ዐፄዎቹ አጥቂ አስፈርመዋል

የዝውውር መስኮቱ መስከረም 20 ከመዘጋቱ በፊት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስሙ ተመዝግቦ የነበረው የከፍተኛ ሊግ የምድብ ሐ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪው በዛሬው ዕለት በይፋ የፋሲል ከነማ ተጫዋች ሆኗል፡፡

የ2015 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድሩን አዳማ ከተማን በመርታት በድል የጀመሩት ዐፄዎቹ በያዝነው ሳምንት ከቱኒዚያው ክለብ ሴፋክሲያን ጋር ላለበት የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የሁለተኛ ዙር የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ የተነሳ የሁለተኛ ሳምንት የሊጉን መርሐ-ግብር የማያደርግ ሲሆን ራሱን ለማጠናከር ግን በዛሬው ዕለት በይፋ የአንድ ተጫዋችን ዝውውር ፈፅሟል፡፡ በዚህም አጥቂው ጉልላት ተሾመ አዲሱ የዐፄዎቹ ፈራሚ በመሆን ክለቡን ተቀላቅሏል፡፡

ከቀናቶች በፊት ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለማምራት ከጫፍ ደርሶ የነበረው የቀድሞው የኢትዮጵያ መድን የታዳጊ እና የዋናው ቡድን አጥቂ የሆነው ጉልላት የተጠናቀቀውን የውድድር ዘመን በከፍተኛ ሊጉ ምድብ ሐ ለአቃቂ ቃሊቲ ተሰልፎ በመጫወት ስምንት ጎሎችን ከመረብ ያሳረፈ ሲሆን የዝውውሩ መስኮቱ ባሳለፍነው ዓርብ መስከረም 20 ከመጠናቀቁ በፊት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ስሙ ተመዝግቦ የነበረ በመሆኑ የወረቀት ስራዎችን አጠናቆ በአንድ ዓመት ውል በዛሬው ዕለት መዳረሻው ፋሲል ከነማ ሆኗል፡፡

ያጋሩ