ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | የ1ኛ ሳምንት ምርጥ 11

በመጀመሪያው ሳምንት የፕሪምየር ሊጉ ጨዋታዎች በአንፃራዊነት ደምቀው የወጡ ተጫዋቾችን በምርጥ ቡድናችን አስገብተናል።

የተጫዋቾች አደራደር ቅርፅ (3-4-3)

ግብ ጠባቂ

ቢኒያም ገነቱ – ድቻ

ዓምና በተለይ በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች የመሰለፍ ዕድል አግኝቶ ራሱን በሚገባ ያሳየው ቢኒያም የዘንድሮውንም የውድድር ዓመት በጥሩ ብቃት ላይ ሆኖ ጀምሯል። ቡድኑ ኢትዮጵያ ቡናን በገጠመበት ጨዋታም በአጠቃላይ 13 ሙከራዎች ተደርገውበት አንዱም ወደ ግብነት እንዳይቀየር አድርጎ ወጥቷል።

ተከላካዮች

ውሀብ አዳምስ – ወልቂጤ ከተማ

ለውሳኔ የማያመነታው ጋናዊው የመሐል ተከላካይ በአርባምንጩ ጨዋታ አብዛኛውን ደቂቃ ከኳስ ውጪ ሆኖ ሲጫወት ለነበረው ቡድን ጠንካራ መጋረጃ ሆኖ ነበር። እርግጥ አርባምንጭ እንደ ኳስ ቁጥጥሩ የጠራ የግብ ሙከራ ለማድረግ ባይበረታም ውሀብ የቡድኑ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾች በምቾት እንዳይጫወቱ በማድረግ የተዋጣለት ጊዜ አሳልፏል።

ተስፋዬ ታምራት – ባህር ዳር ከተማ

አዲሱ የጣና ሞገዶቹ የኋላ መስመር ተጫዋች ዋና ሥራው በሆነበት ሚናው እምብዛም ተጠምዶ ባይውልም ወሳኝ ሰዓት ላይ የቡድኑ አዳኝ ሆኖ ብቅ ብሏል። እርግጥ በመከላከል አጨዋወትም በግሉ ጥሩ ስራን ሲሰራ የተመለከትን ሲሆን እንደገለፅነው ቡድኑን ሦስት ነጥብ እንዲያገኝ ወሳኝ መነሻ የሆነች ጎል ባለቀ ሰዓት አስቆጥሯል።

መዝገቡ ቶላ – ለገጣፎ ለገዳዲ

አዲስ አዳጊው ለገጣፎ ለገዳዲ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በሊጉ ተሳትፎ ታሪካዊውን ድል ሀዋሳ ከተማ ላይ ሲቀዳጅ የኋላውን መስመር በሚደነቅ ብቃት ሲመራ የነበረው መዝገቡ ቶላ የምርጥ ቡድናችን ሌላኛው ተጫዋች ነው። ግዙፉን አጥቂ ሙጂብ ጨምሮ ፈጣኖቹን ዓሊ እና ኤፍሬም የማጥቃት እንቅስቃሴም ከአጋሮቹ ጋር በመሆን በአግባቡ ሲመክት ነበር።

አማካዮች

ቻርለስ ሪባኑ – ባህር ዳር ከተማ

ናይጄሪያዊው አማካይ ከኳስ ጋርም ከኳስ ውጪም ሲያደርግ የነበረው እንቅስቃሴ ያለከልካይ በምርጥ ቡድናችን ቦታ እንዲኖረው አድርጓል። ከተከላካዮች ፊት ሆኖ “ቆሻሻውን ሥራ” ሲሰራ የነበረው ሪባኑ በቡድኑ የኳስ ምስረታ ወቅትም መነሻ ሆኖ እዕድገት ያላቸው ኳሶችን ወደፊት ሲልክ ነበር።

ዳዊት ተፈራ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ዳዊት በአዲሱ ክለቡ እጅግ የተሳካ የመጀመሪያ የሊግ ጨዋታን በማሳለፉ በአማካይ መስመራችን አካተነዋል። ተጫዋቹ ለአጥቂ ክፍሉ ተጠግቶ እንዲጫወት ኃላፊነት ተሰጥቶት ወደ ሜዳ የገባ ሲሆን የእንቅስቃሴ ፈጣሪነቱን ዳግም በማስመስከር በክፍት ጨዋታ እና በቆመ ኳስ ሁለት ግብ የሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ አቀብሏል።

ቢኒያም በላይ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

በክረምቱ የዝውውር መስኮት ፈረሰኞቹን የተቀላቀለው ቢኒያም ቡድኑ ኢትዮጵያ መድንን ሲረታ አንድ ግብ ሲያስቆጥር አንድ ግብ የሆነ ኳስ አቀብሎ ቸርነት ላስቆጠረው የፍፁም ቅጣት ምትም መነሻ ሆኗል። በዋናነትም በቀኝ መስመር የቡድኑን የማጥቃት ኃይል መነሻ ሆኖ ሲንቀሳቀስ ነበር።

ቸርነት ጉግሳ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ለፍፁምነት የተጠጋ ብልጫ ወስዶ ቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮጵያ መድንን ሲረታ ሌላው በቡድኑ ደምቆ የታየው ተጫዋች የመስመር ተጫዋቹ ቸርነት ነው። ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመግባት የማይፈራው ቸርነት ለተጋጣሚ ተከላካዮች ፈተና ሆኖ ነበር። በጨዋታው በፍፁም ቅጣት ምት ቢሆንም ግብ ያስቆጠረ ሲሆን ለኦሮ አጎሮም ድንቅ ግብ የሆነ ኳስ አመቻችቶ ልኳል።

አጥቂዎች

ካርሎስ ዳምጠው – ለገጣፎ ለገዳዲ

ግዙፉ አጥቂ ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊጉ ሲመለስ በሁለት ግቦች ታጅቦ ነበር። በአየር እና በመሬት ላይ የአንድ ለአንድ ግንኙነቶች የበላይነት ሲወስድ የሚታየው ተጫዋቹ ለገጣፎ ሀዋሳን ባሸነፈበት ጨዋታ ልዩነት ፈጣሪ ሆኖ ታይቷል። በዋናነት ከአንድ ጥሩ አጥቂ የሚጠበቀውን የአጨራረስ እና ተስፋ ሳይቆርጡ አጋጣሚዎችን የመጠቀም ብቃትም አሟልቶ ግቦቹን በስሙ አስመዝግቧል።

እስማኤል ኦሮ አጎሮ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ቅዱስ ጊዮርጊስ አስተማማኙን ድል በሳምንቱ መጨረሻ ሲያገኝ የእስማኤል ኦሮ አጎሮ ብቃት እጅግ አስፈላጊ ነበር። ተቀይሮ እስከወጣበት 74ኛው ደቂቃ ድረስ የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት ማዕከል የነበረው አጎሮ በግራ እና በቀኝ እግሩ በጨዋታው ሦስታ በመስራት የቡድኑን የውድድር ዓመት በድንቅ አጀማመር ከፍቷል።

ፍቃዱ ዓለሙ – ፋሲል ከነማ

ዐፄዎቹ በርከት ያሉ የግብ ምንጮቻቸውን በክረምቱ የዝውውር መስኮት ቢያጡም አሁንም ጨራሽ የሳጥን ውስጥ አጥቂ እንደሆነ በሚያገኛቸው ዕድሎች የሚያሳየው ፍቃዱ በዚህም ሳምንት የቡድኑ አስፈላጊው ተጫዋች ነበር። በቦታ አጠባበቁ፣ አጨራረሱ እና ታጋይነቱ የሚታወቀው ፍቃዱ ቡድኑን አሸናፊ ያደረጉ ሁለት ግቦችንም በስሙ አስመዝግቧል።

አሠልጣኝ ጥላሁን ተሾመ – ለገጣፎ ለገዳዲ

በተለያየ የኃላፊነት መዋቅር ክለቡን ያገለገሉት አሠልጣኝ ጥላሁን ለገጣፎ ለገዳዲ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲያድግ አድርገውት በመጀመሪያው የሊጉ ጨዋታ ቡድናቸውን አዋቅረው ወደ ሜዳ ያስገቡበት መንገድ የሚያስደንቃቸው ነው። እርግጥ በጨዋታ ሳምንቱ የፈረሰኞቹ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታም ቡድናቸው እጅግ ብልጫ ወስዶ የረታበት ፍልሚያ ቢኖርም በአዲሱ መድረክ ቡድናቸውን በሁሉም የጨዋታ ምዕራፍ በሚገባ አዘጋጅተው የቀረቡትን አሠልጣኝ ጥላሁን የሳምንቱ ምርጥ አሠልጣኝ አድርገን መርጠናል።

ተጠባባቂዎች

ፔፔ ሰይዶ – ሀዲያ ሆሳዕና
እንየው ካሳሁን – ድሬዳዋ ከተማ
ሄኖክ አዱኛ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
በረከት ወልዴ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ስንታየሁ ዋለጬ – ኢትዮ ኤሌክትሪክ
ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ – ፋሲል ከነማ
ዱሬሳ ሹቢሳ – ባህር ዳር ከተማ
ጌታነህ ከበደ – ወልቂጤ ከተማ

ያጋሩ