የሁለተኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች

በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ሁለት ጨዋታዎች ዙሪያ ተከታዮቹን መረጃዎች አሰባስበናል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

በመጀመሪያው ሳምንት በቅደም ተከተል ሽንፈት እና ድል ያገኙት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች እና ቅዱስ ጊዮርጊሶች ነገ 7 ሰዓት የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል። ሊጉ በአዲስ መልክ 1990 ላይ ሲመሰረት ሻምፒዮን የሆነው ኤልፓ ከወቅቱ የሊጉ ባለድል ጊዮርጊስ ጋር በሚያደርገው የነገ መርሐ-ግብርም ጥሩ ፉክክር እንደሚደረግ ይጠበቃል። ከአራት ዓመታት በኋላ ሊጉን የተቀላቀለው ኤሌክትሪክ በመጀመሪያው ሳምንት በባህር ዳር ከተማ እየመራ ቢሸነፍም ለክፉ የሚሰጥ ብቃት አላሳየም። እርግጥ ቡድኑ ከኳስ ጋር ጊዜ የሚያሳልፍ ቢሆንም የግብ ማግባት ሙከራዎችን በአጥጋቢ ሁኔታ የመፍጠር ክፍተት ግን አለበት። በነገው ጨዋታም ጠንካራውን ቅዱስ ጊዮርጊስ ለማሸነፍ ይህን ክፍተት መሻሻል ይገባዋል። በተቃራኒው የመጀመሪያ የሊግ ጨዋታቸውን እጅግ አስተማማኝ በሆነ የ7ለ1 ውጤት ያሸነፉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች እንከን አልባ የነበረው የመድን ጨዋታቸው ለመድገም ነገ ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይታሰባል። በተለይ ደግሞ ከተለያዩ ቦታዎች ያላቸውን የጎል ምንጭ ነገም ኤልፓ ላይ ለማሳየት የሚያደርጉት ጥረት ይጠበቃል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ የመጀመሪያ ድሉን ለማግኘት በሚሞክርበት የነገ ጨዋታ በጉዳት እና ቅጣት ምክንያት የሚያጣው ተጫዋች የለም። ቅዱስ ጊዮርጊስ በበኩሉ የመስመር አጥቂው አቤል ያለው ልምምድ ቢጀምርለትም በነገው ጨዋታ ግን እንደማይደርስለት ተገልጿል። ከአቤል ውጪ ግን ሁሉም ተጫዋቾች በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ተጠቁሟል።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም 38 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 26 በማሸነፍ የበላይነተን ሲይዝ ኤሌክትሪክ 3 አሸንፎ በ9 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ 65 ግቦች ሲያስቆጥር ኤሌክትሪክ በበኩሉ 28 አስቆጥሯል።

ይህንን ጨዋታ ባህሩ ተካ ከረዳቶቹ ሙስጠፋ መኪ እና ወጋየሁ አየለ እንዲሁም አራተኛ ዳኛው ኤፍሬም ደበሌ ጋር በመሆን ይመራዋል።

ለገጣፎ ለገዳዲ ከ ድሬዳዋ ከተማ

በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በሊጉ እየተሳተፉ የሚገኙት ለገጣፎ ለገዳዲዎች የምስራቁን ክለብ ድሬዳዋ ከተማ ነገ 10 ሰዓት ይገጥማሉ። በመጀመሪያ ጨዋታቸው ሳይጠበቅ እየተመሩ ሀዋሳ ከተማን ሁለት ለአንድ ያሸነፉ ሲሆን በነገው ጨዋታም ተከታታይ ድል አግኝቶ ለመጓዝ እንደሚጥሩ ይታመናል። በመከላከልም ሆነ በማጥቃት በህብረት ለመጫወት የሚሞክረው ቡድኑ ነገም የካርሎስ ዳምጠውን ምህታት በመጠቀም ሦስት ነጥብን እያለመ ጨዋታውን ይቀርባል። በተቃራኒው ከሲዳማ ቡና ጋር አቻ ተለያይተው የነገውን ጨዋታ የሚቀርቡት ድሬዳዋ ከተማዎች ሁነኛ አጥቂ እስካሁን ባያገኙም በአማካይ እና ተከላካይ ተጫዋቾቻቸው ጎሎችን አግኝተዋል። ከኳስ ጋርም ሆነ ከኳስ ውጪ ታታሪ የሆነው ቡድኑ ይሄንን የፊት መስመር ክፍተት በምን ያህል ደረጃ አሻሽሎ በነገው ጨዋታ ይቀርባል የሚለውም ዋነኛ ተጠባቂ ጉዳይ ነው።

ለገጣፎ ለገዳዲዎች በነገው ጨዋታ በጉዳትም ሆነ በቅጣት ምክንያት የሚያጡት ተጫዋች የሌለ ሲሆን ድሬዳዋ ከተማዎች ግን አቤል ከበደን በጉዳት ኤሊያስ አህመድን ደግሞ በቅጣት ምክንያት አይጠቀሙም። ብርቱካናማዎቹ በአማራ ባንክ ጣና ዋንጫ ውድድር ላይ ተመልክተውት ያስፈረሙት ዩጋንዳዊው አጥቂ ሙሲጊ ቻርለስ የወረቀት ጉዳዮቹ ስለተገባደዱለት በነገው ጨዋታ መሰለፍ እንደሚችል ተመላክቷል።

ኢንተርናሽናል ዳኛ ማኑሄ ወልደፃዲቅ ሁለቱ ቡድኖች በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በሊጉ የሚገናኙበትን ጨዋታ በመሀል አልቢትርነት ሲመራው ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ተመስገን ሳሙኤል እና ሰለሞን ተስፋዬ በረዳትነት እንዲሁም ተካልኝ ለማ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት የሚሳተፉ ይሆናል።

ያጋሩ