አዲሱ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ዘመን ባሳለፍነው ሳምንት ዓርብ ጅማሮውን አድርጓል። እኛም አዲሱን የውድድር ዘመን መጀመር አስመልክቶ በየዓመቱ ከቡድን ግንባታ መርህ በተፃረረ መልኩ ባለ ሁለት አሀዝ ብዛት ያላቸውን ተጫዋቾች ማዘዋወር መደበኛ ነገር ስለሆነበት ሊጋችን ጥቂት ነጥቦችን ለማንሳት ወደናል።
አዲስ ዓመት እና አዳዲስ ነገሮች የተዛመዱ ናቸው። እርግጥ ስለ አዲስ ነገር ለማሰብ አዲስ ዓመትን መጠበቅ ግድ ባይልም አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር በተለያዩ መልኮች ራስን ለውጦ የተሻለ ሆኖ መገኘት የተለመደ ሰዋዊ እሳቤ ነው። ይህን ሰዋዊ እሳቤ ከፍ አድርገነው ደግሞ ተቋማዊ ገፅታ ብናላብሰው ተቋማት ከዓምናው አፈፃፀም በመነሳት በአዲሱ ዓመት ልቀው ስለመገኘት ያስባሉ። በዚህ ሂደት አሰራርን ከማዘመን አልፎ ተቋሙን በሰው ሃይል የማጠናከር እና ሌሎች አዳዲስ መንገዶችን ሊከተሉ ይችላሉ።
እግር ኳስ ክለቦቻችን እስከነ ደካማ አደረጃጀታቸውም ቢሆን እንደ አንድ ተቋም ብለን ብንወስዳቸው ከውድድር ዘመን መጠናቀቅ በኋላ ለሚመጣው የውድድር ዘመን ተሽሎ ስለመቅረብ ያልማሉ። ታድያ የእኛ ክለቦች ተሻሽሎ የመቅረብ ህልም አጠቀላይ ያሉ ጉድለቶችን ከመሙላት እና የተሳሳቱ አካሄዶችን ከማረም ይልቅ ባለሙያዎችን በመቀየር ማለትም አሰልጣኞችን እና ተጫዋቾችን በጅምላ በመቀየር ላይ ብቻ የተንጠለጠለ ሲሆን እንመለከታለን።
ምናልባት እነዚህ የአሰልጣኝ መለዋወጦች ሆነ በተጫዋቾች የጅምላ ቅየራ በተለወጠ ስብስብ ለመቅረብ መሻት በራሱ ሀጢያት ባይሆንም ከቀደመው የውድድር ዘመን ግምገማ በተገኙ እግር ኳሳዊ ግኝቶች በተለዩ ድክመቶች መነሻ አለመሆናቸው እና በየዓመቱ ሜዳ ላይ አንዳች የተለወጠ ነገር በሌለበት በየዓመቱ መደጋገሞች እግር ኳሱን እየመሩ የሚገኙ አካላት ላይ ጥያቄ እንድናነሳ ያስገድዳሉ።
የዚህ የጅምላ ቅየራ አንደኛው እና ዋነኛው መነሻ የክለቦች የአሰልጣኝ ሹም ሽር ነው። ረዘም ላሉ ዓመታት በአንድ ክለብ ቆይተው ከጊዜያዊ ማሸነፍ መሸነፍ በዘለለ ቡድኖችን በሒደት ገንብተው “አንፃራዊ ስኬትን” አስመዘገቡ ብለን የምንጠቅሳቸው አሰልጣኞች አሁን አሁን ፈልጎ ማግኘት ከብዷል። ከዓመት ዓመት ክለብ እየለዋወጡ መሥራት የተለመደው መንገድ ከሆነ ሰነባብቷል። አዲስ በጀመርነው የውድድር ዘመን በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን አብረዋቸው የውድድር ዘመኑን ከፈፀሙ አሰልጣኞች ጋር ተለያይተው በአዲስ አሰልጣኝ የቀረቡ ክለቦች ብዛት ሰባት ነው። በዚህ ቁጥር ላይ ዓምና በውድድር ዘመን መሐል አሰልጣኝ ቀይረው በአዲሱ የውድድር ዘመን ያስቀጠሉት አዳማ ከተማ ፣ ፋሲል ከነማ እና ሲዳማ ቡናን ከጨመርን ይህ ቁጥር ወደ አስር ከፍ ይላል። ይህም እጅግ አሳሳቢ ቁጥር ነው። በየዓመቱ በዚህ መጠን ከፍ ያለ ቁጥር ያላቸው ክለቦች አዳዲስ አሰልጣኞችን መቅጠራቸው “አዲስ ቡድን” ለመገንባት ቀዳሚው ገፊ ምክንያት ስለመሆኑ አያጠያይቅም።
ከቅጥሮቹ ባለፈ አብዛኞቹ አሰልጣኞች እጃቸው ላይ ባሉ ተጫዋቾች ሥራቸውን ከመስራት ይልቅ የሚያወቋቸውን እና ከዚህ በፊት በተለያዩ አጋጣሚዎች አብረዋቸው የሰሩትን ተጫዋቾች ወደ አዲስ ክለባቸው ሲያስኮበልሉ እንመለከታለን። ይህም ባልከፋ ነበር ፤ የነበረው ቡድን ላይ የተወሰኑ የአሰልጣኙ ምርጫ የሆኑ ተጫዋቾች ማምጣት የተለመደ ቢሆንም ከአስር የሚልቁ ተጫዋቾችን በአንድ ጊዜ ወደ አዲሱ ቡድንህ ማምጣት ግን ፍፁም ስህተት ነው።
ቡድን በአንድ ጀምበር አይገነባም፤ ይልቁንስ በሂደት እንደሚገነባ ግልፅ ነው። ይህ ሂደት ምናልባት ነገሮች ከተሰካኩ በአጠረ ጊዜ አልያም የዓመታትን ሂደት ሊፈጅ እንደሚችል ይታመናል። ነገር ግን በእኛ እግር ኳስ በዚሁ ጤናማው መንገድ የሚጓዙ ቡድኖች ቁጥር እጅግ አናሳ ነው። ስለ ቡድን ግንባታ ስናስብ ከመሠረታዊ ፅንሰ ሀሳቦች አንዱ የቡድን መረጋጋት እጅግ ወሳኝ ነው። በሀገራችን ግን ብዙ ቡድኖች በየክረምቱ በጅምላ የተጫዋቾች ቅያሬ መነሻነት በየዓመቱ በስብስብ ደረጃ ብዙ መለዋወጦችን መመልከት በጣም የተለመደ ነው። ነገርግን በአንፃሩ ይህን የተለመደ ሂደት የሰበሩ እና የተረጋጉ ቡድኖች ግን በተሻለ መልኩ ውጤታማ ስለ መሆናቸው ያለፉት ሁለት ዓመታት የሊጉ አሸናፊ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ፋሲል ከነማ የተገነቡበት መንገድ እና ከዓመት ዓመት የነበራቸውን እርጋታ በአስተውሎት መመልከት ተገቢ ይሆናል።
ባሳለፍነው ክረምት አስራ ስድስቱ የሊጉ ተሳታፊ ክለቦች አቅማቸው በፈቀደ መልኩ በገበያው ለመንቀሳቀስ ጥረት አድርገዋል። በዚህም ሦስት ተጫዋቾችን ብቻ ካስፈረሙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች አንስቶ በገበያው አስራ ሰባት አዳዲስ ተጫዋቾችን እስከሸመቱት ወልቂጤ ከተማዎች ድረስ በርከት ያሉ ዝውውሮች የተፈፀሙበት ክረምት ነበር ያሳለፍነው። እንደ አጠቃላይ ግን የሊጉ ክለቦች በክረምቱ ያሳለፉትን እንቅስቃሴ በሁለት ከፍሎ መመልከት ይቻላል።
የመጀመሪያው ጎራ እጅግ የተረጋጋ እንቅስቃሴን በገበያው ያደረጉ ክለቦች የሚገኙበት ነው በዚህም ዝርዝር ውስጥ ቅዱስ ጊዮርጊስ (3 ተጫዋቾች ) ፣ ድቻ (4 ተጫዋቾች) ፣ አርባምንጭ ከተማ (6 ተጫዋቾች) እና ፋሲል ከተማ (7 ተጫዋቾች) ወደ ስብስባቸው መቀላቀል ችለዋል። እነዚህ አራት ክለቦች አምና ከነበሯቸው አሰልጣኞች ጋር የቀጠሉ ሲሆን በዝርዝር ክለቦቹ የፈፀሟቸውን ዝውውሮችን ለተመለከተ አምና የነበረውን የቡድናቸውን ክፍተት እንዲሁም የፋሲል ከነማ ደግሞ በክረምቱ ባልተለመዱ መልኩ ከቡድኑ በለቀቁ ተጫዋቾች ምትክ የተፈፀሙ ዓላማ ያላቸውን ዝውውሮች ስለመፈፀማቸው ገና አንደኛው ሳምንት ላይ ሆኖ መናገር ይቻላል።
ከዚህ ባለፈ ሁለተኛው ጎራ ደግሞ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ተጫዋቾች ያዘዋወሩ ቡድኖች የተካተቱበት ነው። ወልቂጤ ከተማ (17 ተጫዋቾች) ፣ መቻል (16 ተጫዋቾች) ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ኢትዮጵያ መድን (15 ተጫዋቾች) ፣ ለገጣፎ ለገዳዲ (13 ተጫዋቾች) ፣ ኢትዮጵያ ቡና እና ባህር ዳር ከተማ (12 ተጫዋቾች) ፣ ሀዲያ ሆሳዕና እና ሲዳማ ቡና (11 ተጫዋቾች) ፣ ድሬዳዋ ከተማ (10 ተጫዋቾች) ፣ አዳማ ከተማ (9 ተጫዋቾች) ፣ ሀዋሳ ከተማ (8 ተጫዋቾች) በክረምቱ ማዘዋወር ችለዋል።
ምናልባት በዚህ በሁለተኛው ዝውውር ውስጥ ከተካተቱት ቡድኖች ከታችኛው ሊግ በማደጋቸው ቡድናቸውን “ፕሪምየር ሊጋዊ” ለማድረግ አልያም አብዛኞቹ አዲስ አሰልጣኝ ቅጥር ተከትሎ የሚፈፀሙ ተለምዷዊ “አዲስ ቡድን” ግንባታ መንገድን በተከተለ መንገድ የተፈፀሙ ስለመሆናቸው ማንሳት ይቻላል። እንደው የተዘዋወሩት ተጫዋቾች መብዛት ወደ ጎን ትተን በመሰረታዊነት አንድ አዲስ ተጫዋች ወደ አዲስ ክለብ ዝውውር ሲያደርግ ቢያንስ በሚሄድበት ክለብ ላይ በእግር ኳስ ብቃቱ (Quality) ፣ በጨዋታ ባህሪው (profile) ወይንም ደግሞ ለቡድኑ በሜዳም ሆነ ከሜዳ ውጭ የሚሰጠው የተለየ አዕምሯዊ አበርክቶ(Character) ሊኖር ይገባል። ታድያ በዚህ መመዘኛዎች አብዛኞቹን ዝውውሮች ከመዘናቸው ግን አብዛኞቹ የተለየ ነገር ለአዲሱ ቡድናቸው ስለመጨመራቸው ያጠራጥራሉ።
ታድያ እነዚህ ዝውውሮች ተፅዕኗቸው እዚህ ላይ አያበቃም። በመጀመሪያ የጨዋታ ሳምንቱ በተደረጉ ስምንት ጨዋታዎች ላይ አንድ አዲስ ተጫዋችን በመጀመሪያ ተመራጭት ካስጀመሩት ወላይታ ድቻ እና ፋሲል ከነማ አንስቶ ለሙሉነት የቀረበ በአዳዲስ ተጫዋቾች የተሞሉ ቡድኖችን እንድንመለከት አስገድደዋል። እንደ ዝውውር ገበያ ተሳትፏቸው ሁሉ እነዚህን ቡድኖች በሁለት ከፍለን ከተመለከተን ድቻ (1 አዲስ ተጫዋችን) ፣ ሀዲያ ሆሳዕና እና ሲዳማ ቡና (2 አዳዲስ ተጫዋቾችን) ፣ አዳማ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ (3 አዳዲስ ተጫዋቾችን) እና አርባምንጭ ከተማ (4 አዳዲስ ተጫዋቾችን) በመጀመሪያ አስራ አንዳቸው ተጠቅመዋል። በአንፃሩ በብዙ ተለውጠው ከቀረቡት ደግሞ ወልቂጤ ከተማ (9 አዳዲስ ተጫዋቾችን) ፣ ኢትዮጵያ መድን እና መቻል (8 አዳዲስ ተጫዋቾችን) ፣ ኢትዮጵያ ቡና (7 አዳዲስ ተጫዋቾች) በመጀመሪያ ተሰላፊነት ሲያስጀምሩ ባህር ዳር፣ ድሬዳዋ እና ሀዋሳ ከተማ (6 አዳዲስ ተጫዋቾች) እንዲሁም ለገጣፎ ለገዳዲ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ (5 አዳዲስ ተጫዋቾች) በመጀመሪያው የጨዋታ ሳምንት በመጀመሪያ ተመራጭነት ተጠቅመዋል።
እነዚህ ቁጥሮች በጥቅል ስንመለከታቸው ደግሞ በመጀመሪያ የጨዋታ ሳምንት ጨዋታቸውን ያደረጉት 16 የሊጉ ክለቦች በአማካይ በመጀመሪያ አስራ አንድ ዝርዝራቸው ላይ የ4.81(አምስት) ዓምና በስብስባቸው ያልነበሩ አዲስ ተጫዋቾችን ተጠቅመዋል። ይህ በራሱ ከፍተኛ ቁጥር ቢሆንም በቀላሉ ለመረዳት እንዲረዳ ይህ ማለት ቡድኖች በየሁለት ዓመቱ ሙሉ ለሙሉ ቡድናቸውን ይቀየራሉ እንደማለትም ነው።
እግርኳስ አሁን በደረሰበት ደረጃ በሌሎች ሀገራት ቡድኖች በአንድ የዝውውር መስኮት በቀጥታ ወደ መጀመሪያ ተሰላፊነት የሚመጡ ሦስት አልያም አራት ተጫዋቾችን ሲያመጡ ለቡድን ውህደት ከሚፈጀው ጊዜ አንፃር አደገኛ ተደርጎ በሚወሰድበት በዚህ ዘመን የእኛ ሀገር ተሞክሮ ደግሞ በግርምት እጅን በአፍ የሚያሲዝ እንደሆነ ቀጥሏል።
ሊጋችን እርግጥ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የሚታዩ እምርታዎችን እያሳየ ስለመሆኑ ብናወራም በሜዳ ላይ በሚታይ እግር ኳሳዊ ፉክክር ረገድ ግን ብዙ እንደሚቀረን ማስተዋል ይቻላል። የሊግ አክሲዮን ማህበሩ ዘንድሮ በዋነኝነት ሊሰራባቸው ካቀዳቸው ጉዳዮች አንዱ ጨዋታዎች በተሻለ የተመልካች ቁጥር ታጅበው እንዲደረጉ ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገር ይሰማል። ነገርግን ሊጋችን አሁን ባለው የፉክክር ቁመና ለሀገራቸው እግር ኳስ ሩቅ የሆኑ አዳዲስ እና በእግር ኳሳዊ ፉክክር ተስበው ወደ ሜዳ የሚመጡ ደጋፊዎችን ለመሳብ በሚያስችል ደረጃ አይገኝም። በየጨዋታ ሳምንታቱ እጅግ አሰልቺ ይዘት የተላበሱ ደካማ የጥራት ደረጃ ያላቸው ጨዋታዎች ቁጥር ቀላል የሚባል አይደሉም። በመሆኑም የሊጉን የፉክክር ደረጃ ከማሻሻል አንፃር በዚህ አይነት አካሄድ ከዓመት ዓመት በሽግግር ውስጥ በሚጓዙ ክለቦች ይህን ሂደት ይቀለበሳል ለማለት ፍፁም አስቸጋሪ ነው።
ምናልባት ከዚህ ጋር ተያይዞ በመልካምነቱ ሊነሳ የሚችለው ጉዳይ የተጫዋቾች የዝውውር ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እየናረ መምጣቱን ተከትሎ በርከት ያሉ የከተማ አስተዳደር እና የመንግሦት የልማት ድርጅቶች ክለቦች እየተቸገሩ መምጣታቸው ነው። ይህ ብዙሀኑ ክለቦች በዋጋ መነሻነት እንዲገለሉ (Price Discrimination) መፈጠርን “በእርግማን ውስጥ ያለ ምርቃት” መውሰድ ተገቢ ነው። ይህም ክለቦች ከተለመደው በጅምላ በከፍተኛ ዋጋ ተጫዋቾችን ከሌሎች ክለቦች ከማዘዋወር ይልቅ ገንዘብ ካላቸው ክለቦች ጋር ለመገዳደር የሚያስችሏቸውን አቅምን ያገናዘቡ ብልሀት የታከለባቸውን መንገዶችን ወደ መጠቀሙ እንዲመጡ ሊያስገድዳቸው ይችላል ተብሎ ይጠበቃል።
በመጨረሻም በዚህ ማብቂያ በሌለው በዓመት ዓመት የመለዋወጥ አዙሪት ውስጥ መጓዛችን እስከቀጠልን ድረስ የሊጋችን ደረጃ አለፍ ሲልም የብሔራዊ እግር ኳሳችንን እድገት ቀጣይነት ባለው መንገድ ማስቀጠል ፈታኝ መሆኑን ተረድተው ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት በተለይም የክለብ አመራሮች እና አሰልጣኞች ባለ አቅርቦት የመስራት እንዲሁም ተጫዋቾች በማሳደግ እና በማሻሻል ላይ የፀና እምነት በማሳደር በአዲስ ዓመት ከአዲስ ስብስብ ባለፈ አዳዲስ ሀሳቦችን እና መንገዶች የምንከተልበት ጊዜ እንዲመጣ ምኞታችን ነው።