የመለያ ቀለሙ ወደ ቀይና ጥቁር መቀየሩ አልቀረም፡፡

ግሩፖ ስፖርቲቮ አስመራ በአሰልጣኝ ኤንዞ አርቺዮሊ አመካኝነት ሶስት የሊግ ዋንጫዎችን እ.አ.አ. በ1945፣ በ1947 እና በ1948 ማሸነፍ ቻለ፡፡ ሉቺያኖ ወደዚህ ክለብ በገባበት ጊዜ ቡድኑን በአምበልነት የሚመራው በአስመራ የሚገኙ የጣልያን ስፖርተኞች ምልክት የነበረው እና ‘ኤርትራዊው ሄሬራ’ በመባል የሚታወቀው ማሲሞ ፌኒሊ ነበር ፡፡ ፌኒሊ በጣሊያን እንደተወለደ ቤተሰቦቹ ይዘውት ወደ አስመራ መጡ፡፡ ጣልያናዊው ተጫዋች እ.ኤ.አ. እስከ 1974 ዓ.ም በነበረው የኤርትራ ቆይታው በአገሪቱ እግርኳስ ላይ ትልቁን አሻራ ያሳረፈ ሰው መሆን ችሏል፡፡ ሆኖም በ1974 በተፈጠረው የመንግሥት ለውጥ ሳቢያ ወደ አገሩ ጣልያን ተመለሰ፡፡ ፌኒሊ በኤርትራ በተለያዩ የስፖርት ዘርፎች የሻምፒዮንነት ክብሮችን ተቀዳጅቷል፡፡ በቅርጫት ኳስ፣ በእጅ ኳስና በጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮን ከመሆኑም በላይ በእግርኳስ በግሩፖ ስፖርቲቮ አስመራ ሁለት የኤርትራ ሻምፒዮና ድሎችን እ.ኤ.አ. በ1963 እና በ1964 በተጫዋችነት እንዲሁም አ.ኤ.አ. በ1972 እና በ1973 በአሰልጣኝነት አግኝቷል፡፡ በ1974 ደግሞ ከእምባይሶራ ጋር የኢትዮጵያ ሻምፒዮናን አሸንፏል፡፡ በወቅቱም ፌኒሊ የጣሊያን የስፖርት ሚዲያን ትኩረት ስቦ ነበር፡፡ ተጫዋቹ በጣልያኑ ክለብ ቦሎኛ በነበረው አጭር ቆይታ በጥቂት የወዳጅነት ጨዋታዎች ተሠልፎ ተጫውቷል፡፡ በኤርትራ የቅርጫት ኳስ ብሄራዊ ቡድንም የመሠለፍ እድልን አግኝቷል፡፡

ቀጣዩ የሉቺያኖ የክለብ ዝውውር በክልስነቱ የሚፈጠርበትን አሉታዊ ተጽዕኖ በጉልህ ያመላከተ ነው፡፡ በ1950ዎቹ መጨረሻ ግሩፖ ስፖርቲቮ አስመራ የተባለው የጣልያኖች ቡድን ለሉቺያኖ የኮንትራት ጥያቄ አቀረበለት፡፡ የወቅቱ የክለቡ ፕሬዚዳንት ሰርጂዮ ሴሬኞ ወርሀዊ 600 የኢትዮጵያ ብር ደመወዝ እና በጣሊያኖቹ በሚተዳደረው የባቡር ትራንስፖርት ከፍተኛ ባለስልጣን መስሪያ ቤት ውስጥ በመደበኛ ስራ የመቀጠር እድል አመቻቹለት፡፡ ለተጫዋቹ የቀረበለት ይህ ግብዣ እምቢ የሚለው አልነበረም፡፡ እናቱን እንዲሁም ሁለቱን ታናናሽ ወንድምና እህቱን (ኢታሎ እና ሊና) የሚረዳበትን አጋጣሚ ፈጠረለት፡፡ ክለቡ ግሩፖ ስፖርቲቮ አስመራ ሲመሠረት ስያሜው ዲፖላቮሮ ሲሴሮ እንደነበር ከላይ ተገልጧል፡፡ ይህን መጠሪያ ያገኘውም ታዋቂው ጣልያናዊ ስራ ፈጣሪ (ኢንተርፕረነር) ፍራንቼስኮ ሲሴሮና በዘመኑ በፋሽስቶች ከሚመሩት የእግርኳስ ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው ይህ ክለብ በጋራ የመስራት ስምምነትን ከፈጠሩ በኋላ ነው፡፡

ሉቺያኖ ወደ ግሩፖ ዲፖርቲቮ አስመራ ሲገባ እድሜው በ20ዎቹ አጋማሽ ላይ ይገኝ ነበር፡፡ በአዲሱ ክለቡ ከተከላካይነት ወደ አማካይነት ተለወጠ፡፡ በሂደት ብልህ የጨዋታ አቀናባሪ ሆነ፡፡ ጨዋታ የመምራት ብቃቱም አደገ፡፡ ሉቺያኖ በአስገራሚ ብቃቱ ብዙዎችን ማስደመሙን ቀጠለ፡፡ በጠንካራ ምቶቹ ይታወቅም ጀመር፡፡ በጊዜው ውጤታማ የነበረው ግሩፖ ስፖርቲቮ አስመራ እ.ኤ.አ. በ1959 በአፍሪካ ዋንጫ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን በወዳጅነት ጨዋታ አሸነፈ፡፡ ቡድኑ እ.ኤ.አ. በ1960 በተነሳው የተጫዋቾች ምስል ላይ የሉቺያኖ ጠየም ያለው የቆዳው ቀለም በጥቁርና ነጩ መለያ ከሚታዩት አስር ጣልያናውያን ተጫዋቾች የተለየ ያደርገዋል፡፡ ሉቺያኖ በዚህ ክለብ በመጫወቱ ከፍተኛ ጫና ደርሶበታል፡፡ አንድም – በኤርትራውያኑ በበጎ በማይታይ ክለብ (ግሩፖ ዲፖርቲቮ አስመራ) ይጫወታል፡፡ በቀድሞዎቹ ቅኝ ገዢዎች (ጣልያኖች) ምክንያት ክለቡ በአገሬው ህዝብ የተጠላ ሆኗልና፡፡ ሁለትም – ህዝቡ ሉቻኖን በዚህ ክለብ በመጫወቱ እንደ ከዳተኛ ቆጥሮታል፡፡

የሉቺያኖ የህይወት ውጣ ውረድ የሚመደበው ሌሎች ታሪክን ከቀየሩና በአገሪቱ ለውጥ ከፈጠሩ ሰዎች ጋር ነው፡፡ ይህ እውነት በአርነት ጎዳና ብቻ አይወሰንም፡፡ በአስመራ የሚገኘው ዋነኛ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ የሲሴሮ ስታዲየም ነበር ፡፡ ስታዲየሙ እ.ኤ.አ. በመስከረም 29-1938 በፍራንቼስኮ ሲሴሮ ተመርቆ የተከፈተና የራሱ ቡድን እንዲጫወትበት የተሰራ ነበር ፡፡ እ.ኤ.አ. በ1949 ስታዲየሙ ለጣሊያን የቀይ መስቀል ማህበር ተሰጠ፡፡ በአዲሶቹ የአገሪቷ አስተዳዳሪዎች ቁጥጥር ስር እንዳይውል ታስቦ የተደረገ ስጦታ ነበር ፡፡ በኋላም ሜዳው በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሥመ-ጥር ኢትዮጵያዊ የጦር መሪ በነበሩት ራስ አሉላ አባነጋ ስም እንዲጠራ ተወሰነ፡፡ ጀግናው ራስ አሉላ አባነጋ የጣሊያንን ጦር በታላቅ ጀብዱ በዶጋሊ እንዲሁም እ.ኤ.አ. በ1896 አድዋ ላይ ታሪካዊ ድል የተቀዳጁ ታላቅ የጦር መሪ ነበሩ፡፡

የአድዋው ሽንፈት በተለይ በጣሊያን ከፍተኛ ውዝግብን ፈጥሯል፡፡ በሽንፈቱ ምክንያት በአገሪቱ የነበሩት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተዘግተው የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ፍራንቼስኮ ክሪስፒም ከስልጣን ራሳቸውን አገለሉ፡፡ አዲሱ የስታዲየሙ ስያሜም እ.ኤ.አ. በ1962 በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ለተፈጠረው የመዋሀድ ውሳኔ መንገድ አመቻቸ፡፡ እ.ኤ.አ. በ1953 የኤርትራ የእግርኳስ ሻምፒዮና ከኢትዮጵያ የእግርኳስ ውድድር ጋር ተቀላቀለ፡፡ ከኤርትራ ሦስት ቡድኖች፣ ከሸዋ ክፍለ ሀገር እና ከሐረር ጠቅላይ ግዛት ሌሎች አምስት ቡድኖች ተውጣጥተው የ8-ክለቦች ሻምፒዮና ተጀመረ፡፡ በወቅቱ በኤርትራ ይኖር የነበረው 1.5 ሚሊየን ህዝብ ከ23 ሚሊየኑ የኢትዮጵያ ህዝብ አንፃር ሲታይ አነስተኛ መጠን ቢሆንም ኤርትራውያኖቹ ከጣሊያን ባገኙት ልምድ የስፖርት ባህላቸው ከኢትዮጵያ የተሻለ ደረጃ ነበረው፡፡   ያኔ የኤርትራ ቡድኖች በተለያዩ ውድድሮች ይሳተፉ ነበር፡፡ ይህ “ፕሮፖጋንዳ” የሚል ስያሜ የነበረው ውድድር በተለያዩ የኤርትራ ክፍሎች ወዲያው ተስፋፋ፡፡ ማርኮ ባጎዚ እ.ኤ.አ በ1936 “ኤል ሎቶሪያሌ” በተባለው የፋሽስቶች የስፖርት መጽሄት ላይ ከሰፈረው ጽሁፍ የሚከተለውን ይጠቅሳል፡፡ ”የኤርትራ ተወላጆች መጀመሪያ ውድድሩን ከግርግር ጋር ያገናኙት ነበር፡፡ ቀስ በቀስ ግን እየተላመዱት መጡ ፡፡ ህዝቡ እውነተኛ እግርኳስ ወዳድ ነበር፡፡ በፍጥነትም ከስፖርቱ ጋር ተቆራኘ፡፡ ታዳጊዎች የሚመለከቷቸውና እንደነርሱ ለመሆን የሚያልሙባቸው ተጫዋቾችን እያዩ የማደግ እድልን አገኙ፡፡”

እ.ኤ.አ በ1940ዎቹ የኤርትራ ቡድኖች ከጣልያኖቹ ጋር በመቀላቀል በሻምፒዮናው መሳተፍ ጀምረው ነበር፡፡ ሀማሴን የተባለው ቡድንም በውድድሩ ከቀድሞው አሸናፊ ግሩፖ ስፖርቲቮ አስመራ ጋር በተመሳሳይ ነጥብ የሁለተኛ ደረጃን ይዞ ለማጠናቀቅ በቃ፡፡ እጅግ ወሳኝ ተጫዋቻቸው አብርሃ ግዛው ነበር ፡፡ ሉቺያኖ ለባጎዚ በሰጠው ቃለ-ምልልስ አብርሃን ” ከትውልዱ የላቀና እውነተኛ አሸናፊ! ” ሲል ይገልፀዋል፡፡ አብርሃ ጥሩ የቅጣት ምት ባለሟል እንደነበር ይነገራል፡፡ ኤርትራዊ ሆኖ የጣልያን ክለብን መለያ የለበሰ የመጀመሪያው ተጫዋች ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በ1950ዎቹ መባቻ የአብርሃ የፊዮረንቲና ዝውውር ጫፍ ደርሶ በዘረኝነት ችግር እንዳልተፈፀመ በጊዜው በምስራቅ አፍሪካ ከነበሩ ጣሊያናውያን የስፖርት ጋዜጠኞች መካከል ታዋቂው ኤንሪኮ ማንዴ እ.ኤ.አ በ1952 አካባቢ በወጣው መጽሔት ላይ ባሰፈረው ጽሁፉ ያስረዳል፡፡

ከኢትዮ-ኤርትራ የእግርኳስ ሊግ ውህደት በኋላ በነበሩት ሰባት አመታት ከኤርትራ የመጡ ቡድኖች አራት ጊዜ ሻምፒዮን መሆን ችለዋል፡፡ ሐማሴን እ.ኤ.አ በ1955 እና በ1957 ሻምፒዮናውን ሲያሸንፍ፣ አካለ ጉዛይ በ1958 እና የቴሌኮሙኒኬሽን ስፖርት ክለብ (ኋላ ገጀረት ተብሎ የተጠራው) በ1959 የሻምፒዮንነት ክብርን ተጎናጽፈዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ1950ዎቹና በ1960ዎቹ አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አባላት ከኢትዮ-ኤርትራ ውህደት የተገኙ ተጫዋቾች ነበሩ፡፡ ከእነዚህ ተጫዋቾች አንዱ ሉቺያኖ ቫሳሎ ነበር፡፡ ሉቺያኖ እ.ኤ.አ በ1956 የመጀመሪያ የብሄራዊ ቡድን ጥሪ ደረሰው፡፡ ከዚያ በኋላ ከአስር ዓመታት በላይ ቁልፍ ተጫዋች ሆኖ ኢትዮጵያን አግልግሏል፡፡ በእርግጥ ሉቺያኖ ለብሄራዊ ቡድን ከተመረጠ በኋላ የተለያዩ ተግዳሮቶችን መቋቋም ነበረበት ፡፡ በጊዜው ኤርትራውያኑ ተጫዋቾች በኢትዮጵያውያኑ ላይ የነበራቸው ቅራኔ የህብረት ግንኙነቱን ቀላል አላደረገውም፡፡ ሉቺያኖ እንዲያውም ከታላቁ ኢትዮጵያዊ የእግርኳስ ሰው አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ጋር የነበረው ስምምነት መጀመሪያ ላይ ጥሩ የሚሰኝ አልነበረም።

ሉቺያኖ በግሩፖ ስፖርቲቮ አስመራ ለሁለት አመታት ከተጫወተ በኋላ ወደ ድሬዳዋው ጥጥ ማሀበር (ኮተን) አመራ፡፡ የወቅቱ የኢትዮጵያ ሻምፒዮን የነበሩት ኮተኖች ቡድናቸውን ለማጠናከር በሐማሴን ጥሩ አጥቂነቱን ያስመሰከረው የሉቺያኖ ታናሽ ወንድም ኢታሎን ጨምረው አስፈረሙ፡፡ ሁለቱም የሉቺያኖ ታናናሾች ኢታሎና ሊና ከሉቺያኖ እናት ከወ/ሮ መብራቅ አብርሀም እና ከሌላ አባት የተወለዱ ቢሆንም ስማቸው በአስመራ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በቫሳሎ እንዲጠራ ተመዝግቦ ኖሯል፡፡ አንቶኒዮ ፌልሲ በሉቺያኖ የህይወት ታሪክ መጽሐፍ (STELLA d`AFRICA – የአፍሪካ ኮከብ) ላይ ሁኔታውን ሲገልጸው “ሁሉም ልጆች በቫሳሎ ስም ተጠሩ፡፡ እጣ ፈንታቸውም እንዲሁ ተመሳሳይ ነበር፡፡ ጣሊያናዊው ወታደር ቢያንስ የአባት ስም ሰጣቸው፡፡ የቫሳሎ ቤተሰብም ተባሉ፡፡” ብሏል፡፡

በኮተን የሉቺያኖ የመጀመሪያ የውድድር ዘመን የተሳካ አልነበረም፡፡ ቡድኑ በከተማ ተቀናቃኙ ኢትዮ ሲመንት ከባድ ፉክክር ገጥሞት የዋንጫ ድሉን ማስጠበቅ ሳይችል ቀረ፡፡ እ.ኤ.አ ከ1960-1965 ድረስ ሁለቱ የምስራቅ ኢትዮጵያ ኃያላን በኢትዮጵያ ሻምፒዮና ላይ ከፍተኛ የበላይነት አሳይተዋል፡፡ ኮተን ክለብም በቫሰሎ ወንድማማቾች ብቃት ታግዞ ሶስት የሊግ ድሎችን እ.ኤ.አ በ1962፣ በ1963 እና በ1965 ተጎናፀፈ፡፡ ቡድኑ በአፍሪካ የአሸናፊዎች – አሸናፊ ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ ደርሶም ኩማሲ ላይ በማሊው ስታድ ማሊየን የ 3-1 ሽንፈት ገጠመው፡፡

በ3ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የቫሳሎ ወንድማማቾች የብቃት ከፍታ በገሀድ ታየ፡፡ የፍጻሜው ጨዋታ እ.ኤ.አ በጥር 1962 በአዲስ አበባ ስታዲየም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ተመልካችነት የተደረገ ነበር፡፡ ከሁለት አመት በፊት እ.ኤ.አ በ1960 አበበ ቢቂላ በሮም ኦሎምፒክ በባዶ እግሩ ሮጦ ባመጣው ተዓምራዊ የወርቅ ሜዳልያ ድል የአገሪቱን የስፖርት ግርማ ሞገስ ከፍ አድርጎት ነበር፡፡ በእርግጥ በ1960ው የአፍሪካ ዋንጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውጤት አስከፊ የሚባል ነበር፡፡ በሶስት ቡድኖች ተሳትፎ ብቻ በተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ኢትዮጵያ በተባበሩት አረብ ሪፐብሊክ (ግብጽ) እና ሱዳን 5 ጎሎች ተቆጥረውባት፤ ምንም ጎል ሳታስቆጥር ከውድድሩ ተሰናበተች፡፡ ይህ ደካማ ውጤት አቶ ይድነቃቸው ተሰማን አነቃቸው፡፡ በኤርትራውያን ተጫዋቾች ላይ የነበራቸውን ቸልተኝነኝትም እንዲተው አደረጋቸው ፡፡ የቡድኑ ድክመት አቶ ይድነቃቸው ቀድሞ በብሔራዊ ቡድኑ የሚታየውና ኤርትራውያንን ያለማካተት ልማድን እንዲለውጡ አስገድዷቸው በቡድኑ ውስጥ ከስድስት በላይ ቋሚ ተሰላፊ ኤርትራውያን ታዩ፡፡ አቶ ይድነቃቸው የአምበልነት ማዕረጉን ለሉቺያኖ ለመስጠት ባይፈልጉም በቡድን አጋሩ መንግስቱ ወርቁ ጉትጎታ ሉቺያኖ በአምበልነት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቡድን እንዲመራ ተደረገ፡፡

3ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በአራት ቡድኖች መካከል ነበር የተካሄደው፡፡ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ስታዲየም በተደረገው የመጀመሪያ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ በሉቺያኖ 2 ጎሎች፣ በመንግስቱ 1 ጎል እና በተክሌ ኪዳኔ (በገጀረት የሉቺያኖ የቡድን ጓደኛ) ተጨማሪ 1 ጎል አማካኝነት ኢትዮጵያ ቱኒዝያን 4-2 ረታች፡፡

በፍፃሜው ጨዋታ ግብጾች ባልተረጋጋው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ላይ በ35ኛው ደቂቃ በበደዊ አብድልፈታህ አማካኝነት ጎል አግብተው እስከ 75ኛው ደቂቃ ድረስ በመሪነት ዘለቁ፡፡በ75ኛው ደቂቃ ላይ ተክሌ ኪዳኔ ኢትዮጵያን አቻ አደረገ፡፡ የበደዊ ሁለተኛ ግብ ግብፅን ዳግም መሪ አደረገ፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ 6 ደቂቃዎች ሲቀሩ ሉቺያኖ ያስቆጠራት ግብ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ወደ ዳግም አቻነት መለሰች፡፡ ይህች ጎል የግብጾችን ሞራል አወረደች፡፡ በጭማሪው ሰዓት ኢትዮጵያውያኖች በተዳከሙት ግብጾች ላይ ከፍተኛ ብልጫን አሳዩ፡፡ ኢታሎና መንግሥቱ አከታትለው ጎሎችን በማስቆጠር ለብሔራዊ ቡድናቸው የ 4-2 ድልን አስገኙ፡፡ኢትዮጵያም የመጀመሪያውንና ብቸኛውን አለም አቀፍ ዋንጫ አሸነፈች፡፡

በአስመራ ከጣሊያናዊ አባትና ከኤርትራዊት እናት የተወለደው ሉቻኖ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አምበልነት ከአፄ ኃይለሥላሴ እጅ ዋንጫ ተቀብሎ ወደ ላይ ከፍ አደረገ፡፡ ጎሎች አስቆጥሮ የአፍሪካን ዋንጫ የማንሳት ሀሳብ በአዕምሮው መጥቶ እንደማያውቅ ሁሉ እጅጉን የሚያከብራቸው አጼ ኃይለሥላሴ ከአስራ ሁለት ዓመታት በኋላ መጨረሻቸው እንደዛ ይሆናል ብሎ አልጠበቀም፡፡ ሉቺያኖ የእርሳቸውን አይነት መሪ ተፈጥሯል ብሎ አያስብም፡፡

በኢትዮጵያ የንጉሳዊው አገዛዝ ስርዓት ሲያበቃና ደርግ ስልጣን ሲይዝ ሉቺያኖ ኳስ መጫወት አቁሞ ነበር፡፡ በጣሊያን ታዋቂ በሆነው የእግርኳስ አሰልጣኞች የትምህርት ማዕከል ኮቨርሲያኖ ከአርማንዶ ፒቺ ፣ ሴዛሬ ማልዲኒና ሉዊስ ቪንሲዮ ጋር በመማር የአሰልጣኝነት ባጁን (ፈቃዱን) ተረከበ፡፡ በዚሁም ወደ አሰልጣኝነት አለም ተቀላቅሎ በአዲስ አበባ ብዙም ስኬታማ ያልነበረ ቆይታን በቅዱስ ጊዮርጊስ አደረገ፡፡ በመቀጠልም ከአንድ አርመናዊ መካኒክ የቮልስዋገን ጋራዥ ገዛ፡፡ ከዚህ በኋላ ነበር ከደርግ ስርዓት ጋር የማይስማማባቸው በርካታ ምክንያቶች የተፈጠሩት።

የቫሳሎ ባለጠግነት፣ ክልስነት፣ ኤርትራዊነት፣ ከውጭ ዜጎች ጋር የነበረው ግንኙነት እና ከንጉሳውያን ቤተሰቦች ጋር የመሰረተው ወዳጅነት ከደርግ ጋር በእጅጉ አቃረነው፡፡ እ.ኤ.አ በ1976 ከብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነቱ ተነስቶ በጀርመናዊው ፒተር ሺንግተር ሲተካ ከጊዜያት በኋላ የብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች “አምፊታሚን ካፕታጎን” የተባለ አነቃቂ፣ ጉልበት ሰጪና የምግብ ፍላጎት የሚቀንስ መድሀኒት መጠቀማቸውን ማውገዙና መንቀፉ በአዲሱ መንግሥት በጠላትነት እንዲፈረጅ አደረገው፡፡ በአንዱ ማለዳ በሉቺያኖ ጋራዠ ውስጥ ከወታደራዊው መንግሥት ሰዎች አንደኛው መኪናውን አቁሞ ሊወስደው ይጠብቀው ጀመር፡፡ የቀድሞ ዝነኛና ባለውለታ ኳስ ተጫዋች መሆኑን የሚያውቅ ሌላ ኮሎኔል አግኝቶት ባያስለቅቀው ኖሮ የሉቺያኖ መጨረሻ ምናልባትም ያ ቀን ይሆን ነበር፡፡ አስደንጋጩ አጋጣሚ ሉቺያኖን ይበልጥ ጥንቁቅ እንዲሆን አገዘው፡፡ በእርግጥ ብሔራዊ ቡድኑን በድጋሚ እንዲያሰለጥን ጥያቄ ቀርቦለት እ.ኤ.አ በ1978 በአሰልጣኝነት የመጨረሻ ጨዋታው ምስራቅ ጀርመንን ታሪካዊ በሆነ ሁኔታ አሸነፈ፡፡ ከጨዋታው ሁለት ሳምንት በኋላም በጠዋት ወደ ጋራዡ ሄዶ የሁሉንም ሰራተኞች ደመወዝ ከፍሎ ወደ ጅቡቲ አመራ፡፡ ከጅቡቲም በካይሮ በኩል ወደ ሮም በረረ፡፡ ከወራት በፊት ለደህንነት ሲል ቤተሰቦቹን ወደ ሮም ልኮ ነበር፡፡

የቫሳሎ ወንድማማቾች ትልቅ ዋጋ ከፍለው ላስገኙት አስገራሚ ድል ከኢትዮጵያ ምንም አይነት ክብርና ምስጋና አላገኙም፡፡ በአዲስ አበባ የከተመው ኢታሎ የራሱን ሬስቶራንት እያስተዳደረ ኑሮውን ቢገፋም እ.ኤ.አ በ1998 ዓ.ም በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ወደ ሀገራቸው እንዲጓዙ ከተደረጉ ሌሎች 77,000 ኤርትራውያን ጋር ተሰደደ፡፡ ደርግ ሉቺያኖ ከኮበለለ በኋላ ምስጉን ስሙን ከተለያዩ መረጃዎች ላይ እንዲሰረዝ አድርጓል፡፡ ከዚያማ ለኢትዮጵያ ያደረገው በጎ ነገር በሙሉ ተሸፈነ፡፡ ከሁሉ የከፋው ግን በስደት ከሌላ ማንነት ጋር እንዲላመድ መደረጉ ነበር፡፡ ሉቺያኖ በጣልያን ቤተሰቦቹን ከተለያዩ ችግሮች መታደግ ነበረበት፡፡ ስለዚህ በአስቲያ ባህር ዳርቻ የመኪና ጥገና ጀመረ፡፡ ቆይቶም የራሱን ጋራዥ ከፈተ፡፡ ከሁለት አመት እድሜው ጀምሮ ሲከለከል የቆየው የጣሊያን ፓስፖርትም ተቀበለ፡፡ በሮም የወደብ ዳርቻም መጠለያውን አገኘ፡፡ ብዙ ችግሮችን ባየባት ከተማ ተቀምጦ ታሪኩን ማውጋቱን አያቆምም፡፡

በእርግጥም የሉቺያኖን ማንነት በአንድ ቃል ብቻ መግለጽ አስቸጋሪ ነው፡፡ ኤርትራዊ፣ ኢትዮጵያዊ ኢጣልያዊ፣ አፍሪካዊ፣ ባለ ጥምር ዜጋ (ክልስ) ስደተኛ፣ የተገፋ እና አሸናፊ!!!