የመጀመሪያው ሳምንት የሚቋጭባቸውን ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎች

ነገ በሚደረጉ የአንደኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታዎች ዙሪያ ተከታዮቹን መረጃዎች አጠናቅረናል።

ፋሲል ከነማ ከ አዳማ ከተማ

ከቻምፒዮንነት መልስ አምና በሊጉ ሁለተኛ ደረጃን ይዘው የጨረሱት ፋሲል ከነማዎች ከአሰልጣኝ ኃይሉ ነጋሽ ጋር የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን አድርገው ለውድድሩ ደርሰዋል። በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያውን በድል የተወጣው ፋሲል በዚህም ዓመት ለዋንጫ ከሚፎካከሩ ቡድኖች ውስጥ እንደሚካተት ይጠበቃል። ከወትሮው የፉክክር ደረጃቸው እጅግ ዝቅ ብለው ያለፈውን የውድድት ዓመት ያሳለፉት አዳማ ከተማዎች እንደተጋጣሚያቸው ሁሉ ከምክትል አሰልጣኝነት ወደ ዋና አሰልጣኝነት ካመጡት አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ ጋር የዝግጅት ጊዜያቸውን ዝዋይ ላይ አድርገዋል። አዳማ በተከታታይ ዓመታት ሲያሳይ እንደነበረው ከሊጉ ጠንካራ ቡድኖች ተርታ ለመሰለፍ እያለመ የውድድር ዓመቱን በነገው ጨዋታ ይጀምራል።

ፋሲል ከነማ ከጉዳት ነፃ ሆኖ የሊጉን የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደርጋል። አዳማ ከተማ ደግሞ ጉዳት ላይ ሰንብተው ልምምድ የጀመሩት ሲዒድ ሀብታሙ ፣ አቡበከር ወንድሙ ፣ አሜ መሐመድ እና ዊሊያም ሰለሞንን ሊጠቀም የሚችልበት ዕድል ያለ ሲሆን የውጪ ሀገር ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾቹ የወረቀት ሥራ ተጠናቆ ለዚህ ጨዋታ መድረሳቸው ግን እርግጥ አልሆነም።

ከዚህ ጨዋታ ጋር በተያያዛ አምና የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች በ30ኛው ሳምንት ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ሲገናኙ ያልተገባ ባህሪ አሳይተዋል በሚል ሊግ ካምፓኒው በወሰነው መሰረት ባለሜዳ የሆኑበትን የነገውን ግጥሚያ በዝግ የሚያደርጉ ይሆናል።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ነገ 12ኛ ጨዋታቸውን የሚያደጉ ሲሆን እስካሁን ከተገናኙባቸው አጋጣሚዎች ውስጥ አምስቱ ነጥብ በመጋራት ሲቋጩ ፋሲል ከነማ አራቱን አዳማ ከተማ ደግሞ ሁለቱን በድል መወጣት ችለዋል። በእነዚህ ፍልሚያዎች ፋሲል 12 አዳማ ደግሞ 7 ግቦችን አስቆጥረዋል።

ይህንን የዕለቱን ቀዳሚ ጨዋታ በዋና ዳኝነት የሚመሩት አሸብር ሰቦቃ ሲሆኑ ይበቃል ደሳለኝ እና ወጋየሁ አየለ ረዳቶች ፣ በላይ ታደሰ ደግሞ አራተኛ ዳኛ ሆነው ተመድበዋል።

ፋሲል ከነማን በተመለከተ ያዘጋጀነውን የውድድር ዘመን ዳሰሳ ለማንበብ ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ :

የክለቦች የውድድር ዘመን ዳሰሳ | ፋሲል ከነማ

አዳማ ከተማን በተመለከተ ያዘጋጀነውን የውድድር ዘመን ዳሰሳ ለማንበብ ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ :

የክለቦች የውድድር ዘመን ቅድመ ዳሰሳ | አዳማ ከተማ

መቻል ከ ሀዲያ ሆሳዕና

በዘንድሮው የውድድር ዓመት እንደ መቻል ተቀይሮ የመጣ ተወዳዳሪ ማግኘት ይከብዳል። አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝን ከመሾሙ ሌላ ስብስቡን ‘ሙሉ ለሙሉ’ ለሚል ቅጥያ በመቀረበ መልኩ ከመቀየር ባለፈ መከላከያ የሚለው ስያሜውን በመለወጥ ጭምር ለዘንድሮው ውድድር ደርሷል። መቻል ከለውጦቹ አንፃር በፉክክሩ ከሚጠበቁ ቡድኖች ውስጥ አንዱ መሆኑም አልቀረም። 2013 ላይ ያሳዩትን ጠንካራ አቋም በ2014 መድገም ያልቻሉት ሀዲያ ሀሳዕናዎችም እንዲሁ ከአሰልጣኝ ለውጥ ጋር ከተመለሱ ክለቦች ውስጥ ይካተታሉ። ከቀድሞው አሰልጣኛቸው ሙሉጌታ ምህረት ጋር ያላቸው ጉዳይ ባለመጠናቀቁ አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹን በምክትል አሰልጣኝነት ማዕረግ ይዘው የሚቀጥሉት ነብሮቹ ሆሳዕና እና ሀዋሳ ላይ በግማሽ በቀየሩት ስብስብ ዝግጅታቸውን ሲያደርጉ ሰንብተዋል።

የሊጉ አንደኛ ሳምንት ማሳረጊያ በሆነው ጨዋታ የሀዲያ ሆሳዕናዎቹ እንዳለ ደባልቄ እና ቃልአብ ውብሸት በጉዳት እንዲሁም ስቴፈን ኒዪርኮ እና ሪችሞንድ ኦዶንግ የወረቀት ጉዳይ ባለመጨረሳቸው የማይሰለፉ ሲሆን መቻል ስብስቡ ሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኝ አረጋግጠናል።

ቡድኖቹ በሊጉ አራት ጨዋታዎችን ሲያደርጉ አምስት ግቦችን ያስመዘገበው መቻል ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ ሁለት ግቦችን ያስቆጠረው ሀዲያ ሆሳዕና አንዴ ድል አድርጎ በአንድ ጨዋታ ነጥብ ተጋርተዋል።

ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት ለመምራት ለሚ ንጉሴ ሲሰየሙ ረዳቶቹ ተመስገን ሳሙኤል እና ለዓለም ዋሲሁን እንዲሁም አራተኛ ዳኛ በመሆን ባምላክ ተሰማ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል።

መቻልን በተመለከተ ያዘጋጀነውን የውድድር ዘመን ዳሰሳ ለማንበብ ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ :

የክለቦች የውድድር ዘመን ቅድመ ዳሰሳ | መቻል

ሀዲያ ሆሳዕናን በተመለከተ ያዘጋጀነውን የውድድር ዘመን ዳሰሳ ለማንበብ ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ :

የክለቦች የውድድር ዘመን ቅድመ ዳሰሳ | ሀዲያ ሆሳዕና