ወላይታ ድቻ በነበረው ስያሜ ይቀጥላል

ብዙ ውዝግብ አስነስቶ የቆየው የወላይታ ዲቻ ስያሜ ለውጥ ጉዳይ መፍትሔ ያገኘ ይመስላል።

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን የብሔር እና ኃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው ስያሜዎችን የሚጠቀሙ ክለቦች ስያሜያቸውን እንዲያስተካክሉ መመሪያ ማውጣቱ ይታወሳል።

በዚህ መሠረት ከዚህ ቀደም “ወላይታ ድቻ ስፖርት ክለብ” በሚል ይጠቀምበት የነበረውን መጠርያ ወደ “ድቻ ስፖርት ክለብ” ስለመለወጡ ክለቡ ለፌደሬሽኑ በደብዳቤ ማሳወቁን ተከትሎ ይፋዊ መረጃ መሰራጨቱ ይታወቃል።

ሆኖም ግን ይህ መረጃ ከወጣበት ጊዜ አንስቶ በክለቡ ሥራ አስኪያጅ በኩል ምንም ዓይነት የስያሜ ለውጥ አለመደረጉን እና መረጃው የተሳሳተ መሆኑ ሲያስተባብሉ ቢቆዩም የክለቡ ቦርድ ትናንት ባደረገው አስቸኳይ ስብስባ ሥራ አስኪያጁን ከኃላፊነታቸው በማንሳት በምትካቸው አቶ ምትኩ ኃይሌን በጊዜያዊ ሥራ አስኪያጅነት ተክቷል። ከቦርዱ እውቅና ውጪ ወደ ፌዴሬሽኑ የደረሰውን የስም ለውጥ በመሻርም ለእግርኳሱ የበላይ አካል ሌላ ደብዳቤ አስገብቷል።

ሶከር ኢትዮጵያ አሁን ባገኘችው መረጃ መሰረት ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የስያሜ ለውጡን የሚሽረው ደብዳቤ እንደደረሰው እና የዘንድሮ የፕሪምየር ሊግ የክለቦች ስያሜ ምዝገባ ተደርጎ በመጠናቀቁ ክለቡ በቀድሞ መጠርያው “ወላይታ ድቻ ስፖርት ክለብ” በሚለው ስያሜው እንደሚቀጥል አረጋግጣለች።