ከፕሪምየር ሊግ ወደ ከፍተኛ ሊግ የወረደው ሰበታ ከተማ በቀድሞ ተጫዋቹ ክስ ከዝውውር እንቅስቃሴ እንዲታገድ ውሳኔ ተላልፎበታል።
ከ2012 ጀምሮ በኢትዮጵያ ከፍተኛው የሊግ እርከን ሲወዳደር የነበረው ሰበታ ከተማ ዓምና ከሊጉ ተሰናብቶ ወደ ከፍተኛ ሊግ መውረዱ ይታወቃል። ውድድር ላይም እያለ በተለያዩ የሜዳ ውጪ ጉዳዮች ስሙ ሲነሳ የነበረው ክለቡ ከሳምንታት በፊት የቀድሞ የቡድኑ ተጫዋቾች በነበሩት አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ፣ ዱሬሳ ሹቢሳ፣ በኃይሉ ግርማ፣ በረከት ሳሙኤል፣ ለዓለም ብርሃኑ፣ ፍፁም ገብረማርያም፣ ወልደአማኑኤል ጌቱ፣ ሳሙኤል ሳሊሶ፣ ገዛኸኝ ባልጉዳ፣ ዘላለም ኢሳይያስ እና ምንተስኖት አሎ ክስ ቀርቦበት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴ የዕግድ ውሳኔ አስተላልፎበት እንደነበር አይዘነጋም።
አሁን ደግሞ ሌላኛው የቀድሞ የክለቡ ተጫዋች ታፈሰ ሰርካ ከደሞዝ ጋር በተያያዘ ለፌዴሬሽኑ አቤቱታ አቅርቦ የዲሲፕሊን ኮሚቴው የተጫዋቹ ደሞዝ በየቀኑ ከሚታሰብ 2% ወለድ ጋር እንዲከፈለው ውሳኔ ቢሰጥም ክለቡ የተላለፈውን ውሳኔ ተግባራዊ ባለማድረጉ ከዛሬ ጀምሮ በተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ላይ እንዳይሳተፉ መወሰኑን የተጫዋቹን ጉዳይ ከያዙት የህግ ጠበቃ አቶ ብርሃኑ በጋሻው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።