በሁለተኛው አጋማሽ የተቆጠሩ ሁለት ግቦች ለገጣፎ ለገዳዲ እና ድሬዳዋ ከተማን ነጥብ አጋርተዋል።
የለገጣፎ ለገዳዲው አሰልጣኝ ጥላሁን ተሾመ ሀዋሳን ካሸነፉበት አሰላለፍ አንድ ለውጥ ሲያደርጉ ተፈራ አንለይ በየአብቃል ፈረጃ ምትክ ጨዋታውን ጀምሯል። ከሲዳማው አቻ አንፃር በድሬዳዋ ከተማ በኩል በተደረጉ ለውጦች ደግሞ እያሱ ለገሰ ፣ ጋዲሳ መብራቴ እና አዲሱ አጥቂ ቻርለስ ሙሴልጌ ቅጣት ያለበት አህመድ ኤልያስ ፣ አማረ በቀለ እና ጋዲሳ መብራቴን ተክተው በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ተካተዋል።
በመጀመሪያዎቹ 10 ደቂቃዎች ካርሎስ ዳምጠው ከቅጣት ምት ባደረገው ሙከራ እንዲሁም አብዱለጢፍ መሐመድ በፈጣን መልሶ ማጥቃት በግራ መስመር ገብቶ በፈጠረው ዕድል የተነቃቃ አጀማመር የነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ታይቶበታል። ተደጋጋሚ የቆሙ ኳስ ዕድሎች ይታዩበት በነበረው ጨዋታ 15ኛው ደቂቃ ላይ ቻርለስ ሙሴንጌ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታው እና ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣው ኳስ ቀዳሚው አደገኛ የግብ ሙከራ ነበር።
የለገጣፎ ለገዳዲን የኳስ ምስረታ ሂደት አደገኛ ዞኖች ላይ እንዳይደርስ በማድረጉ የተሻለ የተንቀሳቀሱት ድሬዎች የመስመር ጥቃት ላይ በማተኮር ወደ ሳጥን ያደርሷቸው የነበሩ ኳሶች ያሰቡትን ያህል አደገኛ መሆን አልቻሉም። ከቅጣት ምት መነሻቸውን ባደረጉ ኳሶችም ቡድኑ በቢኒያም ጌታቸው እና እንየው ካሳሁን ዕድሎችን መፍጠር ችሎ ነበር።
35ኛ ደቂቃ ላይ አብዱለጢፍ መሐመድ ከማዕዘን ምት ያሻገረው ኳስ የድሬ ለግብ የቀረበ የጎል ዕድል ሆኖ ሲታይ ቢኒያም ጌታቸው ግልፅ አጋጣሚ ቢያገኝም በግንባሩ አምክኗታል። በለገጣፎ በኩል የቡድኑ የኳስ ንክኪዎች የሰመሩበት አጋጣሚ 41ኛ ደቂቃ ላይ ሲታይ ከመሀል ያቋረጡትን ኳስ ኦኬይ ጁል አድርሶት የአጥቂ አማካዩ ተፈራ አንለይ ተከላካዮችን በማለፍ ድንቅ ኳስ ቢያደርሰውም ብሩክ ብርሀኑ ከቀኝ ደርሶ ያደረገው ሙከራ ወደ ውጪ ወጥቷል።
ከዕረፍት መልስም የቆሙ ኳሶች መበራከት የቀጠለበት እንቅስቃሴ ታይቷል። ከእነዚህ ውስጥ 50ኛው ደቂቃ ላይ ድሬዎች ከቀኝ በቶሎ በጀመሩት ቅጣት ምት እንየው ካሳሁን ከሳጥን ውጪ ጥሩ ሙከራ አድርጓል።
የቆሙ ኳሶቹ ጋብ ሲሉ የለገጣፎ ለገዳዲ የማጥቃት ሂደት እየጎላ ሲመጣ በአንፃሩ ድሬዳዋ ከተማዎች ወደ ፊት የሚያዳርሷቸው ኳሶች ቁጥር ተመናምኗል።
በለገጣፎ በኩል 62ኛው ደቂቃ ላይ ኦኬይ ጁል በድሬዳዋ ሳጥን አቅራቢያ የነጠቀውን ኳስ አድርሶት ብሩክ ብርሀኑ በግራ ሳጥን ውስጥ ግልፅ ዕድል አግኝቶ ደካማ ሙከራ አድርጓል። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ ለገጣፎዎች በቀኝ የድሬዳዋ ሳጥን አቅራቢያ ያገኙትን አጋጣሚ ግን ወደ ውጤት ለውጠውታል። የድሬዳዋ ተከላካዮች በተዘናጉበት ቅፅበት በቀኝ የዳዊት ቀለመወርቅ እና ተፈራ አንለይ አንድ ሁለት ቅብብል ሰምሮ ተፈራ ኳስ ይዞ ግብ አፋፍ በመድረስ እያሱ ለገሰን አታሎ ያወጣለትን ኦኬይ ጁል ደርሶ 67ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ አገናኝቶታል።
ከግቡ በኋላ ድሬዎች የማጥቃት ኃይላቸውን ጨምረው ቢጫወቱም ለለገጣፎ መልሶ ጥቃት የተመቻቹ ሆነው ታይተዋል። ነገር ግን ጣፎዎች ውጤት ከማስጠበቅ ይልቅ ማጥቃታቸውን ቀጥለው በነበረበት ሰዓት ድሬዳዋዎች በድንገት የአቻነት ግብ አግኝተዋል። እንየው ካሳሁን ከቀኝ መስመር በረጅሙ ወደ ሳጥን የላከውን ኳስ ለማግኘት አብረው የዘለሉት የድሬዳዋ ተጫዋቾች ተቀይሮ የገባው አድናን መኪ በግንባሩ ሲጨርፈው እና ቻርለስ ሙሴልጌም በተመሳሳይ በግንባሩ ሲገጭ ኳስ 83ኛ ደቂቃ ላይ በጣፎ መረብ ላይ ወጥቷል።
በተቀሩት ደቂቃዎች ሁለቱም አሸንፈው ለመውጣት ፈጣን ጥቃት ለመሰንዘር ቢጥሩም ካርሎስ ዳምጠው 88ኛው ደቂቃ ላይ ካደረገው ኢላማውን የጠበቀ የቅጣት ምት ሙከራ ውጪ ሌላ ግብ ሳይቆጠር ጨዋታው 1-1 ተጠናቋል።
በዚህም መሰረት ለገጣፎ ለገዳዲ አራተኛ ነጥቡን ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ ተከታታይ አቻ በማስመዝገብ ሁለቱም ያለሽንፈት ወደ ሦስተኛ ሳምንት ጨዋታዎቻቸው አምርተዋል።
አሰልጣኞች በሰጡት አስተያየት ጨዋታው ጠንካራ እንደሚሆን ጠብቀው እንደነበር የገለፁት አሰልጣኝ ጥላሁን ተሾመ በሊጉ ፉክክሩ ተመጣጣኝ ቢሆንም የልምድ ችግር እንዳለ ሆኖም እስከሰባተኛ ደረጃ መጨረስ የሚያስችላቸው ስለመሆኑ ጠቁመዋል። በተመሳሳይ ጨዋታው ጥሩ እንደነበር ያነሱት አሰልጣኝ ዮርዳኖስ አባይ በበኩላቸው አሁንም ጠንካራ ቡድን እንዳላቸው እንደሚያምኑ ሆኖም ሜዳ ላይ መረጋጋት ማጣታቸው ጨዋታውን በመጀመሪያው አጋማሽ ጨርሰው እንዳይወጡ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።