የሦስተኛ ቀን የሊጉ ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች

በመጀመሪያው ሳምንት የሊጉ የሦስተኛ ቀን ውሎ የሚደረጉ ሁለት ፍልሚያዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አጠናክረናል።

ወላይታ ድቻ ከ ኢትዮጵያ ቡና

በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት አምስተኛ እና ስድስተኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁት ወላይታ ድቻ እና ኢትዮጵያ ቡና ነገ 7 ሰዓት የዘንድሮውን ዓመት የመጀመሪያ ጨዋታ ያከናውናሉ። በክረምቱ የዝውውር መስኮት ለየቅል ጊዜያትን በማሳለፍ በቅደም ተከተል ያለውን የቡድን ግንባታ ማስቀጠል እና አዲስ ቡድን መገንባት ላይ ተጠምደው ያሳለፉት ድቻ እና ቡና ዘንድሮም የላይኛው የደረጃ ሰንጠረዥ ፉክክር ላይ ለመገኘት እርምጃቸውን ነገ አንድ ብለው ይጀምራሉ።

ከቅዱስ ጊዮርጊስ በመቀጠል አነስተኛ አዳዲስ ተጫዋቾችን ያስፈረሙት ወላይታ ድቻዎች በነገው ጨዋታ የመስመር አጥቂያቸውን ቢኒያም ፍቅሬ ግልጋሎት በጉዳት ምክንያት አያገኙም። በክረምቱ ከፈረሙ አራት ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ሚካኤል ሳርፖንግም በተመሳሳይ በጉዳት በነገው ጨዋታ የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ እንደሆነ ተጠቁሟል።

ያለፉትን ሦስት ዓመታት ከመሩዋቸው አሠልጣኝ ካሣዬ አራጌ ጋር ተለያይተው አሠልጣኝ ተመስገን ዳናን በመንበሩ በመሾም ከ12 በላይ አዳዲስ ተጫዋቾችን ያስፈረሙት ኢትዮጵያ ቡናዎች ደግሞ ከብዙ መጠበቅ ጋር የሚያደርጉትን የነገ ጨዋታ ያለምንም ጉዳት እና ቅጣት በሙሉ ስብስቡ የሚከውን ይሆናል።

ይህንን ጨዋታ በዋና አልቢትርነት በላይ ታደሰ በረዳትነት እሱባለው መብራቱ እና ሻረው ጌታቸው እንዲሁም በአራተኛ ዳኛነት ሀይለየሱስ ባዘዘው የሚመሩት ይሆናል።

እርስ በርስ ግንኙነት

– በ16 ጊዜ የክለቦቹ የቀደመ ግንኙነት 7 የአቻ ውጤቶች ከፍተኛውን ድርሻ ይዘዋል። ወላይታ ድቻ አምስቱን ሲረታ ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ አራቱን አሸንፏል። በእነዚህ 15 ጨዋታዎች አጠቃላይ ከተቆጠሩት 26 ጎሎች ሲቆጠሩ ቡድኖቹም እኩል 13 13 ግብ በስማቸው አስመዝግበዋል።

ወላይታ ድቻን በተመለከተ ያዘጋጀነውን የውድድር ዘመን ዳሰሳ ለማንበብ ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ :

የክለቦች የውድድር ዘመን ቅድመ ዳሰሳ | ወላይታ ድቻ

ኢትዮጵያ ቡናን በተመለከተ ያዘጋጀነውን የውድድር ዘመን ዳሰሳ ለማንበብ ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ :

የክለቦች የውድድር ዘመን ቅድመ ዳሰሳ | ኢትዮጵያ ቡና

ሀዋሳ ከተማ ከ ለገጣፎ ለገዳዲ

የሳምንቱ መጨረሻ የማሳረጊያ ፍልሚያ ደግሞ የሊጉን ዋንጫ ሁለት ጊዜ ባነሳው ሀዋሳ ከተማ እና በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገሪቱ ከፍተኛ የሊግ እርከን በሚሳተፈው ለገጣፎ ለገዳዲ መካከል ይከወናል።

በ2014 የውድድር ዘመን አራተኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁት ሀዋሳ ከተማዎች በተከላካይ እና በአጥቂ ቦታ ላይ ወሳኝ ተጫዋቾችን ያጡ ቢመስሉም ክፍተታቸውን በአዳዲስ 8 ተጫዋቾች በመድፈን ዓመቱን በአንፃራዊነት ቀለል ባለ መርሐ-ግብር ለመጀመር ተሰናድተዋል። ቡድኑም በነገው ጨዋታ አብዱልባሲጥ ከማልን ብቻ ከዓምና በዞረ ቅጣት ምክንያት ካለመጠቀሙ ውጪ የሚያጣው ተጫዋች እንደሌለ ተሰምቷል።

ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊግ ያደገው አዲሱ ክለብ በነገው ዕለት ታሪካዊውን ጨዋታ ያከናውናል። አሳዳጊ አሠልጣኙ ጥላሁን ተሾመን በመንበሩ ያስቀጠለው ክለቡም በዝውውሩ ከ10 በላይ ተጫዋቾችን በማስፈረም አዲሱን ፈተና ለመጋፈጥ እየተሰናዳ ይገኛል። በቡድኑ ውስጥ ያለውን የቅጣት እና ጉዳት ዜና ለማጣራት ያደረግነው ጥረት ሊሳካ ባለመቻሉ ማቅረብ አልቻልንም።

10 ሰዓት ላይ የሚደረገውን መርሐ-ግብር ተካልኝ ለማ በዋና ዳኝነት ከረዳቶቹ ሙስጠፋ መኪ እና
ሰለሞን ተስፋዬ እንዲሁም አራተኛ ዳኛው ማኑሄ ወልደፃዲቅ ጋር ይመሩታል።

ሀዋሳ ከተማን በተመለከተ ያዘጋጀነውን የውድድር ዘመን ዳሰሳ ለማንበብ ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ :

የክለቦች የውድድር ዘመን ዳሰሳ | ሀዋሳ ከተማ

ለገጣፎን በተመለከተ ያዘጋጀነውን የውድድር ዘመን ዳሰሳ ለማንበብ ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ :

የክለቦች የውድድር ዘመን ቅድመ ዳሰሳ | ለገጣፎ ለገዳዲ

ያጋሩ