ኢትዮጵያ ቡና የውጪ ዜግነት ያለው ግብ ጠባቂ አስፈርሟል

ኢትዮጵያ ቡና የግብ ጠባቂ ኮታውን በቦትስዋናዊ የግብ ዘብ ማሟላቱ ታውቋል።

ኢትዮጵያ ቡና በአሰልጣኝ ተመስገን ዳና መሪነት በርካታ አዳዲስ ተጫዋቾችን በማስፈረም የ2015 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታውን በነገው ዕለት ወላይታ ድቻን በመግጠም ይጀምራል።

ክለቡ የመጨረሻው ሊሆን በሚችል ቅጥር ከሳምንት በፊት የኬኒያ ዜግነት ያለውን ግብ ጠባቂ ጃኮብ ሆሳኖን ለማስፈረም ተቃርቦ በልምምድ ወቅት ተጫዋቹ ባሳየው አቋም ሀሳቡን የቀየረ ሲሆን አሁን ደግሞ ፊቱን ወደ ሌላ ግብ ጠባቂ በማዞር ወደ ስብስቡ እንደቀላቀለው ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡

በዚህም መሰረት የቦትስዋና ዜግነት ያለው ኤዝቄል ሞራኬ አዲሱ የኢትዮጵያ ቡና ግብ ጠባቂ ሆኗል፡፡ 1 ሜትር ከ81 ሴንቲ ሜትር የሚረዝመው የ26 ዓመቱ ግብ ጠባቂ እግር ኳስን በሀገሩ ክለብ ሳትሞስ በመጫወት የጀመረ ሲሆን በመቀጠል ወደ ደቡብ አፍሪካ ተጉዞ በቲኤስ ጋላክሲ ቆይታ ነበረው።

በቦትስዋና ብሔራዊ ቡድን ውስጥ የመጫወት ዕድልን ያገኘው ግብ ጠባቂው በድጋሚ ወደ ሀገሩ ተመልሶ ጅዋንግ ጋላክሲ በተባለ ክለብ ውስጥ ከተጫወተ በኋላ ቀጣይ መዳረሻውን ኢትዮጵያ ቡና አድርጓል፡፡ ተጫዋቹ የሥራ እና የመኖሪያ ፍቃድ ሰነዶችን ካሟላ በኋላ በቡና መለያ እንደምንመለከተው ይጠበቃል። ክለቡ በማህበራዊ ገፁ ማምሻውን እንዳሳወቀው ደግሞ አቶ አሮን ታሪኩን በቪዲዮ ተንታኝነት በአሰልጣኝ ቡድን አባላቱ ውስጥ ማካተቱ ታውቋል።