በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በሊጉ የተጫወተው ለገጣፎ ለገዳዲ ከመመራት ተነስቶ በካርሎስ ዳምጠው ሁለት ግቦች ታግዞ ሀዋሳ ከተማን አሸንፏል።
በአሠልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ የሚመሩት ሀዋሳ ከተማዎች በክረምቱ የዝውውር መስኮት ካስፈረሟቸው 8 ተጫዋቾች መካከል ሰዒድ ሀሰን፣ ሰለሞን ወዴሳ፣ አዲሱ አቱላ፣ ሙጂብ ቃሲም እና ዓሊ ሱሌይማንን በመጀመሪያ አሰላለፍ አስገብተው ጨዋታውን ጀምረዋል። በተቃራኒው በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሊጉ ያደጉት ለገጣፎ ለገዳዲዎች በአሳዳጊ አሠልጣኛቸው ጥላሁን ተሾመ እየተመሩ ነባር እና አዳዲስ ተጫዋቾቻቸው በማጣመር ጨዋታውን ቀርበዋል።
የተመጣጠነ እንቅስቃሴ በማድረግ የመጀመሪያዎቹን ደቂቃዎች የከወኑት ሁለቱ ቡድኖች እስከ 16ኛው ደቂቃ ድረስ የጠራ የግብ ማግባት ዕድል ሳይፈጥሩ ተጉዘዋል። በ7ኛው ደቂቃ ግን ሀዋሳዎች ዓሊ ሱሌይማን ከግራ የሳጥኑ ክፍል ሞክሮ የግብ ዘቡ ወንድወሰን ገረመው በተሳሳተው ኳስ ለግብ ቀርበው ነበር ። የመጀመሪያውን ሙከራ ያደረጉት ሀይቆቹ በጠቀስነው ደቂቃ ደግሞ አዲሱ አቱላ ከርቀት አክርሮ በሞከረው ኳስ ዒላማውን የጠበቀ አጋጣሚ አስመልክተውናል።
በአንፃራዊነት ወደ ግብ በመድረስ የተሻሉት ሀዋሳ ከተማዎች በአጋማሹ አካፋይ ሰዓት በግዙፉ አጥቂ ሙጂብ ቃሲም አማካኝነት ጥሩ ዕድል ፈጥረው ተመልሰዋል። በዚህ ደቂቃም ከቀኝ መስመር የተገኘውን የቅጣት ምት ዳንኤል ደርቤ ሲያሻመው ሙጂብ ከተከላካዮች ጋር ታግሎ የሞከረውን ኳስ ግብ ጠባቂው ወንደሰን አውጥቶበታል። ከመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በተቃራኒ ደቂቃ በደቂቃ ጫናዎች የበዛባቸው ለገጣፎዎች በ26ኛው ደቂቃ እጅ ሰጥተዋል። በዚህም አዲሱ አቱላ ወደፊት የላከውን ተከላካይ ሰንጣቂ ኳስ ዓሊ ሱሌይማን በግራ እግሩ ግብ አድርጎታል።
ጨዋታውን በእጃቸው ያስገቡት ሀዋሳዎች በ31ኛው ደቂቃ ኤፍሬም አሻሞ ከዳንኤል ደርቤ ተቀብሎ በመታው ኳስ መሪነታቸውን በደቂቃዎች ልዩነት ሊያሳድጉ ነበር። በተቃራኒው ጣፎዎች ግልፅ የግብ ማግባት ዕድል መፍጠር ቢቸገሩም ከደቂቃ በኋላ የአብቃል ፈረጃ በረጅሙ የተላከለትን ኳስ በቀኝ እግሩ ተቆጣጥሮ ሰብሮ በመግባት በግራ እግሩ በሞከረው ኳስ አቻ ለመሆን ጥረዋል። ወዲያው ግን ዓሊ ጠንካራ ባልሆነው የቀኝ እግሩ ሁለተኛ ጎል ሊያስቆጥርባቸው ነበር።
አተውት የነበረውን የኳስ እና የጨዋታ ቁጥጥር መልሰው ያገኙት ለገጣፎዎች አጋማሹ ሊጠናቀቅ ሦስት ደቂቃዎች ሲቀሩት በቁመታሙ አጥቂያቸው ካርሎስ ዳምጠው አማካኝነት ግብ አግኝተዋል። በዚህም ከወደ ግራ ካደላ ቦታ የተነሳውን የቅጣት ምት መሐመድ ሙንታሪ መቆጣጠር ተስኖት ከእጆቹ የለቀቀውን ኳስ ኪሩቤል ሲያሻማው ካርሎስ በግንባሩ ከመረብ ጋር አዋህዶታል። አጋማሹም አንድ ለአንድ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ዳግም ወደ መሪነት ለመሸጋገር የተጫዋቾች እና የአደራደር ለውጦችን ያደረጉት ሀዋሳዎች በ57 እና 58ኛው ደቂቃ ዓሊ ከቅጣት ምት ሰዒድ ደግሞ ከክፍት ጨዋታ በሞከሯቸው ኳሶች የጣፎን መረብ ለማግኘት ሞክረዋል። በአጋማሹ መገባደጃ ላይ አቻ የሆኑት ጣፎዎች ደግሞ ለመከላከል ቅድሚያ ሰጥተው ቢጫወቱም ግዙፉን አጥቂ ካርሎስ ዳምጠው ዒላማ ያደረጉ ረጃጅም ኳሶችን በመላክ ከጨዋታው አንዳች ነገር ለማግኘት መንቀሳቀስ ይዘዋል። ይህ ውጥናቸው ሰምሮም በ61ኛው ደቂቃ በዐየር ላይ የመጣውን ኳስ ላውረንስ ላርቴ በግንባሩ ለግብ ጠባቂው መሐመድ ሙንታሪ አቀብላለው ብሎ የመታውን ኳስ ካርሎስ በመሐል አቋርጦት መዳረሻው የግቡ መረብ እንዲሆን አስችሎታል።
በኋላ መስመራቸው ስህተት ከመምራት ወደ መመራት የተሸጋገሩት የአሠልጣኝ ዘርዓይ ተጫዋቾች በ78ኛው ደቂቃ ይባስ ሦስተኛ ጎል ሊያስተናግዱ ነበር። በዚህ ደቂቃም የሀዋሳ ተከላካዮች ፈተና የሆነው ካርሎስ ለራሱ እና ለቡድኑ ሦስተኛ ግብ ለማስቆጠር ቢጥርም ስህተታቸውን ለማረም ጊዜ ያገኙት የኋላ ተጫዋቾች አጋጣሚውን መክተውታል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላም የአቋቋም እና የቅብብል ስህተት የፈፀሙትን ተከላካዮች ኪሩቤል ወንድሙ ሊቀጣ ተቃርቦ ነበር። በቀሪ ደቂቃዎች ግልፅ የግብ ማግባት አጋጣሚ ሳይፈጠር ጨዋታው በለገጣፎ ለገዳዲ 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ታሪካዊውን ጨዋታ በድል ያጠናቀቁት አሠልጣኝ ጥላሁን በድህረ-ጨዋታ አስተያየታቸው በማሸነፋቸው እጅግ እንደተደሰቱ ሳይሸሽጉ ጠቁመው የተጫዋቾቹን የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ አድንቀዋል። አሠልጣኙ ጨምረውም የጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ ካርሎስ ዳምጠው ብቃት አወድሰዋል። የሀዋሳ ከተማው አሠልጣኝ ዘርዓይ በበኩላቸው በቡድናቸው ላይ የታየውን ክፍተት ሸንቆጥ አድርገው በተለይ ሁለተኛው ጎል የቡድኑን ተነሳሽነት እንዳወረደ በመግለፅ በቀጣይ ጨዋታዎች ያሉባቸውን ስህተቶች አርመው እንደሚመጡ ተናግረዋል።