ሴካፋ | ኢትዮጵያ በሱማሊያ ተረታለች

በ17 ዓመት በታች የሴካፋ ውድድር የመክፈቻ ቀን አስተናጋጁዋ ሀገር ኢትዮጵያ በሱማሌያ ስትረታ ብሩንዲም በዩጋንዳ በሰፋ የግብ ልዩነት ተሸንፋለች።

በአልጄሪያ አስተናጋጅነት የሚከናወነው የ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ላይ ለመሳተፍ የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ሀገራት ብሔራዊ ቡድኖች የዞኑን የማጣሪያ ፍልሚያ በዛሬው ዕለት ማከናወን ጀምረዋል። ከቀትር በኋላ በተደረጉት የሁለቱ ምድብ የመጀመሪያ ጨዋታዎችም ዩጋንዳ እና ሱማሌያ ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ ዕድላቸውን አስፍተው ወጥተዋል።

7 ሰዓት ላይ በቡሩንዲ እና ዩጋንዳ መካከል የተደረገው የውድድሩ የመክፈቻ ጨዋታ የአንድ ቡድን የበላይነት ነግሶ የታየበት ነበር። በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ድንቅ የነበሩት ዩጋንዳዎች ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ በመከተል በቶሎ ውጤት ለመያዝ ሲጥሩ ታይቷል። ይህ እንቅስቃሴያቸው ተሳክቶም አሌክስ ይጋ በ17 እና 45ኛው ደቂቃ እንዲሁም አራፋት ንኮላ በ35ኛው ደቂቃ ባስቆጠሯቸው ሦስት ጎሎች መሪ ሆነው ለእረፍት የወጡ ሲሆን በሁለተኛው አጋማሽ ሪቻርድ ኦኬሎ አንድ ጎል አክሎ ጨዋታውን አራት ለምንም አሸንፈዋል። ቡሩንዲዎች በሁለተኛው አጋማሽ የተቻለ ለመንቀሳቀስ ቢጥሩም ወደ ጨዋታው መመለስ ተስኗቸዋል። በ82ኛው ደቂቃ ተቀይሮ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ ለተከላካዮች ፈተና የሆነው አሌክስ ይጋ የጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ የሆነበትን ውሎ አሳልፏል።

በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የኢትዮጵያ እና ሱማሌያ ጨዋታ ደግሞ 10 ሰዓት ላይ በአንፃራዊነት በርከት ባሉ ደጋፊዎች ታጅቦ ተከናውኗል።ገና በጅምሩ በ12ኛው ደቂቃም ፍልሚያው ሱማሊያን ቀዳሚ አድርጓል። በዚህም አብዲአፊድ መሐመድ በተከላካዮች መካከል የደረሰውን ኳስ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ተከላካዮች እና ግብ ጠባቂውን በማለፍ ግብ አስቆጥሯል።

ወደ ጨዋታው ለመመለስ መጣር የጀመሩት ኢትዮጵያዎች በ18ኛው ደቂቃ አቤኔዘር ተክሉ ከመዓዘን ምት መነሻን ያደረገ ኳስ ከርቀት አክርሮ መትቶ ለጥቂት ወጥቶበታል። ከደቂቃ በኋላ ግን የግቡ ባለቤት አብዲአፊድ መሐመድ ለተሰነዘረባቸው ጥቃት ወዲያው ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ሞክሮ ነበር። ይህ ብቻ ሳይሆን አብዱራሂን ሙሐመድ ከእድሪስ መሐመድ ጋር ተቀባብሎ ሌላ ጠንከር ያለ ሙከራ ቢያደርግም ተከላካዮች አውጥተውበታል።

የቡድን ውህደት ችግር የታየበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አጋማሹ ሊገባደድ ሰከንዶች ሲቀሩት ከመዓዘን ምት በተነሱ ሁለት ኳሶች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥሮ ነበር። በቅድሚያ ብሩክ ስዩም በግንባሩ የላከውን ኳስ የግብ ዘቡ አብዲካድር ዓሊ ሲመልሰው በመቀጠል ደግሞ አክረም ዴታሞ ያሻማውን ኳስ ዮርዳኖስ ገለቱ ሞክሮት ለጥቂት ወጥቶበታል

የአሠልጣኝ ታዲዮስ ተጫዋቾች ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረም ጫና ፈጥረው መጫወት ይዘዋል። በ49ኛው ደቂቃም ከወደ ቀኝ ካደላ ቦታ የተገኘውን የቅጣት ምት ኪሩቤል ዳኜ ሞክሮት በረኛው እንደምንም ባያድነው አቻ ለመሆን ተቃርበው ነበር። ከስድስት ደቂቃዎች በኋላም አቤኔዘር ተክሉ ከቀኝ መስመር የሞከረውን ኳስ አልቀመስ ያለው አብዲካድር ዓሊ አውጥቶታል። በተቃራው የሚፈልጉትን በጊዜ ያገኙት ሱማሊያዎች መከላከል ላይ ተጠምደው መጫወታቸውን ቀጥለዋል። በ74ኛው ደቂቃ ግን በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ሄደው እድሪስ መሐመድ ከአብዲራህኒ መሐመድ ተቀብሎ ወደ ግብ በላከው ኳስ መሪነታቸው ሊያሰፉ ነበር። ከደቂቃ በኋላ ከግራ መስመር የተሻገረን ኳስ ተቀይሮ የገባው ቢኒያም ተክሉ በግንባሩ ከሞከረው ውጪ ባለሜዳዎቹ አቻ ለመሆን ጥረቶችን ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ጨዋታውም በሱማሌያ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ አሠልጣኝ ታዲዮስ ተክሉ ተከታዩን የድህረ-ጨዋታ አስተያየት ሰጥተዋል።

ስለጨዋታው…?

“ጨዋታውን ስንጀምር የመጀመሪያዎችን 15 ደቂቃዎች ተጭነን ለመጫወት ነው ተነጋግረን የገባነው። ሱማሊያዎች በዚህ መልኩ ይመጣሉ ብለን አልጠበቅንም ፤ ተጭነው ከራሳችን ሜዳ እንዳንወጣ አድርገውን ነበር። በዛ ሽግግር ውስጥ ጨዋታውን ለማስተካከል ጥረት በምናደርግበት ሰዓት በተፈጠረ ስህተት በመጀመሪያው 11 ደቂቃ ግብ ተቆጥሮብናል። ክፍተቶቻችንን እያስተካከልን ሄደን ነበር ፤ ግን ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች አለመጠቀማችን እንድንሸነፍ ምክንያት ሆኖናል።”

ስለዝግጅታቸው…?

“ለዝግጅት የነበሩን ሁለት ሳምንታት ነበሩ። ቡድኑ ከመጀመሪያው ዕድገት እያሳየ ነው። ከወዳጅነት ጨዋታዎች ጀምሮ እያደገ ነው የመጣው። ከነበረን ጊዜ አንጻር ጥሩ ዝግጅት አድርገናል ብዬ ነው የማስበው።”

ስለተሸነፉበት ምክንያት…?

“ሱማሊያ ጠንካራ ቡድን ነው ፤ ቢሆንም የእኛ ድክመት ተጨምሮበታል። በልጠን ማሸነፍ እንችል ነበር። እነሱ መከላከል ላይ ላደረጉት ነገር ማድነቅ እፈልጋለሁ።”

ቡድኑ ላይ ስለነበረው ታክቲካዊ አጨዋወት…?

“ተጫዋቾችን ከተለያዩ ክልሎች ነው የመለመልነው። በአካዳሚ ያደጉ ስላልሆኑ የታክቲክ መረዳታቸው ዝቅተኛ ነበር። አሁን ግን በ15 ቀን የተሻለ ዕድገት አሳይተናል።”

በስነልቦና ጠንካራ ስላለመሆናቸው…?

“በስነልቦና በደንብ ተዘጋጅተናል ግን ግብ ሲቆጠር መደናገጥ ነበር የመጀመሪያ ጨዋታ ስለሆነ። በሚቀጥሉት ጨዋታዎች ተነሳሽነታችን ይጨምራል።”