የክለቦች የውድድር ዘመን ዳሰሳ | ፋሲል ከነማ

ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ብቅ ብሎ በአጭር ጊዜ ተፎካካሪ የሆነው ፋሲል ከነማ ዘንድሮም ዋንጫ ማንሳትን እያለመ የሚጀምረውን የውድድር ዓመት እንደሚከተለው ቃኝተነዋል።

ጎንደር ከተማ ላይ መቀመጫውን ያደረገው ፋሲል ከነማ ዘንድሮ 55ኛ የምስረታ በዓሉን እያከበረ ይገኛል። ይህ በዓል ደግሞ አይረሴ ሆኖ በደማቁ እንዲከበር የሊጉን ዋንጫ ማንሳት አማራጭ የሌለው ትልም ይመስላል። እርግጥ ቡድኑ 2009 ላይ ወደ ሀገሪቱ ከፍተኛ የሊግ እርከን ካደገ በኋላ ራሱን በሊጉ እያደላደለ ቆይቶ ያለፉትን አራት ዓመታት ኮስታራ የዋንጫ ተፎካካሪ ቡድን ሆኗል። 2013 ላይም በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የሊጉን ዋንጫ 4 የጨዋታ ሳምንታት እየቀሩት ከፍ ማድረግ ችሏል።

በ2014 የውድድር ዓመት የዋንጫ ማግስት የሚከሰተው ‘ሀንጎቨር’ ያገኘው ፋሲል ከነማ በመጀመሪያው ዙር የሊጉ ውድድር መጠነኛ መንገራገጭ አጋጥሞት ነበር። ሊጉን ተከታታይ ሦስት ጨዋታዎችን በድምሩ ስምንት ግቦችን በማስቆጥር የጀመረው ክለቡም በመቀጠል ተከታታይ ሦስት ጨዋታዎችን ከድል ጋር መገናኘት ሳይችል ጫና ውስጥ ወድቋል። በተለይ በተለይ ደግሞ በቀጥተኛ የዋንጫ ተፎካካሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ10ኛ ሳምንት የደረሰበት የ4ለ0 ሽንፈት ከፍተኛ ምስቅልቅል እንዳመጣ ይታመናል። ከዛ ጨዋታ በኋላም በተደረጉ ሰባት ጨዋታዎች ሁለቱን ብቻ ያሸነፈ ሲሆን የገጠመውን የውጤት ድባቴም በቶሎ መላቀቅ ሳይችል ቀርቷል። በዚህም ካቻምና ዋንጫ ያስገኘውን አሠልጣኝ ሥዩም ከበደ ከ17 የጨዋታ ሳምንት በላይ ዕድል ሳይሰጥ በምክትል አሠልጣኙ ኃይሉ ነጋሽ እየተመራ ውድድሩን ለመፈፀም ውሳኔ አስተላልፏል። ባለ አደራው አሠልጣኝም ቡድኑን በመሩባቸው የመጨረሻ 13 የጨዋታ ሳምንታት አንድ ሽንፈት ብቻ በማስተናገድ ተረስቶ የነበረውን የዋንጫ ፉክክር ዳግም ቆስቁሰውታል። እስከ መጨረሻኛው የጨዋታ ሳምንትም የሊጉን መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር በእግር እየተከተሉ ዋንጫውን ለማግኘት ቢጥሩም በአራት ነጥቦች ተበልጠው በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች የተፋፋመው ውጥናቸው ሳይሰምር ቀርቷል።

ዓምና በአጠቃላይ 18 ጨዋታዎችን አሸንፎ በ7ቱ አቻ በመውጣት በተቀሩት 5ቱ ተረቶ 61 ነጥቦችን በመያዝ ሀገራችን ኢትዮጵያን በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ የመወከል ዕድል ያገኘው ፋሲል ከነማ ከአብዛኞቹ ክለቦች (ቅዱስ ጊዮርጊስ አያካትትም) ቀድሞ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ጀምሯል። በጠቀስናቸው 13 ጨዋታዎች ክለቡን ርቆት ወደነበረው ወጥ ውጤት የወሰዱት አሠልጣኝ ኃይሉ ነጋሽ በዋና አሠልጣኝነት ሚና ውላቸውን እንዲያራዝሙ ተደርጎ ከረዳታቸው ሙሉቀን አቦሀይ እና ግብ ጠባቂዎች አሠልጣኙ አዳም ባዘዘው በተጨማሪ የቀድሞውን የአሠልጣኝ ቡድን አባል ምንተስኖት ጌጡን የአካል ብቃት አሠልጣኝ በማድረግ የአለቆቹን ስብስቡ ለማደራጀት ጥሯል።

ክለቡ የአሠልጣኝ ቡድኑን ቢያስቀጥልም በተጫዋች ረገድ ግን ብዙም ስኬታማ የሆነ አይመስልም። በዚህም ባለፉት ሦስት እና አራት ዓመታት በቡድኑ ጥንካሬ የአንበሳውን ድርሻ ከሚይዙ ተጫዋቾች መካከልም ያሬድ ባየ፣ በረከት ደስታ፣ ሙጂብ ቃሲም እና ሰዒድ ሀሰንን ማቆየት ሳይችል ቀርቶ በሌሎች ክለቦች ተቀምቷል። በተለይ በሁለቱ ወሳኝ የፍፁም ቅጣት ምት ክልሎች የጥንካሬው ምሰሶ የነበሩት ያሬድ እና ሙጂብ አለመቀጠላቸው ብዙ ደጋፊዎችን አስከፍቷል። ከፊት ሙጂብ ብቻ ሳይሆን ዓምና የቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የነበረው ኦኪኪ አፎላቢ እና ሦስተኛው የግብ ምንጭ በረከት ደስታም አለመኖራቸው የማጥቃት ኃይሉን የሚያዳክም ይመስላል። በዋናነት በፋሲል ከነማ ያለፉት ዓመታት የስኬት ሚስጢር ተደርጎ በብዙዎች የሚወሰደው የተረጋጋ የቡድን ግንባታም ዘንድሮ በመጠኑ መንገራገጩ እና መውጣትና መግባታ ማብዛቱ ወደአለመደው አዲስ የግንባታ ሂደት እንዲገባ ያስገድደዋል የሚል እምነት በብዙዎች ዘንድ አለ።

እርግጥ በሀገራችን የክለቦች ቁመና በየዓመቱ አዳዲስ የቡድን ግንባታዎች የተለመዱ ቢሆንም ፋሲል ግን ከ2010 በኋላ ከዚህ በተቃራኒ ሲኋዝ ነበር። ምናልባታም ይህን አዲስ ባህሪ ክለቡ እስኪለምድ እና የወጡትን ወሳኝ ተጫዋቾች በአስተማማኝ መልሉ በመተካት ተፈላጊውን ውህደት እስኪያገኝ መጠነኛ ችግር እንዳያጋጥመው ያሰጋል። ክረምት ላይ ከጊዜያዊነት ወደ ዋና አሠልጣኝነት የተሸጋገሩት ኃይሉ ነጋሽም ከዝውውር ሂደቱ ጋር ተያይዞ ያሉ ሀሳቦችን እንደሚከተለው ያስረዱናል። “የዝውውሩ ሂደት ለእኛ በጣም አስቸጋሪ ነበር። ምክንያቱም ሙሉ ቡድኑ ውል የጨረሰ ስለነበር ሁለት የቤት ሥራ ነበር የገጠመን ፤ አንደኛው አዲስ ተጫዋቾችን ማስፈረም ሁለተኛው ደግሞ የነበሩትን ማቆየት ፤ ይህ በጣም ትልቅ ፈተና ነበር። የሆነው ሆኖ መቆየት የነበረባቸው ተጫዋቾች ለቀዋል ግን እነሱን የሚተኩ ተጫዋቾች ደግሞ አምጥተናል።” እያሉ ሀሳባቸውን እየሰጡ የወጡትን ወሳኝ ተጫዋቾች ለመተቃት በተቀዳሚ ምርጫቸው (Plane A) ሳይሆን በሁለተኛ ምርጫቸው ተጫዋቾችን እንዳገኙ ይጠቁማሉ።

አሠልጣኙ እንዳሉት በሁለተኛ እቅዳቸው ተጫዋቾችን አስፈርመው የወጡትን ቢተኩም ያለባቸውን ክፍተት ሸፍነው ወደ ዝግጅት እንደገቡ እና ከዓምናው የተሻለ ቡድን እንደሚኖራቸው ይገልፃሉ። “ወሳኝ ተጫዋቾች የምንላቸው ብናጣም እኛ የእነርሱን ክፍተት ለመድፈን ሞክረናል ፤ ግን ዋናው 90% ዓምና የነበረውን ቡድን ነው ያስቀጠልነው። ለእኛ ክለብ ትልቁ ነገር እርሱ ነው። የመጡትም ትንሽ ባሉን ክፍተቶች ላይ የሚሞሉ ስለሆኑ ከ2014 የተሻለ ቡድን ይኖረናል ብዬ አስባለሁ።”

በዝውውር መስኮቱ ኦኪኪ አፎላቢ፣ በረከት ደስታ፣ ሙጂብ ቃሲም፣ ያሬድ ባየ፣ ሰዒድ ሀሰን፣ ቴዎድሮስ ጌትነት እና ሳሙኤል ዮሐንስን ያጣው ክለቡ በተቃራኒው መናፍ ዐወል፣ ታፈሰ ሠለሞን፣ ተስፋዬ ነጋሽ፣ ሀብታሙ ገዛኸኝ፣ ወንድማገኝ ማርቆስ፣ ጋይራ ጁፍ እና ኪሩቤል ደሳለኝን ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል። በአዲስ መልክ የመጡት ተጫዋቾች በአብዛኛው ተቀዳሚ ምርጫ ባይሆኑም ክለቡን ያጠናክራሉ ተብለው የታሰቡ እንደሆነ ተጠቅሷል። ይህ ቢሆንም ግን አዲሶቹን ከነባሮቹ ጋር ለማዋሀድ ጊዜ እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ። “የመጡት ተጫዋቾች ምን ያህል ተዋህደዋል የሚለው በጣም ጊዜ ይፈልጋል። ተደጋጋሚ ጨዋታዎችን ሲያገኙ ነው ከቡድኑ ጋር የሚግባቡት። ዞሮ ዞሮ ግን የተወሰኑ ተጫዋቾች ከቡድኑ ቅኝት ጋር ወዲያው ለመግባባት ሞክረዋል። ግን የመጡት ተጫዋቾች ይጠቅሙናል ብዬ ነው የማስበው ፤ በደንብ ሲዋሃዱ ደግሞ ክለባችን ጠንካራ ይሆናል ብዬ አስባለሁ።”

በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት 2ኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቁ ሀገራችንን በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ የመወከል ክብር ያገኘው ፋሲል ከቅዱስ ጊዮርጊስ በመቀጠል የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ቀድሞ የጀመረ የሊጉ ሁለተኛው ክለብ ነው። በዚህም ነሐሴ 2 መቀመጫውን ባህር ዳር ከተማ በማድረግ ነባር እና አዳዲስ ተጫዋቾችን በማካተት መደበኛ ልምምዱን ጀምሯል። ለውድድር ዓመቱ ስንቅ የሚሆኑ ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርገው የሰሩት ፋሲል ከነማዎች ለአህጉራዊው ውድድር ትኩረት ሰጥተው በሚሰናዱበት ሰዓት ምንም እንኳን ከፈታኝ ቡድኖች ጋር ባይሆንም የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችንም አድርገዋል። “የውጪ ውድድር ስለነበረን ዝግጅታችንን ነሐሴ 2 ነው የጀመርነው። ጠንከር ያለ ቡድን ባናገኝም ባሕርዳር ከሚገኙ ቡድኖች ጋር የወዳጅነት ጨዋታዎች ለመጫወት ሞክረናል። ከዛ በኋላ ወደ ዋናው ጨዋታው ነው የገባን። ከቡሩንዲው ቡድን (ቡማሙሩ) ጋር ሜዳችን ላይ ተጫውተን በሳምንቱ ደግሞ የመልሱን ጨዋታ አከናውነን በአጠቃላይ ውጤት ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ችለናል። ከዛ ከመጣን በኋላ ትኩረታችንን ሊጉ ላይ አድርገም ስንለማመድ ቆይተናል። በአጠቃላይ ቡድናችን ጥሩ ስብስብ ነው ያለው ፤ ጥሩ ሥራ ለመሥራት ሞክረናል። በጂም እና ሜዳ ላይም ያንን ሠርተን ለውድድሩ ለመቅረብ ተሰናድተናል።”

ቀድመው ወደ ዝግጅት መግባታቸውን እንደ ጥሩ ነገር የሚያነሱት አሠልጣኙ የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን አለማግኘታቸው ግን ወቅታዊ ጠንካራ እና ደካማ ጎናቸውን እንዳይለዩ እንዳደረጋቸው ይጠቁማሉ። “ዝግጅት ቀድመን መጀመራችን ጠቀሜታ አለው። ግን ደግሞ ብዙ ልምምድ ከመሥራት የወዳጅነት ጨዋታዎች አድርገህ አቋምህን መፈተሽ ይገባ ነበር። ግን እኛ ብዙ የወዳጅነት ጨዋታዎችን አላደረግንም። ቀድመን በመጀመራችን ግን ለውድድሩ ጥሩ ነገር አግኝተናል ብዬ አስባለሁ።” ብለዋል። እርግጥ ከሊጉ በፊት ከቡሩንዲው ክለብ ቡማሙሩ ጋር ያደረጓቸው ሁለት የደርሶ መልስ ጨዋታዎች እና ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ በሜዳቸው 55ኛ ዓመት የምስረታ በዓላቸውን የሚያወድስ ጨዋታ ከዩጋንዳው ክለብ ሞደርን ጋዳፊ ጋር ማድረጋቸው ከዋናው የሊግ ድግስ በፊት ያላቸውን አቋም እንዲያውቁ የሚያደርግ ይመስላል።

እንደ ፋሲል ከነማ ካሉ ቡድኖች እንከኖችን መፈለግ ቢቸግርም ዓምና ግን በተለይ በመጀመሪያው ዙር የነበረበትን የወጥነት ችግር እንደ ሁለተኛው ዙር ዘንድሮም ማስተካከል አለበት። ስብስቡ ከመጀመሪያዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ውጪ እስከ 17ኛ ሳምንት ድረስ አንድም ጊዜ ተከታታይ ድል ሳያስመዘግብ ተጉዞ የነበረ ሲሆን ይህ የወጥነት ችግርም ለዘንድሮ በተናጥል በተጫዋቾች ብቃትም ሆነ በቡድናዊ መዋቅር መቀረፍ ይገባዋል። ከሁሉም በላይ ግን አሠልጣኝ ኃይሉ የዋና አሠልጣኝነትን መንበር ከያዙ በኋላ የተስተካከለውን የማሸነፍ ሥነ-ልቦናው ክፍተት ዘንድሮ መደገም ስለሌለበት ተጫዋቾቹን ለሌላ የዋንጫ ረሀብ ማነሳሳት ቁልፉ የቤት ሥራ ነው። የሊጉን የመጀመሪያ አምስት ጨዋታዎች ደግሞ በርካታ ደጋፊዎቻቸው ባሉበት ባህር ዳር ማድረጋቸው የውድድር ዓመቱን በአውንታዊ መንገድ እንዲጀምሩ ያደርጋል ተብሎ ይታሰባል።

ፋሲሎች በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ወደ ሁለተኛ ዙር ማጣሪያ በማለፋቸው ትኩረታቸው በሁለት ውድድሮች እንዳይወጠር ቢታሰብም አሠልጣኝ ኃይሉ ግን ሁለቱንም ውድድር በጥሩ ሁኔታ ለመከወን እየተዘጋጁ እንደሆነ ይናገራሉ። “ከቡድኑ ጋር በምክትል አሠልጣኝነት እና ከዓምና ግማሽ ዓመት በኋላ ደግሞ በዋና አሠልጣኝነት አራት ዓመታት ቆይቻለሁ። እኔ ብቻ ሳልሆነ የአሠልጣኝ ቡድን አባላቱም ነባር ስለሆንን ቡድኑን በሚገባ እናውቀዋለን። ምን እንደሚያስፈልግ በደንብ ስለምናቅም ምንም አልከበደንም። ዓምና የሊጉን ዋንጫ ለጥቂት ነው ያጣነው ፤ ዘንድሮ ግን ብዙ አቅደን ነው የተነሳነው። የመጀመሪያው ዕቅዳችን በኮንፌዴሬሽን ካፕ የመጀመሪያውን ጨዋታ ማለፍ ነው። አሁን ደግሞ ሁለተኛውን አሸንፈን ለቀጣይ ምድብ ለመግባት ጥረት በማድረግ እየሠራን ነው ያለነው። ጎን ለጎን ደግሞ ለሊጉ የተሻለ ቡድን ይዘን ቀርበን ዓምና ያጣነውን የሊጉን ዋንጫ ዘንድሮ ለማግኘት ነው ጥረት የምናደርገው።” በንግግራቸው መካከል በተደጋጋሚ የተሻለ ስብስብ እንዳላቸው ሲገልፁ የሚሰሙት አሠልጣኙ ያለምንም ጥርጥር ዋንጫውን እንደሚያነሱ አስረግጠው በመናገር ሀሳብ መስጠታቸውን አገባደዋል።

በዐፄዎቹ ስብስብ ውስጥ ዘንድሮ ተፅዕኖ ይፈጥራሉ ተብለው የሚጠበቁ በርካታ ተጫዋቾች አሉ። ምንም እንኳን ቡድኑ የኋላ መስመሩ መሪ እና አምበል የሆነው ያሬድ ባየን ቢያጣም ወደ ጥሩ ብቃቱ እየተመለሰ በሚገኘው አስቻለው ታመነ ክፍተቱን በሚገባ እንደሚሸፍን በተደረጉት ጥቂት ጨዋታዎች ፍንጮች ታይተዋል። ተጫዋቹም ያለፉት ዓመታት የቡድኑ ግንባታ አካል ከሆነው ከድር ኩሊባሊ ጋር የሚያደርገው ጥምረት የሚጠበቅ ይሆናል። በአማካይ መስመር ላይም የይሁን እንዳሻው እና ሀብታሙ ተከስተ እንዲሁም የታፈሰ ሠለሞን፣ ሱራፌል ዳኛቸው እና በዛብህ መለዮ ፉክክር ለቡድኑ ትልቅ ግብዓት እንደሚሆን እሙን ነው። በተለይ በአንድ ቦታ ላይ ጥራት ያላቸው በርከት ያሉ ተጫዋቾች መኖራቸው ለቋሚነት የሚደረገው ፉክክር ከፍ ሲያደርገው ቡድኑም በዚህ የፉክክር ሂደት የሚጠቀም ይሆናል። ፊት መስመር ላይም በኦኪኪ እና ከግማሽ ዓመት በኋላ በመጣው በሙጂብ የመሰለፍ ዕድሉ ጠቦ የነበረው ፍቃዱ ዓለሙም አሁን ራሱን ማሳያ ጊዜ ያገኘ ይመስላል። በተለይ ጋምቢያዊው አጥቂ ጋይራ ጁፍ ቡድኑን፣ ሊጉን እና ሀገሩን እስኪላመድ ድረስ ፍቃዱ የሚያገኛቸውን አጋጣሚዎች ለመጠቀም እና ራሱን በተደጋጋሚ በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ለማግኘት የሚያደርገው ጥረት የቡድኑን ስልነት የሚጨምረው ይሆናል።

ፋሲል ከነማ የዘንድሮውን የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ጨዋታ ነገ 7 ሰዓት ከአዳማ ከተማ ጋር የሚያደርግ ይሆናል።

የ2015 የፋሲል ከነማ ሙሉ ስብስብ


ግብ ጠባቂዎች

1 ሚኬል ሳማኪ
16 ይድነቃቸው ኪዳኔ
22 ዮሐንስ ደርሶ

ተከላካዮች

21 አምሳሉ ጥላሁን
5 ከድር ኩሊባሊ
15 አስቻለው ታመነ
25 ዳንኤል ዘመዴ
2 መናፍ አወል
12 ተስፋዬ ነጋሽ
26 ወንድማገኝ ማርቆስ
32 ዳንኤል ፍፁም
3 ሔኖክ ይትባረክ

አማካዮች

14 ሀብታሙ ተከስተ
19 ሽመክት ጉግሣ
17 በዛብህ መለዩ
6  ኪሩቤል ኃይሉ
24 አቤል እያዩ
10 ሱራፌል ዳኛቸው
8 ይሁን እንዳሻው
7 ታፈሰ ሠለሞን
30 ኪሩቤል ደሳለኝ
33 ደጀን ገበየሁ
11 ሀብታሙ ገዛኸኝ

አጥቂዎች

27 ዓለምብርሃን ይግዛው
18 ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ
9 ፍቃዱ ዓለሙ
4 ጋይራ ጁፍ
28 ናትናኤል ማስረሻ
35 ፋሲል ማረው

የአሰልጣኞች ቡድን አባላት

ዋና አሠልጣኝ – ኃይሉ ነጋሽ
ምክትል አሰልጣኝ – ሙሉቀን አቡሃይ
የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ – አዳም ባዘዘው
የአካል ብቃት አሰልጣኝ – ምንተስኖት ጌጡ
ፊዚዮቴራፒስት – ሽመልስ ደሳለኝ
የቡድን መሪ – ሀብታሙ ዘዋለ

ያጋሩ