የሊጉ ሁለት ክለቦች እና ስድስት ተጫዋቾች ተቀጥተዋል

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያው ሳምንት ጨዋታዎች ላይ በተፈፀሙ የዲሲፕሊን ግድፈቶች መነሻነት አክሲዮን ማህበሩ የቅጣት ወሳኔዎች አስተላልፏል፡፡

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ባሳለፍነው ዓርብ በባህር ዳር ጅምሩን አድርጓል፡፡ በሳምንቱ የውድድር ወቅት በታዩ የዲሲፕሊን ግድፈቶች ላይ የሊግ ካምፓኒው የውድድር አመራር እና ሥነ ስርዓት ኮሚቴ ከዳኞች እና ታዛቢዎች የቀረቡለትን ሪፖርቶች ከመረመረ በኋላ የተለያዩ የዲሲፕሊን ውሳኔዎችን አሳልፏል።

የድሬዳዋ ከተማው አማካይ ኤልያስ አህመድ ድሬዳዋ ከተማ ከሲዳማ ቡና ጋር ባደረገው ጨዋታ የዕለቱን ዋና ዳኛ ኤፍሬም ደበሌን አፀያፊ ስድብ በመሳድቡ በቀይ ካርድ ከሜዳ መወገዱ ይታወሳል፡፡ ተጫዋቹ በፈፀመው ድርጊትም 3 ጨዋታ እንዲታገድ እና 3 ሺህ ብር እንዲከፍል ሲደረግ በዚሁ ጨዋታ የሲዳማ ቡናው ተከላካይ ጊትጋት ጉት ፣ ፋሲል ከነማ ከአዳማ ከተማ ጋር ባደረገው ጨዋታ የፋሲሉ ሽመክት ጉግሳ በሁለተኛ ቢጫ ከሜዳ በመወገዳቸው እንዲሁም የአዳማው አማካይ ዊሊያም ሰለሞን በፋሲል ከነማ ተጫዋቾች ላይ ባሳየው አላስፈላጊ ድርጊት በሁለተኛ ቢጫ ካርድ በቀይ ካርድ በመውጣቱ ሦስቱም ተጫዋቾች የአንድ ጨዋታ ዕግድ ተላልፎባቸዋል፡፡

የድሬዳዋ ከተማው የመስመር ተከላካይ እንየው ካሳሁን ሲዳማ ቡና ላይ ጎል ካስቆጠረ በኋላ ኃይማኖታዊ መልዕክት በምስል በውስጥ ልብሱ ስለማሳየቱ ሪፖርት ስለተደረገበት ተጫዋቹ 3 ሺህ ብር እንዲሁም ክለቡ ደግሞ ብር 10 ሺህ ብር እንዲከፍሉ ተወስኗል። ወልቂጤ ከተማ አርባምንጭ ሲረታ የመስመር ተከላካዩ ሳሙኤል አስፈሪ ከተፈቀደው ውጪ 66 ቁጥርን ለብሶ በመገኘቱ 3 ሺህ ብር እንዲከፈል ተወስኗል፡፡

በክለብ ደረጃ ድሬዳዋ ከተማ አምስት ቢጫ ካርድ ተጫዋቾቹ በማየታቸው ክለቡ አምስት ሺህ ብር ሲቀጣ አዲስ አዳጊው ኢትዮጵያ መድን በቅዱስ ጊዮርጊስ ሽንፈት ባስተናገደበት ወቅት የክለቡ ተጫዋቾች ከዕረፍት መልስ ዘግይተው ወደ ሜዳ በመግባታቸው በክለቡ ላይ የ15 ሺህ ብር ቅጣት ተላልፏል፡፡ በተጨማሪም የውድድሩ የምስል መብት የሚመለከተው ዲኤስቲቪ አክሲዮን ማህበሩን የካሳ ክፍያ ከጠየቀ ክፍያውን ክለቡ እንደሚፈፅምም በቅጣቱ ተካቷል፡፡