የሁለተኛው ሳምንት ቀዳሚ በነበረው ጨዋታ የተመስገን በጅሮንድ ድንቅ ጎል ወልቂጤ ከተማ ባህር ዳር ከተማን 1-0 እንዲያሸንፍ አድርጋለች።
ተጋጣሚዎቹ ወደ ሜዳ ከገቡ በኋላ አስቀድሞ የባህር ዳር ከተማ ቡድን አባላት ለቀድሞው አሰልጣኛቸው ማስታወሻ የሚሆን የላብቶፕ እና የምስል ማስታወሻ ስጦታ አበርክተዋል። ጨዋታው ከመጀመሩ አስቀድሞ ደግሞ ለቀድሞው የባህር ዳር ከተማ ከንቲባ እና የክለቡ ፕሬዘዳንት ለነበሩት አቶ ሙሉቀን አየሁ የህሊኒ ፀሎት ተደርጓል።
ባህር ዳር ከተማ ኢትዮ ኤሌክትሪክን ካሸነፈበት ስብስብ ውስጥ ፋሲል ገብረሚካኤል ፣ ማሳይ አገኘው እንዲሁም ጉዳት የገጠመማቸው ፍቅረሚካኤል ዓለሙ እና ሀብታሙ ታደሰን በቴፒ አልዛየር ፣ ሳለአምላክ ተገኘ ፣ አለልኝ አዘነ እና ፍፁም ዓለሙን ተክተዋል። በወልቂጤ ከተማ በኩል በተደረጉ ሁለት ለውጦች ደግሞ ጀማል ጣሰው በፋሪስ አለዊ እንዲሁም ፋሲል አበባየሁ ብዙአየሁ ሰይፈ ምትክ ጨዋታውን ጀምረዋል።
የመጀመሪያው አጋማሽ በአመዛኙ የተመጣጠነ ፉክክርን ቢያስመለክተንም የግብ ዕድሎች በብዛት የተፈጠሩበት አልነበረም። በኳስ ቁጥጥሩ እና በማጥቃት ሂደት መጠነኛ ብልጫ የነበራቸው ባህር ዳር ከተማዎች ዱሬሳ ሹቢሳ እና ኦሴይ ማዉሊን ያነጣጠሩ ጥቃቶችን ለመሰንዘር ሞክረዋል። የተጋጣሚያቸውን ጥቃት በማቋረጥ ጥሩ ሴኬት ያሳዩት እና ፈጠን ባለ ጥቃት ወደ ቀኝ መስመር ባደላ እንቅስቃሴ ምላሽ ለመስጠት ይሞክሩ የነበሩት ወልቂጤዎችም ወደ ባህር ዳር ሳጥን የደረሱባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ።
ሆኖም በአጋማሹ የታዩት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች በቁጥር ሁለት ነበሩ። ዱሬሳ ሹቢሳ ሳለአምላክ ተገኘ 23ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ተቆጣጥሮ ወደ ግብ ሲሞክር ግብ ጠባቂው ጀማል ጣሳው ሲያድንበት በድጋሚ ሲሞክር ደግሞ ከዳኛ እይታ ውጪ ቢሆንም ኳስ በውሀብ አዳምስ እጅ ልትመለስ ችላለች። በወልቂጤዎች በኩል ደግሞ 35ኛ ደቂቃ ላይ ተመስገን በጅሮንድ ከቀኝ መስመር ወደ ውስጥ በመሬት ባደረሰው ኳስ ጌታነህ ከበደ ነፃ የማግባት ዕድል ቢያገኝም ባልተጠበቀ ሁኔታ ያደረገው ሙከራ ወደ ውጪ ወጥቷል።
ከዕረፍት እንደተመለሱ ባህር ዳሮች ፈጣን አጀማመር አድርገዋል። በኦሴይ ማዉሊ እና አለልኝ አዘነ በተከታታይ ጎል ለማስቆጠር ሲቃረቡ 49ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ሳለአምላክ ከቀኝ ካሻገረው ኳስ ዱሬሳ ሹቢሳ በቀጥታ ያደረገው ሙከራ በጀማል ጣሰው የዳነ ነበር። ነገር ግን ሰራተኞቹ የጣና ሞገዶቹን አጀማመር በማርገብ ወደ ጨዋታው ምት በገቡበት አጋጣሚ አስደናቂ ግብ አስቆጥረዋል። የቀኝ መስመር አጥቂው ተመስገን በጅሮንድ ከሳጥን ውጪ ሁለቴ ገፍቶ አክርሮ የመታው ይህ ኳስ 60ኛው ደቂቃ ላይ በባህር ዳር መረብ ላይ አርፏል።
ቀጣዮቹ ደቂቃዎች ጨዋታው ለዓይን መራኪ የሆነባቸው ነበሩ። ባህር ዳር ከተማዎች አቻ ለመሆን የማጥቃት ጫናቸውን ቢጨምሩም ወልቂጤዎችም ከማፈግፈግ ይልቅ በፈጣን ጥቃት ወደ ሳጥን ይደርሱ የነበረበት መንገድ በሁለቱም ጎሎች ከባባድ ሙከራዎችን አሳይቶናል። 65ኛው ደቂቃ ላይ ጌታነህ ከበደ ከጥልቅ አማካይ ስፍራ ላይ ተቀይሮ የገባው ብዙአየሁ ሰየፈ በረጅሙ ያደረሰውን ኳስ ሳጥን ውስጥ በሰውነቱ ሸፍኖ ከቀኝ የሞከረበት አጋጣሚ የወልቂጤን መሪነት ለማስፋት ተቃርቦ ነበር። ከአንድ ደቂቃ በኋላ ደግሞ በተቃራኒው ተቀይሮ የገባው አደም አባስ በግራ ሳጥን ውስጥ ደርሶ ሳሙኤል አስፈሪን አልፎ አክርሮ የመታው ኳስ በጀማል ተመልሷል።
የመጨረሻዎቹ 20 ደቂቃዎች ወልቂጤ ከተማዎች ፈጣን የማጥቃት ሽግግራቸውን ረገብ አድርገው ውጤት የማስጠበቅ እንቅስቃሴ ላይ ያመዘኑበት ነበር። ባህር ዳሮች በተለይም ከዱሬሳ አቅጣጫ በሚሰነዘሩ ጥቃቶች አቻ ለመሆን ያደረጉት ጥረት ከሳጥን ውጪ በሚደረጉ ሙከራዎች ተገድቦ ያሰቡትን ሳያሳኩ ጨዋታው በሰራተኞቹ አሸናፊነት ተቋጭቷል።
ከጨዋታው መጠናቀቀ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች መሸነፍ እንዳልነበረባቸው እና በመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታውን መጨረስ ይችሉ እንደነበር የገለፁት አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው በተጫዋቾቻቸው ጥረት መደሰታቸውን አንስተው የአጨራረስ ችግር እንደታየባቸው ተናግረዋል። አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ በበኩላቸው ከዕረፍት በኋላ ያደረጉት ማስተካከያ እንዳገዛቸው በማንሳት ሚዛናዊ ጨዋታ ማድረጋቸውን በተለይም የማጥቃት ሽግግር ላይ ማተኮራቸው ውጤታማ እንዲሆኑ እንዳደረጋቸው ጠቁመዋል።