የክለቦች የውድድር ዘመን ቅድመ ዳሰሳ | ሀዲያ ሆሳዕና

ነብሮቹ በስብስባቸው ላይ ለውጦችን በማድረግ በአዲሱ የውድድር ዘመን ወጥ አቋም ለማሳየት ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል ፤ እኛም በተከታዩ ፅሁፋችን የቡድኑን ዝግጅት ዳሰናል።

በ2014 የውድድር ዘመን እጅግ የተቀዛቀዘ አጀማመርን በማድረግ ከመጀመሪያዎቹ ስድስት ጨዋታዎች ሦስት ነጥቦችን ብቻ አግኝተው የነበሩት ነብሮቹ ከዚህ አስከፊ አጀማመር መልስ ምንም እንኳን በወጥነት ውጤቶችን ለማስመዝገብ ቢቸገሩም ዓመቱን ከወራጅ ቀጠና በጥቂቱ ከፍ ብለው በ37 ነጥቦች 10ኛ ደረጃን ይዘው በማጠናቀቅ በፕሪሚየር ሊጉ ለሦስተኛ ተከታታይ የውድድር ዘመን ተካፋይ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

በአዲሱ የውድድር ዘመን የቀድሞ ምክትል አሰልጣኞቻቸውን ወደ ዋና አሰልጣኝነት ካሳደጉ ሦስት ቡድኖች አንደኛው የሆኑት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ዓምና ቡድኑን የመራው አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት በክረምቱ ያቀረበውን የልቀቁኝ ጥያቄ ተከትሎ በአሰልጣኙ ስር ረዳት በመሆን ያገለገሉትን አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹን ለመጪዎቹ ዓመታት በዋና አሰልጣኝነት የሾሙ ቢሆንም ለጊዜውም ቢሆን ከቀድሞው አሰልጣኛቸው ሙሉጌታ ምህረት ጋር ከውል ማፍረስ ጋር በተያያዘ መግባባት ላይ አለመድረሳቸውን ተከትሎ ጉዳዩ በፌደሬሽኑ የዲሲፕልን ኮሜቴ ውሳኔ እስኪያገኝ ድረስ አሰልጣኝ ያሬድ የመጀመሪያዎቹን ጨዋታዎች ቡድኑን በምክትል አሰልጣኝነት ማዕረግ የሚመሩ ይሆናል። በተጨማሪነትም ቅዱስ ዘሪሁን በምክትል አሰልጣኝነት የአሰልጣኝ ቡድኑ አባል ሆኗል።

ከአሰልጣኝ ለውጥ ባለፈ በክረምቱ ቡድኑ ቀሪ የአንድ ዓመት ውል ከነበራቸው አስር ባለ ልምድ ተጫዋቾች ጋር ለመለያየት የመወሰኑ ጉዳይ ትኩረት የሚስብ ነበር። በ2014 የውድድር ዘመን ቡድን በወጥነት ሲያገለግሉ የነበሩት እንደነ ተስፋዬ አለባቸው ፣ ሀብታሙ ታደሰ እና ኤፍሬም ዘካርያስ ያሉ ባለልምድ ተጫዋቾችን የለለቀው ሆሳዕና በዝውውር መስኮቱ እነዚህን ወሳኝ ተጫዋቾችን በመተካት ግዴታ ውስጥ ሆነው የጀመሩት ነበር።

በተለያዩ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ተወጥሮ የነበረው ክለቡ ወደ ዝውውር ገበያው የገባው ዘግይቶ ነበር። ሀዲያ ሆሳዕናዎች በሙከራ ዕድል የጨመሯቸውን ሦስት ተጫዋቾችን ጨምሮ በድምሩ አስራ አንድ አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ በስብስባቸው አካተዋል። አይቮሪኮስታዊው ፔፕ ሰይዱ ኒዲያዬ ስብስቡን በግብ ጠባቂነት የተቀላቀለ ሲሆን ተከላካይ መስመራቸው ላይ ደግሞ ዳግም ንጎሴ ብቸኛው ፈራሚ ነው። ከዚህ ባለፈም ቡድኑ በአማካይ እና አጥቂ ክፍሉ ላይ በርከት ያሉ አዳዲስ ፊቶችን አካቷል። አማካይ ስፍራ ላይ ቤዛ መድህን ፣ አክሊሉ ዋለልኝ ፣ ሰመረ ሀፍትተይ ፣ ስቴፈን ናያርኮ ፣ ብሩክ ማርቆስ እና መለሰ ሚሻሞን ሲያስፈርሙ የፊት መስመራቸው ላይ ደግሞ እንዳለ ደባልቄ ፣ ዘካሪያስ ፍቅሬ እና ሪችሞንድ ኦዶንጎን ነብሮቹን ተቀላቅለዋል። ከዚህ በተጨማሪ አምና በቡድኑ ውጥ ተካተው የነበሩ ወጣት ተጫዋቾችም ዘንድሮ ከፍ ባለ ኃላፊነት የመጫወት ዕድል እንዳላቸው ይገመታል።

ከ2013 ጋር ሲነፃፀር 2014 ላይ ሆሳዕና እንደ ቡድን በመከላከሉ ረገድ የአደረጃጀት ሆነ ከፍተኛ ግለሰባዊ ስህተቶች መገለጫዎቹ ነበሩ ማለት ይቻላል። በተለይም አብዝቶ ስህተቶችን በመፈፀም ቡድኑን ዋጋ ሲያስከፍል በነበረው ሶሆሆ ሜንሳ ምትክ ግብ ጠባቂ ስፍራ ላይ የተሻለ አቅም እንዳለው የታመነው ፔፕ ሰይዱ መምጣት ቡድኑን ያሻሽላል ተብሎ ሲጠበቅ ባለፉት ዓመታት በወልቂጤ ከተማ ጥሩ ብቃቱን ያሳየው ዳግም ንጎሴም ለተከላካይ መስመሩ ጥሩ አቅም እንደሚጨምር ይታመናል።

ሌላው የአምናው ስብስብ ችግር የነበረው ዕድሎችን ወደ ግብነት መቀየር እንደነበረ አይዘነጋም። ደካማ በነበረው የአጥቂ መስመር ውስጥ ባሳለፍነው የውድድር ዘመን ስምንት ግቦች በማስቆጠር የቡድኑ ከፍተኛ ግብ አሰቆጣሪ የነበረውን ሀብታሙ ታደሰን ላጡት ሀዲያዎች አምና ከሊጉ በተሰናበቱት አዲስ አበባ ከተማዎች መለያ 14 ግቦችን በማስቆጠር በሊጉ ለከፍተኛ አስቆጣሪነት ሲፎካከር በነበረው ጋናዊው ሪችሞንድ አዶንጎ መተካት መቻላቸው በትልቁ የሚነሳው ዝውውር ነው።

እርግጥ ሪችሞንድ አዶንጎ ባለፈው የውድድር ዘመን ዕድሎችን ወደ ግብነት በመቀየር ረገድ የተሻለ ዓመት ማሳለፉ ባይካድም ሌሎቹ አብረውት ወደ ቡድኑ የተቀላቀሉት አጥቂዎች ግን ጥሩ አቅም እንዳላቸው ቢታመንም በትልቅ ደረጃ ራሳቸውን ያስመሰከሩ ጨራሽ አጥቂዎች ያለመሆናቸው ነገር ግን አሳሳቢ ይመስላል።

የክለቡ አጠቃላይ የክረምቱ የዝውውር እንቅስቃሴ በአሰልጣኙ ዕምነት ከሞላ ጎደል ጥሩ ስለ መሆኑ ይናገራሉ “ወደ ዝውውር መስኮቱ ዘግይተን ነው የገባነው። ቢሆንም በሊጉ ላይ አሉ የተባሉ ተጫዋቾችን ባናገኝም መካከለኛ የሆኑ በሊጉ የመጫወት ልምድ ያላቸውን እና በዚህ ክለብ ልክ ሊጫወቱ የሚችሉ ተጫዋቾች ማዘዋወር ችለናል ፤ ከሞላ ጎደል ጥሩ ነው።” ሲሉ ገልፀውታል።

ከዚህ ባለፈ ቡድናቸው ወደ ዝውውር ገበያው ዘግየት ብሎ መግባቱ ስለሚፈጥረው ተፅዕኖም እንዲሁ የሚሉት አላቸው ፤ “ተፅዕኖ ሊኖረው ይችላል። በምልመላ ላይ የምትፈልጋቸውን ተጫዋቾች ላታገኝ ትችላለህ። ነገር ግን ወደ ስራ ዘግይተን እንደመግባታችን የተወሰኑ ያጣናቸው ነገሮች አሉ ፤ በሊጉ አሉ የተባሉ ተጫዋቾችን መያዝ ባንችልም ያመጣናቸው ተጫዋቾች የሚተናነሱ ስላልሆኑ ብዙ የጎላ ችግር ይፈጥራል የሚል ዕምነት ግን የለኝም።” ይላሉ አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ።

ከነሀሴ 8 አንስቶ በክለቡ መቀመጫ በሆነችው ሆሳዕና ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን ሲያደርጉ የቆዩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ከ24 ቀናት ቆይታ በኋላ በሀዋሳ ሊደረግ ታቅዶ በነበረው የሲዳማ ደቡብ ጎፈሬ ዋንጫ ላይ ለመካፈል በማለም ወደ ሀዋሳ ቢያቀኑም ውድድሩ ሳይካሄድ መቅረቱን ተከትሎ ቀሪ ዝግጅታቸውን በሀዋሳ ከተማ ከማድረግ ባለፈ አራት የወዳጅነት ጨዋታዎችን ከከፍተኛ ሊግ ተካፋይ ከሆኑት ደቡብ ፖሊስ እና ሻሸመኔ ከተማ እንዲሁም በሀዋሳ ከተማ ተሰባስበው ከሚሰሩ ወጣቶች ጋር አድርገዋል። ምንም እንኳን የጨዋታዎቹ የጥራት ደረጃ ጥያቄ ቢነሳበትም አጋጣሚውን በተሻለ መጠን ቡድናቸውን ለመገምገም እንደተጠቀሙበት አሰልጣኙ ያነሳሉ።

በሁለት ከተማዎች ቡድኑ በነበረው የዝግጅት ወቅት ዓመቱን ሙሉ ለመጓዝ የሚያስችሉ ስራዎች ስለመሰራታቸው አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ ይናገራሉ ፤ “በሁሉም መስክ ነው የሰራነው ፤ ምክንያቱም ዓመቱን ሙሉ ሊያጫውት የሚችል ነገር ስለሆነ መሥራት የሚጠበቅብን በዛ ልክ በአካል ብቃት ፣ በቴክኒክ ፣ በታክቲክ ፣ በሥነልቦና በተጫዋቾቻችን ላይ ሁሉን ነገር ያካተተ ሥራ ሠርተናል።” ይላሉ።

በአዲሱ የውድድር ዘመን በአሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ የሚመራው ስብስብ በዋነኝነት ለሁሉም ጨዋታዎች ዕኩል ትኩረት በመስጠት ነጥቦችን ለመያዝ መጫወት ይኖርባቸዋል። የአምናው ስብስብ በዋነኝነት የሚቀርብበት ወቀሳ ከሰንጠረዡ አጋማሽ በላይ የሚገኙ ተጋጣሚዎችን ሲገጥም በተለየ አቀራረብ እና በተለየ ታታሪነት የሚጫወት በአንፃሩ ደግሞ ከአጋማሽ በታች የሚገኙ ቡድኖችን ሲገጥም ደግሞ ፍፁም በተቃራኒው በቀላሉ የሚከፋፈት ቡድን ሲሆን አስተውለናል። በመሆኑም ቡድኑ አምና በሰንጠረዡ ይዞት ካጠናቀቀው ስፍራ በተሻለ መፈፀም የሚያልም ከሆነ ስለወጥነት አብዝቶ መጨነቅ መጀመር ይኖርበታል።

ሌላኛው ሀዲያ ሆሳዕና ወደ አዲሱ የውድድር ዘመን ሲመጣ መፍትሄ ሊያበጅለት የሚገባው የቡድኑ የመከላከል አወቃቀር ጉዳይ ላይ ነው። በሊጉ 40 ግቦችን አስተናግዶ ያጠናቀቀው ቡድኑ ከወረዱት ሦስት ቡድኖች ቀጥሎ በሊጉ ያስተዋልነው እጅግ ደካማ ቁጥር መሆኑ በአዲሱ የውድድር ዘመን ይህን በችግሮች የታጠረውን መዋቅር መፍትሄ ማበጀት ሌላው የትኩረት አቅጣጫ መሆን ይገባዋል።

በ2014 የውድድር ዘመን የቡድኑን የቀኝ መስመር ማጥቃት ከኋላ እየተነሳ ይዘውር የነበረው የመስመር ተመላላሹ ብርሃኑ በቀለ ዘንድሮም ይደምቃል ተብሎ ሲጠበቅ ከእሱ በተጨማሪም በተከላካይ መስመር በትልቅ ደረጃ የመጫወት አቅም እንዳለው ፍንጭ የሰጠው ወጣቱ ቃለዓብ ውብሸት እንዲሁም ባለፈው የውድድር ዘመን በወረደው አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በግሉ እጅግ ምርጥ ጊዜን ማሳለፍ የቻለው ጋናዊው የፊት አጥቂ ሪችሞንድ አዶንጎም እንዲሁ የአምናው ብቃቱን ይደግም ዘንድ የነብሮቹ ደጋፊዎች ብዙ ይጠብቁበታል።

ሀዲያ ሆሳዕናዎች በመጪው ሰኞ መስከረም 23 መቻልን በመግጠም የሊግ መርሃግብራቸውን የሚከፍቱ ይሆናል

የሀዲያ ሆሳዕና የ2015 ስብስብ ዝርዝር

ግብ ጠባቂዎች

1 ፔፕ ሰይዱ
30 መሳይ አያኖ
22 ያሬድ በቀለ

ተከላካዮች

5 ቃለአብ ውበሸት
12 ብርሃኑ በቀለ
13 ካሌብ በየነ
14 እያሱ ታምሩ
15 እሸቱ ግርማ
17 ሄኖክ አርፊጮ
16 ፍሬዘር ካሳ
21 ግርማ በቀለ
19 ዳግም ንጉሴ
20 ምንተስኖት አካሉ

አማካዮች

2 ብሩክ ማርቆስ
3 እክሊሉ ዋለልኝ
4 ፀጋዬ ብርሃኑ
6 መለሰ ሚሻሞ
8 ሳምሶን ጥላሁን
7 ሠመረ ሃፍታይ
10 ፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን
18 እንዳለ አባይነህ
23 ቅዱስ ዮሀንስ
26 ክብርዓብ ያሬድ
28 ቤዛ መድህን
31 ስቲፈን ናርኮን

አጥቂዎች

9 ባዬ ገዛኸኝ
24 ተመስገን ብርሃኑ
25 ዋቸሞ ጳውሎስ
27 ደስታ ዋሚሾ
29 ሪችሞንድ አዶንጎ
32 ነጋሽ ታደሰ
33 እንዳለ ደባልቄ
39 ራምኬል ሎክ
41 ዘካርያስ ፍቅሬ

የአሰልጣኝ ቡድን አባላት

ዋና አሰልጣኝ – ያሬድ ገመቹ
ረዳት አሰልጣኝ – ቅዱስ ዘሪሁን
ቡድን መሪ – ታደሰ ሰይፈ
የህክምና ባለሙያ – መሳይ ጥበቡ