የአምና የሊጉ አሸናፊዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊሶች አዲሱን የውድድር ዘመን አዲስ አዳጊዎቹ ኢትዮጵያ መድኖችን ላይ የግብ ናዳ በማውረድ አሀዱ ብለዋል።
የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ኳሱን ተቆጣጥረው በተለያዩ መንገዶች ለማጥቃት ጥረት ያደረጉበት በአንፃሩ ደግሞ ፍፁም ደካማ የነበሩት ኢትዮጵያ መድኖች ደግሞ ከኳስ ውጪ አብዛኛውን ጊዜ በማሳለፍ ለመከላከል የሞከሩቡት ነበር።
ገና ከጅምሩ ጫና ፈጥረው መጫወት የጀመሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች የመጀመሪያ ሁለት ሙከራዎቻቸውን ከመድን ተጫዋቾች ስህተት የተገኙ ነበሩ። በመጀመሪያዎቹ ሰከንዶች አስጨናቂ ፀጋዬ የተነጠቀውን ኳስ ቸርነት ጉግሳ ሞክሮ ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣችበት እንዲሁም በ7ኛው ደቂቃ ደግሞ ሀብታሙ ሸዋለም ከተሳሳተው ኳስ መነሻ ያደረገውን ማጥቃት እስማኤል ኦሮ-አጎሮ ከሳጥን ጠርዝ በቀጥታ ሞክሮ ለጥቂት ከግቡ አናት በላይ በወጣችበት ኳስ ሙከራዎችን ማድረግ ጀምረዋል።
ጫና ፈጥረው መጫወታቸውን የቀጠሉት ጊዮርጊሶች በ21ኛው ቀዳሚ መሆን ችለዋል ፤ ዳዊት ተፈራ ከመሀል ያቀበለውን ኳስ እስማኤል ኦሮ-አጎሮ ተመስገን ተስፋዬን ሸፍኖ ከዞረ በኋላ ከሳጥኑ ጠርዝ በግሩም ሁኔታ አክርሮ የመታት ኳስ ከመረብ ተዋህዳ ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችላለች።
የቅዱስ ጊዮርጊሶች ፍፁም የሆነ የበላይነት በተመለከትንበት የመጀመሪያ አጋማሽ በተለይም ቢኒያም በላይ እና ሄኖክ አዱኛ በተሰለፉበት የቀኝ መስመር በኩል ተደጋጋሚ ዕድሎችን ሲፈጥር ተመልክተናል። በተጨማሪነትም ሳጥን ውስጥ ከመገኘት ባለፈ በነፃነት እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ የነበረው ኦሮ-አጎሮ ለቡድኑ አጋሮቹ አጋጣሚዎችን ለመፍጠርም ሲጥር ያስተዋልንበት አጋማሽ ነበር።
ተደጋጋሚ ዕድሎችን መፍጠራቸውን የቀጠሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ31ኛው ደቂቃ ጋቶች ፖኖም ከሳጥን ውጭ በቀጥታ እንዲሁም በ41ኛው ደቂቃ ላይ እስማኤል ኦሮ- አጎሮ ከቀኝ ያሻውን ኳስ ቸርነት በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት ወደ ውጪ በወጣችበት አጋጣሚ የመድኖችን ግብ ማንኳኳት ቀጥለዋል።
በ43ኛው ደቂቃ ታድያ ቅዱስ ጊዮርጊሶች መሪነታቸውን ወደ ሁለት ማሳደግ የቻሉበትን ግብ አግኝተዋል። ሀብታሙ ሸዋለም በአደገኛ ስፍራ ከተነጠቀው ኳስ የጀመረው ማጥቃት ቸርነት ጉግሳ ወደ ሳጥን ውስጥ ያሳለፈለትን ኳስ እስማኤል ኦሮ-አጎሮ ተቆጣጥሮ በግሩም ሁኔታ ከመረብ ማዋሀድ ችሏል።
ጫና መፍጠራቸውን የቀጠሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ45ኛው ደቂቃ ሄኖክ አዱኛ ከቀኝ የሳጥን ጠርዝ ወደ ውስጥ ያሳለፈለትን ኳስ ቸርነት ጉግሳ ወደ ግብ ሞከሮ አቡበከር ኑራ ያዳነበት ኳስ አስቆጭ ሙከራ ነበር። መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨመረው አንድ ደቂቃ ላይ ዳዊት ተፈራ ያሻማውን የማዕዘን ምት ኳስ ልማደኛው ፍሪምፖንግ ሜንሱ ካልተጠበቀ ስፍራ በግንባሩ ገጭቶ አቡበከር ኑራ መረብ ላይ በማሳረፍ የመጀመሪያው አጋማሽ በፈረሰኞቹ የ3-0 መሪነት እንዲጠናቀቅ አስችሏል።
በጨዋታው የዕረፍት ሰዓት የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር በበላይ ጠባቂው አቶ አብነት ገ/መስቀል አማካኝነት በ2014 የወድድር ዘመን በመጨረሻዎቹ 9 የጨዋታ ሳምንታት የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር እና ነዋሪው ላደረገላቸው የላቀ መስተንግዶ የምስጋና ምስክር ወረቀት እና የማስታወሻ ዋንጫ ለከተማው ከንቲባ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) አበርክተዋል።
ኢትዮጵያ መድኖች በመጀመሪያ አጋማሽ የነበረባቸውን የመከላከል ክፍተት ለማረም በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ አማካዩን አሚር ሙደሲር አስወጥተው ሙሉ ጤንነት ላይ የማይገኘውን የመሀል ተከላካያቸው ፀጋሰው ቢያስገቡም ጨዋታው ከዕረፍት እንደተመለሰ ፈረሰኞቹ አራተኛ ግባቸውን አግኝዋል። ቢኒያም በላይ ከቀኝ የሳጥን ጠርዝ ወደ ውስጥ ያሳለፈለትን ኳስ እስማኤል ኦሮ-አጎሮ ከተቆጣጠረ በኋላ በግሩም ሁኔታ በመዞር የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ሐት-ትሪክ የሰራበትን ግብ አስቆጥሯል።
ምንም እንኳን በጉዳት እና ባልተጠናቀቁ የወረቀት ስራዎች በርከት ያሉ የመጀመሪያ ተሰላፊ ተጫዋቾቻቸውን ማግኘት ያልቻሉት ኢትዮጵያ መድኖች ሜዳ ላይ በመከላከሉ ረገድ የነበራቸው አደረጃጀት ፍፁም ደካማ የነበረ ሲሆን ከኳስ ጋርም የተሳኩ ጥቂት ቅብብሎችን እንኳን ለማድረግ ተቸግረው አስተውለናል። በ58ኛው ደቂቃ ላይ የመድኑ ግብ ጠባቂ አቡበከር ኑራ ቢኒያም በላይ ላይ በሰራው ጥፋት ፈረሰኞቹ ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት በጨዋታው ጥሩ ሲጥር የነበረው ቸርነት ጉግሳ ወደ ግብነት ቀይሯታል።
ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሳጥን ቀርበው ሙከራ ለማድረግ አንድ ሰዓት መጠበቅ የተገደዱት ኢትዮጵያ መድኖች በሀቢብ ከማል እና ተቀይሮ በገባው ኪቲካ ጀማ አማካኝነት በግል ከሚያደርጓቸው ጥረቶች ውጭ ለተቆጠሩባቸው ግቦች ምላሽም መስጠት የሚያስችል ቁመና ላይም አልነበሩም።
ፍፁም በነፃነት መጫወታቸውን የቀጠሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ68ኛው ደቂቃ ላይ በሜዳው የላይኛው ክፍል የነጠቁትን ኳስ ቢኒያም በላይ እየነዳ ወደ ሳጥን ከደረሰ በኋላ ወደ ውስጥ ያሳለፈውን ኳስ በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ተከላካዩ ፀጋሰው ድማሞ በራሱ ግብ ላይ አስቆጥሯል። መደበኛው የጨዋታ ደቂቃ ሊጠናቀቅ በተቃረበበት በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ተገኑ ነጋሽ ከተከላካይ ጀርባ የተጣለለትን ኳስ ተጠቅሞ ለቡድኑ 7ኛውን ግብ አስቆጥሯል።
ነገር ግን በ92ኛው ደቂቃ ላይ ሀቢብ ከማል ከቀኝ መስመር ወደ ውስጥ ያሻማውን ኳስ ብሩክ ሙሉጌታ በግንባሩ በመግጨት ኢትዮጵያ መድኖችን በባዶ ከመሸነፍ የዳኑበትን ብቸኛ ግብ ማስቆጠር ችሏል።
በፈረሰኞቹ ፍፁም የሆነ የበላይነት 7-1 በሆነ ውጤት ከተጠናቀቀው ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች በሰጡት አሰተያየት አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ የተከላካይ መስመራቸው በጉዳት መሳሳት እና የብስለት ጉዳይ ልዩነት ፈጥሯል ሲሉ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ደግሞ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በመጀመሪያ ጨዋታዎች ላይ የነበረብንን የትኩረት ማጣት አሻሽለን መምጣታችን ደስተኛ አድርጎኛል ሲል ሀሳቡን ሰጥቷል።