የሁለተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ነገ ከሚደረጉ ጨዋታዎች በፊት ሊያውቋቸው የሚገቡ ጉዳዮችን እንደሚከተለው አሰናድተናል።

ባህር ዳር ከተማ ከ ወልቂጤ ከተማ

የዘንድሮው የውድድር ዘመን መክፈቻ በሆነው የጨዋታ ዕለት ድል ያጣጣሙት ሁለቱ ቡድኖች እርስ በርስ በመገናኘት ሁለተኛውን ሳምንት ይጀምራሉ። ኢትዮ ኤሌክትሪክን ከኋላ በመነሳት መርታት የቻሉት ባህር ዳሮች በቡድን ውህደት በኩል ይበልጥ መሻሻል እንደሚያስፈልጋቸው የሚጠቁም ጨዋታ ቢያደርጉም ጨዋታውን በድል ማጠናቀቅ መቻላቸው ለቀጣይ ጉዟቸው እጅግ ወሳኝ እንደሚሆንላቸው ይጠበቃል። በደጋፊው ፊት ቀዳሚዎቹን ሳምንታት የመጫወት ዕድሉን ያገኛው ባህር ዳር ከተማ በተለይም ከአዲስ ፈራሚዎቹ ቻርለስ ሪባኑ ፣ ተስፋዬ ታምራት እና ዱሬሳ ሹቢሳ የተመለከተውን መልካም አጀማመር በነገውም ጨዋታ ይጠብቃል። አምበላቸው ጌታነህ ከበደ ዛሬም እንደትናንቱ ጎል ከማስቆጠር እንደማይሰንፍ ማሳያ የሆነ ቀዳሚ ጨዋታ ያደረጉት ሰራተኞቹ በርካታ ለውጦች አድርገው ቢመጡም ከተጋጣሚያቸው አርባምንጭ ከተማ የተሻለ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ታይተዋል። የኳስ ቁጥጥርን ምርጫው ያደረገው የአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ቡድን በዛ ጨዋታ ግብ ሳያስቆጥር መውጣት መቻሉም ለነገው ጨዋታ ጥሩ ስንቅ እንደሚሆነው ይገመታል።

የቡድን ዜናዎችን ስንመለከት የባህር ዳር ከተማዎቹ ያሬድ ባዬ እና ፈቱዲን ጀማል ያላገገሙ ሲሆን በረከት ጥጋቡ እንዲሁም የመጀመሪያ ጨዋታ ላይ የተሰለፉት ሀብታሙ ታደሰ እና ጉዳት ገጥሞት የወጣው ፍቅረሚካኤል ዓለሙ ለነገው ጨዋታ አይደርሱም። በወልቂጤ በኩል በመጀመሪያው ጨዋታ ጉዳት ገጥሞት የወጣው ጌታነህ ከበደ አገግሞ ለነገው ጨዋታ እንደሚደርስ ሲገልፅ ቀሪው የቡድኑ ስብስብም ሙሉ ጤናነት ላይ ይገኛል።

ወልቂጤ እና ባህር ዳር ከዚህ ቀደም አራት ጊዜ ተገናኝተዋል። በግንኙነታቸውም ዕኩል አንድ አንድ ጊዜ ተሸናንፈው ሁለት ጊዜ አቻ ወጥተዋል። በአራቱ ጨዋታዎች ወልቂጤ አራት ባህር ዳር ደግሞ አምስት ግቦች አስቆጥረዋል።

ጨዋታው በኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ ፣ መሪነት የሚከናወን ሲሆን በረዳትነት ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ይበቃል ደሳለኝ እና ሻረው ጌታቸው ሲመደቡ ሌላኛው ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ አራተኛ ዳኛ ሆነዋል።

አርባምንጭ ከተማ ከ ኢትዮጵያ መድን

የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ከመጀመሪያው በተቃራኒ ከሽንፈት የተመለሱ ቡድኖች የሚገናኙበት ነው። አዞዎቹ በጠባብ ውጤት በተሸነፉበት የመጀመሪያ ጨዋታ በ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተመራጭ የነበሩ ተጫዋቾቻቸውን የሙሉ ሰዓት የመሰለፍ ዕድል ያልሰጡ ሲሆን ከዚህ ቀደም የነበረው የቡድኑ የውህደት ደረጃ በተወሰነው የጨዋታ ክፍል ላይ ቀንሶ ታይቷል። የአሰልጣኝ መሳይ ቡድን ነገ በተሻለ መልኩ ወደ ቀደመ ጠጣርነቱ ተመልሶ መምጣትም ይጠበቅበታል። በሊጉ በታሪክ ከሚጠቀሱ ሰፊ የግብ ልዩነት ከታየባቸው ጨዋታዎች የሚመደብ ሽንፈት ያገኛቸው ኢትዮጵያ መድኖች አጀማመራቸው አላማረም። ነገ ቡድኑ በሥነ ልቦናው ራሱን አድሶ እና በጉዳት የሳሳው የተከላካይ ክፍሉን በተሻለ መልኩ በማደስ ከአዞዎቹ ጋር እንደሚፋለም ይጠበቃል።

አርባምንጭ ከተማ ጉዳት ላይ የሰነበቱት ተጫዋቾቹ በላይ ገዛኸኝ እና አንድነት አዳነ እያገገሙ ቢግኙም ለነገው ጨዋታ የማይደርሱ ሲሆን አጥቂው ኤሪክ ካፓይቶም ልምምድ ላይ መጠነኛ ጉዳት ገጥሞታል። በኢትዮጵያ መድን በኩል ባለፈው ከነጉዳቱ ተቀይሮ የገባው ፀጋሰው ድማሙ ጉዳቱ ያገረሸበት በመሆኑ መሰለፉ አጠራጣሪ ሲሆን በተመሳሳይ ባለፈው ከጉዳት ጋር ተቀይሮ በመግባት ጥሩ የተንቀሳቀሰው ኪቲካ ጀማ ከጉዳት ሙሉ ለሙሉ አገግሟል። ለኢትዮጵያ መድን መልካም በሆነ ሌላ ዜና ቴዎድሮስ በቀለ ወደ ሜዳ እንደሚመለስ ሲጠበቅ የክለቡ የውጪ ዜጋ ፈራሚዎች ግን ለነገውም ጨዋታ እንደማይደርሱ ታውቋል።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በሊጉ በተጋናኙባቸው አራት አጋጣሚዎች በአስገራሚ ሁኔታ አራቱንም አቻ ሲለያዩ ሦስቱ ጨዋታዎች ያለ ግብ ነበር የተጠናቀቁት።

ለዚህ ጨዋታ በዋና ዳኝነት የተመደቡት እያሱ ፈንቴ ሲሆኑ በረዳትነት ሲራጅ ኑርበገን እና እሱባለው መብራቱ እንዲሁም አራተኛ ዳኛ በመሆን ኤፍሬም ደበሌ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል።

ያጋሩ