ሦስት ኢትዮጵያዊያን ዳኞች የሴካፋ ዋንጫ ውድድርን እንዲመሩ ተመርጠዋል

በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት የሚከወኑት የሴካፋ ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ ጨዋታዎችን በዳኝነት ለመምራት ሦስት ኢትዮጵያዊያን ዳኞች ጥሪ ደርሷቸዋል፡፡

በምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ስር በሚገኙ ሀገራት መካከል የሚደረገው የ2022 የሴካፋ ከ17 ዓመት በታች ውድድር ቀደም ብሎ ይጀመራል ከተባለበት ወቅት ለሁለት ያህል ጊዜያት ተራዝሞ ነገ በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም በይፋ ይጀመራል፡፡ በሁለት ምድብ ተከፍሎ በስድስት ሀገራት መካከል ለሚደረገው ፍልሚያ የውድድሩ የበላይ አካል ሴካፋ ሀያ ዳኞችን ከዞኑ የመረጠ ሲሆን ከእነኚህን ዋና እና ረዳት ዳኞች ውስጥ ሦስት ዳኞች ከሀገራችን መካተታቸው ታውቋል፡፡

በዚህ ውድድር ላይ ኢንተርናሽናል ዳኞች የሆኑት ቴዎድሮስ ምትኩ በመሀል ትግል ግዛው እና ፋሲካ የኋላሸት ደግሞ በረዳት ዳኝነት እንዲያገለግሉ ጥሪ ደርሷቸዋል።