ሪፖርት | መቻል የመጀመሪያ ሦስት ነጥቡን አሳክቷል

በሊጉ የመጀመሪያ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ የምንይሉ ወንድሙ የፍፁም ቅጣት ምት ጎል መቻል ሀዲያ ሆሳዕናን 1-0 እንዲያሸንፍ አድርጋለች።

ጨዋታው ከባድ ሙከራ በማስመልከት የጀመረ ነበር። 2ኛ ደቂቃ ላይ ፍፁም ዓለሙ ከምንተስኖት አዳነ ከቀኝ በተነሳ እና ተሾመ በላቸው ባመቻቸው ኳስ ከሳጥን መትቶ ወደ ላይ የተነሳው ይህ ሙከራ ጨዋታውን የተነቃቃ ቢያስመስለውም በሂደት እጅግ ተቀዛቅዞ ታይቷል።

የዳኛ ፊሽካ እየበዛበት በሄደው እንቅስቃሴ በፀጋዬ ብርሀኑ እና ብርሀኑ በቀለ የሜዳው ቁመት ጥምረት ወደ ቀኝ አድልተው ለማጥቃት ይጥሩ የነበሩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች የቆሙ ኳስ ዕድሎችንም ያገኙ የነበረ ቢሆንም ከባድ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። 14ኛ ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት የተነሳ እና ሄኖክ አርፌጮ ከግራ ወደ ውስጥ የላከውን ኳስ ቶማስ ስምረቱ ለማውጣት ሞክሮ ተቆርጦበት ራሱ ላይ ለማቆጠር ተቃርቦ ተክለማሪያም ሻንቆ ያዳነው የነብሮቹ ለግብ የቀረበ ዕድል ነበር።

ከሳጥን ሳጥን ዝግ ያለ ፍሰት በማሳየት በቀጠለው እና ከሙከራ በተራራቀው ጨዋታ የተሻለ የኳስ ምስረታ ሂደት የነበራቸው መቻሎች በሀዲያ ሳጥን አቅራቢያ የደረሱባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት የሚባሉ ባይሆኑም ባልተሳኩ የመጨረሻ ቅብብሎች እና ደካማ የመጨረሻ ውሳኔ አሰጣጦች ዓይን ሳቢ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። አጋማሹ ሊጠናቀቅ ሲቃረብ ተሾመ ለላቸው እና ፍፁም ዓለሙ ከሳጥን ውስጥ ያደረጓቸው ሙከራዎች ብቻ በመቻል በኩል የተሻሉ ተብለው የሚጠቀሱ ነበሩ።

ከዕረፍት መልስ ነብሮቹ የተሻለ በነበረው የቀኝ መስመራቸው በንፅፅር ጫና ፈጥረው ሲታዩ ጠንካራ ሙከራ በማድረግ ግን መቻሎች ቀዳሚ ሆነዋል። 59ኛው ደቂቃ ላይ ምንይሉ ወንድሙ ከፍፁም ዓለሙ የደረሰውን ኳስ ከሳጥን ውስጥ በጥሩ ሁኔታ አክርሮ ሞክሮ ፔፔ ሰይዶ በቅልጥፍና ያዳነበት ይህ ሙከራ የጨዋታው የመጀመሪያ ጠንካራ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ሆኗል። ግብ ጠባቂው 70ኛው ደቂቃ ላይም ከነዓን ማርክነህ ከሳጥን ውጪ ያደረገውን ሌላ አደገኛ ሙከራ ማምከን ችሏል።

ከሙከራዎቹ ባሻገር መቻሎች የኳስ ንክኪያቸው ከቀደመው በተሻለ ፍሰት ወደ ሆሳዕና የግብ ክልል ሲቀርቡ ታይተዋል። በመልሶ ማጥቃት ምላሽ ለመስጠት ሲሞክሩ በታዩት ሆሳዕናዎች በኩል ደግሞ 79ኛው ደቂቃ ላይ ባዬ ገዛኸኝ ከቅጣት ምት በቀጥታ ያደረገው ሙከራ ግብ ከመሆን የተረፈው በተክለማሪያም ሽንቆ ቅልጥፍና ነበር። ሆኖም መቻልን የበላይ ያደረገ የጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ ክስተት 82ኛ ደቂቃ ላይ ተፈጥሯል። በዚህም ተቀይሮ የገባው የሀዲያ ሆሳዕናው ተመስገን ብርሀኑ ፍፁም ዓለሙ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ መቻሎች ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ምንይሉ ወንድሙ አስቆጥሯል።

ነብሮቹ ቀጥተኝነታቸውን በመጨመር በቀሩት ደቂቃዎች የአቻነት ግብ ፍለጋ ጥረት ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው መቻል ጨዋታውን 1-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።

ከጨዋታው በኋላ አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ የጨዋታውን ጠጣርነት አንስተው ቡድናቸው ጠንካራ ተጋጣሚን በመፈተኑ ተጫዋቾቻቸውን በማመስገን የግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶን አቋም አድንቀዋል። አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በበኩላቸው በውጤቱ መደሰታቸውን ገልፀው የቡድናቸው ውህደት ገና በሚፈልጉት ደረጃ ላይ አለማድረሱን እና ያንን ለማድረግ ጠንክረው አንደሚሰሩ ተናግረዋል።