ሪፖርት | ድሬዳዋ እና ሲዳማ የዓመቱን የመጀመሪያ አቻ አስመዝግበዋል

ጥሩ ፉክክር በተደረገበት በድሬዳዋ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ጨዋታ ሲዳማ ሁለት ጊዜ መምራት ቢችልም ድሬዳዋ ጨዋታው በ2-2 ውጤት እንዲጠናቀቅ አድርጓል።

የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ማራኪ ፉክክር ያስተናገደ ነበር። ወደ ሁለቱ ሳጥኖች የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን በማስመልከት የጀመረው ፍልሚያ 7ኛው ደቂቃ ላይ ጎል ለማስተናገድ ተቃርቦ ነበር።
ሳላዲን ሰዒድ ከግራ ከይገዙ ቦጋለ ተቀብሎ ሳጥን ውስጥ ዞሮ የመታው ይህ ኳስ የመጀመሪያው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ሆኖ በፍሬው ጌታሁን ልዩ ጥረት ድኗል።

የሁለቱም ቡድኖች ፈጣን ሽግግሮች የታጀበው ጨዋታ የሲዳማዎች የተሻለ ጫና ፈጣሪነት ታይቶበታል። በድሬ በኩል ወደ ቀኝ መስመር ያደላ ጥቃት ይስተዋል የነበረ ቢሆንም ወደ መጨረሻ የግብ ዕድልነት ሳይቀየር ቆይቷል። ተጋጣሚን በማስከፈት በንፅፅር የተሻለ ሂደት ያሳዩ የነበሩት ሲዳማዎች ባገኙት ሌላ አደገኛ ዕድል 16ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ ፈጣን ጥቃት ሰንዝረው ፍሬው ሰለሞን ነፃ ዕድል አግኝቶ የመጀመሪያ ንክኪው ባለመሳካቱ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

ከዚህ ሙከራ በኋላ ጨዋታው በተመጣጠነ ፉክክር ቀጥሎ ሲዳማዎች በግራ መስመር 31ኛው ደቂቃ ላይ ያስጀመሩት ስኬታማ ጥቃት ወደ ጎልነት ተቀይሯል። ሳጥን ውስጥ ሳላዲን ሰዒድ ከግራ ያሻገረውን ይገዙ ቦጋለ ሲጨርፈው በቀኝ ነፃ ሆኖ የደረሰው እንዳለ ከበደ ሲዳማ ቡናን ቀዳሚ ያደረገበትን ጎል አስቆጥሯል።

ከሜዳቸው በጥሩ ፍጥነት መውጣት ቢችሉም በሳጥኑ መግቢያ ላይ ጥቃታቸው ይቋረጥባቸው የነበሩት ድሬዳዋ ከተማዎች ግን ከስምንት ደቂቃ በኋላ አቻ የሆኑበትን ጎል ከማዕዘን ምት አግኝተዋል። በዚህም አብዱለጢፍ መሐመድ ያሻማውን የማዕዘን ምት 38ኛው ደቂቃ ላይ እንየው ካሳሁን በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሯል።

ከዕረፍት መልስም ጨዋታው ሳቢነቱ ቀጥሎ አፍታም ሳይቆይ ጎል አስተናግግዷል። 47ኛው ደቂቃ ላይ ሳላዲን ሰዒድ እንየው ካሳሁን በእጁ መንካቱን ተከትሎ የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት አስቆጥሮ ሲዳማን ዳግም መሪ ማድረግ ችሏል አድርጓል።

ድሬዎች ምላሽ ለመስጠት ወዲያውኑ ከፍ ያለ ጫና መፍጠር ሲጀምሩ 49ኛው ደቂቃ ላይ አብዱለጢፍ መሐመድ ከቀኝ የማዕዘን ምት መምቻ ጋር ከተገኘ ቅጣት ምት ወደ ግብ የላከው ኳስ ለጥቂት በመክብብ ደገፉ ድኖበታል።

ተቀይሮ በገባው ጋዲሳ መብራቴ 58ኛው ደቂቃ ላይ ኢላማውን የጠበቀ የቅጣት ምት ሙከራ ያደረጉት ድሬዳዋዎች ምላሽ ለመስጠት ጫን ቢሉም በሚፈልጉት ልክ ሲዳማን ሳያስጨንቁ ቆይተዋል። ነገር ግን 64ኛው ደቂቃ ላይ የብርቱካናማዎቹ አማካይ ዮሴፍ ዮሐንስ ከረጅም ርቀት በአስደናቂ ሁኔታ አክርሮ የመታው ኳስ በመክብን ደገፉ መረብ ላይ አርፎ ጨዋታውን ወደ አቻ ውጤት መልሶታል።

በቶሎ የማጥቃት ሪትማቸውን መልሰው ባገኙት ሲዳማዎች በኩል ግብ አስቆጣሪው እንዳለ ከበደ 68ኛው ላይ እንደጎሉ ሁሉ በቀኝ ነፃ ሆኖ ገብቶ በመምታት 71ኛው ላይ ደግሞ ሳላዲን ሰዒድ ከማዕዘን ተሻምቶ በግንባሩ የገጨውን ኳስ በመጭረፍ ለራሱ ሁለተኛ ግብ ለማስቆጠር ተቃርቦ ነበር። በሜዳቸው ቀርተው የሲዳማን ጥቃት በማርገብ ፈጣን ጥቃት መሰንዘርን ምርጫቸው ባደረጉት ድሬዳዋዎች በኩልም 75ኛው ደቂቃ ላይ አጥቂው ቢኒያም ጌታቸው ከመልሶ ማጥቃት በቀኝ ከረጅም ርቀት ያደረገው ጥሩ ሙከራ ወደ ውጪ ወጥቷል።

ተጨማሪ ግብ አስቆጥሮ ጨዋታውን ለማሻነፍ የሚደረገው ትግል በሁለቱም በኩል ቀጥሎ ጨዋታው ወደ ማብቂያው ሲቃረብ ሌላ ክስተት አስተናግዷል። 90ኛው ደቂቃ ላይ የሲዳማው ተከላካይ ጊትጋት ጉት ብሩክ ቃልቦሬ ላይ በሰራው ጥፋት በሁለተኛ ቀይ ካርድ ፣ የድሬዳዋው አማካይ ኤልያስ አሕመድ ደግሞ ከዳኛ ጋር እሰጥ አገባ በመፍጠሩ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥተዋል።

ከጨዋታው በኋላ ባተሰጡ አስተያየቶች የሲዳማ ቡናው አሰልጣኝ ወንድምአገኝ ተሾመ የሚታረሙ ነገሮች ቢኖሩም ጨዋታው ጥሩ እንደነበረ ገልፀው የጊት ጋት ዘንድሮም ቀይ ማየት በምክር እንደሚስተካከል እንዲሁም የማሸነፍ ሥነ ልቦናቸው በሂደት እንደሚገነባ አንስተዋል። አሰልጣኝ ዮርዳኖስ አባይ በበኩላቸው ገብቶባቸው ከኋላ ተነስተው ነጥብ መጋራታቸው ጥሩ መሆኑን አንስተው ቡድናቸው ይበልጥ እየተሻሻለ እንደሚሄድ ዕምነታቸውን በመግለፅ በተደጋጋሚ የሚታዩ ስህተቶችን ለማረም ምንደሚሰሩ ጠቁመዋል።