ሪፖርት | አፄዎቹ ሊጉን በድል ጀምረዋል

ሁለት ቀይ ካርዶች በተመዘዙበት ጨዋታ ፍቃዱ ዓለሙ በሁለቱ አጋማሾች ባስቆጠራቸው ጎሎች ፋሲል ከነማ አዳማ ከተማን 2-1 አሸንፏል።

ጨዋታው ቀዝቅዝ ያለ አጀማመር ያደረገ ቢመስልም በክስተቶች ለመሞላት ጊዜ አልወሰደበትም። የተሻለ ወደ ተጋጣሚ ሜዳ ቀረብ ይሉ የነበሩት ፋሲል ከነማዎች 7ኛው ደቂቃ ላይ ሽመክት ጉግሳ በተከላካዮች መሀል ሰንጥቆ ያሳለፈለትን ኳስ በቀኝ አድልቶ ሳጥን ውስጥ የገባው ፍቃዱ ዓለሙ ጎል አድርጎታል። ከግቡ በኋላ የተሻለ የማጥቃት ኃይላቸውን የጨመሩት አዳማዎችም 14ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ ንክኪዎች የታጀበ ጎል አስቆጥረዋል።

ቡድኑ በግራ መስመር በከፈተው እና ወደ አምስት ከሀምሳው የተመለሰውን ኳስ ዳዋ ሆቴሳ ወደ ግራ ሲያወጣለት መስዑድ መሐመድ በውጪ እግሩ ዳግም የመለሰውን አሜ መሐመድ ግብ አድርጎታል። ሆኖም አዳማዎች ደስታቸውን አጣጥመው ሳይጨርሱ በደስታ አገላለፅ ውስጥ ዳዋ በተመለከተው ቢጫ ካርድ ምክንያት ከአርቢትሩ ጋር ንክኪ የፈጠረው ዊሊያም ሰለሞን በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል።

ከአቻ ውጤቱ በኋላ በእንቅስቃሴ ጨዋታው ሰከን ያለ ሲሆን በቁጥር ያነሱት አዳማ ከተማዎች የተሻለ ጉልበት ባለው የኳስ ቁጥጥር ለተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ቀርበው ተንቀሳቅሰዋል። በአንፃሩ የመልሶ ማጥቃት መልክ የታየባቸው ፋሲል ከነማዎች ከረጅም ርቀት ሙከራዎችን በማድረግ ተወስነው ቆይተዋል።

በመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች ፋሲሎች የጨዋታ ቁጥጥር የበላይነታቸውን መልሰው ማግኘት የቻሉ ሲሆን በተለይም 38ኛው ደቂቃ ላይ የጎሉ ኮፒ በሆነ ድንቅ ፓስ ሽመክት ጉግሳ ፍቃዱን ከግብ ጠባቂ ጋር ቢያገናኘውም አጥቂው በደካማ ውሳኔ አሰጣጥ አምክኖታል። አዳማዎችም 42ኛው ደቂቃ ላይ ዳዋ ሆቴሳ ከዓለምብርሀን ይግዛው ጀርባ በመግባት እንዲሁም ከአንድ ደቂቃ በኋላ ደግሞ ግብ አስቆጣሪው አሜ መሐመድ ከቀኝ መስመር ከርቀት ጥሩ ሙከራዎች አድርገዋል።

ከዕረፍት መልስ 49ኛው ደቂቃ ላይ ዓለምብርሀን ይግዛው በግንባር ባደረገው ሙከራ ማጥቃታቸውን ይቀጠሉት ፋሲሎች ሁለተኛ ጎል አግኝተዋል። ይሁንን እንዳሻው ከመሀል ሜዳ በረጅሙ በመላክ ያስጀመረውን ጥቃት አምሳሉ ጥላሁን ከግራ አድርሶት ዓለምብርሀን ተከላካዮችን በማለፍ ወደ ውስጥ ያመቻቸለትን ፍቃዱ 53ኛው ደቂቃ ላይ ሁለተኛ ግብ አድርጎታል።

ከመጀመሪያው ዝግ ባለ ፍጥነት በፋሲል ከነማ የእንቅስቃሴ የበላይነት በቀጠለው ጨዋታ ኢንተርናሽናል አርቢትር አሸብር ሰቦቃ 68ኛው ደቂቃ ላይ የጨዋታውን ሁለተኛ ቀይ ካርድ መዘዋል። የቀይ ካርዱ ሰለባ የሆነው ሽመክት ጉግሳ አማኑኤል ጎበና ላይ ጥፋት ሰርቶ ጨዋታው ባልቆመበት ሁኔታ ኳስ በእጅ በመያዙ ነበር ከሜዳ የተወገደው። 

ተጋጣሚዎቹን በቁጥር ካመጣጠነው ከዚህ ውሳኔ በኋላ አዳማዎች የተሻለ ተነቃቅተው ታይተዋል።

ከአዳማ ለግብ የቀረቡ ቅፅበቶች ውስጥ 84ኛ ደቂቃ ላይ ደስታ ዮሐንስ ሳጥን ውስጥ ነፃ ሆኖ ገብቶ በውሳኔ የዘገየበት እንዲሁም ከአንድ ደቂቃ በኋላ አድናን ረሻድ ከሳጥን ውጪ ያደረገው ሙከራ ተጠቃሽ ነበሩ። ሆኖም አዳማዎች አቻ የመሆን ጥረታቸው ሳይሰምር ፋሲል ከነማ ውጤቱን አስጠብቆ መጨረስ ችሏል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ ቀይ ካርዱ ተፅዕኖ ቢፈጥርባቸውም የተቻላቸውን ለማድረግ እንደሞከሩ ገልፀው ሽመክትም በቀይ ሲወጣ በቁጥር ከተመጣጠኑ በኋላ አቅም በመጨረሳቸው ባሰቡት መጠን ዕድል አለመፍጠራቸውን ተናግረዋል። አሰልጣኝ ኃይሉ ነጋሽ በበኩላቸው ጨዋታው ከባድ እንደሚሆን መገመታቸውን አስታውሰው የቁጥር ብልጫ በነበራቸው ሰዓት ብዙ በመሮጣቸው ወደ መጨረሻው ላይ ለመዳከማቸው ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።

ያጋሩ