የዕለቱ የመጀመሪያ በነበረው መርሐ-ግብር ድቻ እና ኢትዮጵያ ቡና የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ያለ ግብ በአቻ ውጤት የተጠናቀቀውን ጨዋታ አስመልክተውናል።
ፍፁም በተለያየ መንገድ ጨዋታውን የጀመሩት ሁለቱ ቡድኖች ድቻዎች ከአምናው የመጀመሪያ ተመራጭ አስራ አንዳቸው ላይ የአንድ ተጫዋቾች ብቻ ለውጥ አድርገው ሲቀርቡ ኢትዮጵያ ቡናዎች ደግሞ ሰባት አዳዲስ ፈራሚዎቻቸውን በመጀመሪያ ተሰላፊነት ያስጀመሩበት ጨዋታ ነበር።
ቀዝቀዝ ያለ እንቅስቃሴ በተመለከትንበት የመጀመሪያው አጋማሽ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናዎች የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫን በመውሰድ ጨዋታውን በድቻ አጋማሽ ለማድረግ ጥረት ቢያደርጉም የቡድኑ ማጥቃት በጠበበ መልኩ መሀል ለመሀል በሚደረጉ ቅብብሎች የተገደበ መሆኑ ቡናዎች የድቻን የተደራጀ መከላከል አልፈው እድሎችን እንዳይፈጥሩ ተግዳሮት ፈጥሮባቸው ተመልክተናል።
በጨዋታው 16ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም ወርቁ ሳጥን ውስጥ ለቡድን አጋሮቹ ለማቀበል የሞከረውን ኳስ አንተነህ ጉግሳ በእጅ በመንካቱ ኢትዮጵያ ቡናዎች ፍፁም ቅጣት ምት ማግኘት ቢችሉም ብሩክ በየነ የመታው ኳስ ቢኒያም ገነቱ በጥሩ ሁኔታ ሊያድንበት ችሏል።
በአጋማሹ የመጨረሻዎቹ ደቂቃ መጠነኛ መሻሻሎችን ቢያሳዩም ድቻዎች በቁጥር በርከት ብለው በራሳቸው የሜዳ አጋማሽ ከመከላከል ባለፈ ኳስ በቁጥጥራቸው ስር ስትወድቅ መልሶ ማጥቃቶችን ለመሰንዘር የነበራቸው ዝግጁነት እጅግ ደካማ ነበር።
ኢትዮጵያ ቡናዎቹ በአጋማሹ በሁለት አጋጣሚዎች ብሩክ በየነ በቀጥታ ከሳጥን ውጭ በቀጥታ ካደረጋቸው ሙከራዎች ውጭ በ29ኛው ደቂቃ ሮቤል ተክለሚካኤል ከግቡ ትይዩ ከርቀት የመታው እና ቢኒያም ገነቱ ያዳናት የቆመ ኳስ አጋጣሚ ተጠቃሽ ነበረች።
ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር በተወሰነ መልኩ ነቃ ያለ አጀማመር በነበረው የሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በሁለቱም ቡድኖች በኩል መጠነኛ መነቃቃቶችን የተመለከትንበት ነበር።
በ49ኛው ደቂቃ በድቻዎች በኩል በሀይሉ ተሻገር ከተከላካይ ጀርባ እንዲሮጥ ያሳለፈለትን ኳስ ስንታየሁ መንግሦቱ ከራምኬል ጀምስ ጋር ታግሎ ያደረገውን ሙከራ በረከት አማረ ሲያድንበት ከደቂቃዎች በኋላ በ53ኛው ደቂቃ በቡናዎች በኩል መስፍን ታፈሰ ከቀኝ መስመር ወደ ሳጥን ለማሻማት አስቦ የላካት የምትመስለው ኳስ ሳትጠበቅ ቢኒያም ገነቱን መፈተን ችላለች።
በ66ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር በተነሳ የማጥቃት እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ ቡናዎች በግሩም አንድ ሁለት ቅብብል ወደ ሳጥን ውስጥ በመግባት የፈጠሩትን እድል መስፍን ታፈሰ ሳይጠቀምበት ቀረ እንጂ በጨዋታው የተመለከትነው እጅግ ያለቀለት አጋጣሚ ነበር።
ቀስ በቀስ ይበልጥ ተነቃቅቶ በቀጠለው ጨዋታ ድቻዎች ከመከላከል ባለፈ ይበልጥ በድፍረት ተደጋጋሚ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን መፍጠር የጀመሩ ሲሆን በአንፃሩ ኢትዮጵያ ቡናዎች ከመጀመሪያ አጋማሽ በተሻለ የመስመር ተከላካዮቻቸውን በማጥቃቱ ለመጠቀም ሲጥሩ አስተውለናል።
በሁለቱም ቡድኖች በኩል ወደ ማጥቂያው ሲሶ በመድረስ ረገድ የተሻለ ነገር ብንመለከትም በሁለቱም ቡድኖች በኩል የነበሩ ደካማ ውሳኔ አሰጣጦች ጨዋታው ያለ ግብ በአቻ ውጤት እንዲጠናቀቅ አስገድሏል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም አንድ የወዳጅነት ጨዋታ ብቻ አድርጎ እንደመጣ ቡድን የቅንጅት ችግሮች ቢኖርብንም ሊጉን ሳይሸነፉ በመጀመራቸው ደስተኛ ስለመሆናቸው ሲናገሩ በአንፃሩ አሰልጣኝ ተመስገን ዳና በሁለተኛው አጋማሽ የተሻሉ እንደነበሩ ጠቅሰው እንደ መጀመሪያ ጨዋታ ጥሩ ተንቀሳቅሰናል ብለው እንደሚያምኑ ገልፀዋል።