ሴካፋ | የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከምድብ የወደቀበት ውጤት ከተመዘገበ በኋላ የተሰጠ የድህረ- ጨዋታ አስተያየት

👉”እውነት ለመናገር አንደኛ እና ሁለተኛ ሳይሆን ሦስተኛ ምርጫችንን ነበር ይዘን ወደ ውድድር የገባነው” ታዲዮስ ተክሉ

👉”ስም ባልጠራም ከአንድ ክለብ 8 ተጫዋቾችን መርጠን 7ቱ በእድሜ ወድቀው ነበር” ታዲዮስ ተክሉ

👉”ታንዛኒያዎች የስራቸውን ነው ያገኙት” ታዲዮስ ተክሉ

👉”ተጫዋቾቹ ወደፊት ሥራ ቢሰራባቸው ጥሩ አቅም ያላቸው ስለሆነ እንደነታንዛኒያ ትልቅ ደረጃ መድረስ ይቻላል” ታዲዮስ ተክሉ


👉”የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የጨዋታ መንገድ አጫጭር ኳሶችን ማብዛት ነው ፤ ይህንንም ተከትሎ አግሬሲቭ ለመሆን ሞክረናል” ኪም ፖልሰን

በአልጄሪያ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ላይ ለማለፍ የሴካፋ የማጣሪያ ውድድር በመዲናችን አዲስ አበባ እየተደረገ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከሱማሊያ ጋር አከናውኖ አንድ ለምንም የተሸነፈ ሲሆን ዛሬ ደግሞ ሁለተኛ ጨዋታውን ከታንዛኒያ ጋር አድርጎ 3ለ2 በመሸነፍ ወደ ግማሽ ፍፃሜ የማለፍ ዕድሉ መክኗል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላም የሁለቱ ቡድን አሠልጣኞች ተከታዩን የድህረ-ጨዋታ አስተያየት ለብዙሃን መገናኛ አባላት ሰጥተዋል።

አሠልጣኝ ታዲዮስ ተክሉ – ኢትዮጵያ

ስለጨዋታው…?

ጨዋታው ትንሽ ጠንከር ያለ ነበር። እኛ አስበን የመጣነውን ታክቲክ በመተግበር ረገድ ከታንዛኒያ የመጣብን ከፍተኛ ጫና እየተቆራረጠ ነበር። ኳሱን ተጫውተን ለመውጣት ስንሞክር ይቆራረጥብን ነበር። መጀመሪያ ላይ በ3-5-2 ለመጫወት ሞክረን ነበር ፤ ግን ከ15ኛው ደቂቃ በኋላ ይሄ እንደማያዋጣን ስናቅ ወደምናውቀው 4-3-3 ተመልሰን ጨዋታውን አከናውነናል። ጨዋታው ጥሩ ፉክክር የታየበት ነው። ታንዛኒያዎችም እድለኛ ሆነው የመጀመሪያውን የጎል ቅድሚያ ባልጠበቅንበት መንገድ አግኝተው የተወሰነ ብልጫ ለመያዝ ሞክረዋል። ያም ሆነ ይሂ ጨዋታው ጥሩ ፉክክር ተደርጎበት በታንዛኒያ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከሱማሊያ ጨዋታ የተጫዋቾችም ሆነ የቅርፅ ለውጥ አድርገው ወደ ሜዳ ስለገቡበት ምክንያት…?

የሱማሊያውን እና የዛሬውን ጨዋታ ያደረግነው በሁለት ቀን ልዩነት ነው። መጀመሪያ አስበን የነበረው ሁለቱን ጨዋታዎች ተቀራራቢ አቅም ያላቸውን ተጫዋቾች እየለዋወጥን ለመጠቀም ነበር። ያንን በመንተራስ ዛሬ የተወሰኑ ተጫዋቾችን ለውጠናል። ከዚህ ባለፈም የታንዛኒያን አጨዋወት የተመለከተ የተወሰነ የሰማናቸው ነገሮች ነበሩ። በተለይ በመስመር በማጥቃት ጎሎችን ለማስቆጠር እንደሚጥሩ ሰምተን ነበር። ይህንን ለመዝጋት በ3-5-2 አደራደር ስንከላከል 5 እንድንሆን ጥረት አድርገን ነበር። በጨዋታው ውስጥ ግን ይሄንን ብንከተልም ጎሎች ተቆጥረውብናል። ከነበረን ጊዜ አንፃር ይሄንን ታክቲክ ተጫዋቾቻን ተረድተው ስላልተጫወቱ ወደምናውቀው 4-3-3 አደራደር ተመልሰን ተጫውተናል።

በውድድሩ ላይ ቡድኑ ስላሳየው ጥሩ ነገር…?

ታንዛኒያዎች በደንብ ሰርተውበት ረጅም ጊዜ ለፍተው የመጡበት እንደሆነ ያስታውቃል። የሥራቸውንም ነው ያገኙት። የእኛ ተጫዋቾች ደግሞ እንደሚታወቀው ለአጭር ቀናት ውድድሮች የሚዘጋጁ እና ብዙ ስልጠና ያላገኙ ናቸው። እኛም የነበረን ጊዜ በጣም አጭር ከመሆኑ የተነሳ ታክቲኮችን የመረዳት ችግርም ነበር። እኔን ጨምሮ ያለነው የአሠልጣኝ ቡድን አባላት ያለንን አቅም ተግባራዊ በማድረጉ ረገድ ድክመቶች ነበሩ። ይሄ ደግሞ የመጣው ከጊዜ አንፃር ነው። ተጫዋቾቹ ወደፊት ሥራ ቢሰራባቸው ጥሩ አቅም ያላቸው ስለሆነ እንደነታንዛኒያ ትልቅ ደረጃ መድረስ ይቻላል። አሁን ባገኘነው አጭር ጊዜ ያየናቸው ለውጦች ስላሉ ወደፊት ደግሞ በደንብ ቢሰራባቸው ትልቅ ደረጃ እንደሚደርሱ መናገር ይችላል።

ለዛሬው ጨዋታ ስለተዘጋጁበት መንገድ…?

ከሽንፈት መልስ ነው የዛሬው ጨዋታ። ታንዛኒያዎች ደግሞ የእኛን ጨዋታ ተመልክተው ነው የመጡት ፤ እኛ ግን የታንዛኒያን ምንም አይነት ጨዋታ አላየንም።ይህ ቢሆንም በከፍተኛ ተነሳሽነት የባለፈውን ስህተቶቻችንን ተነጋግረን አርመን ነበር የመጣነው። ቅድም እንደገለፅኩት መስመሮችን ዘግተን ኳሱን ተቆጣጥረን ለመጫወት ነበር ያሰብነው። ኳሱን ስንቆጣጠር በታንዛኒያዎች በኩል ከፍተኛ ጫና ነው የነበረው። በምንፈልገው መልኩም ኳሱን መስርተን አልወጣንም። አላስፈላጊ የሆኑ ረጃጅም ኳሶችም ይበዙ ነበር። ይሄንን ፈልገነው ሳይሆን ተገደን ነበር ስናደርግ የነበረው። ወጥመዶችን የምናልፍበትን መንገድ አውርተን ነበር ወደ ሜዳ የገባነው ፤ ግን ይሄንን ታክቲክ ተጫዋቾቹ አልተገበሩትም። ታክቲኩን ያልተገበሩበት መንገድ ደግሞ ልጆች በመሆናቸው እና በዚህ መንገድ እያደጉ ስላልሆነ በዚህች አጭር ጊዜ ለመረዳት በጣም ስለተቸገሩ ነበር።

ስለተጫዋቾች ምርጫ…?

በሀዋሳው ውድድር ላይ የታዩ 51 ተጫዋቾች በቴክኒክ ኮሚቴው ተመርጠው እኛም ውድድሩ ላይ ስለነበርን 14 ተጫዋቾችን ጨምረን በአጠቃላይ 65 ተጫዋቾችን ይዘን በ5 ቀን ውስጥ ነው ያጣራነው። እነዚህን 65 ተጫዋቾች በ5 ቀን አጣርተን በ5 ቀን ስናስቀር 5 ተጫዋቾችን ብቻ ነው በብቃት የቀነስነው። ሌላው እንዳለ በእድሜ ምርመራ ነው የወደቀው። እውነት ለመናገር አንደኛ እና ሁለተኛ ሳይሆን ሦስተኛ ምርጫችንን ነበር ይዘን ወደ ውድድር የገባነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በውስጥ ውድድሮች ላይ ቡድኖች በትክክለኛው ዕድሜ ላይ የሚገኙ ተጫዋቾችን ቢይዙ ጥሩ ነው። በዚህ መልክ ቡድኖች ቢዘጋጁ ኖሮ እኛ አንቸገርም ነበር። መፍትሔ የሚሆነው በትክክለኛ እድሜ ላይ የሚገኙ ተጫዋቾችን ይዞ ትክክለኛውን ስልጠና እየሰጡ መሄድ ነው። በዚህ ሂደት ተጫዋቾች ቢሄዱ ብሔራዊ ቡድን ሲመጡ አይቸገሩም ነበር። አሁን ለምሳሌ ስም ባልጠራም ከአንድ ክለብ 8 ተጫዋቾችን መርጠን 7ቱ በእድሜ ወድቀው ነበር። ይህ ክለብ ግን ውድድሩ ላይ ተሳታፊ ነበር። ስለዚህ በዚህ መንገድ መጓዝ ያስፈልገናል።

አሠልጣኝ ኪም ፖልሰን – ታንዛኒያ

ጨዋታው እንዴት ነበር?

በውጤቱ ደስተኛ ነኝ። ይሄ የመጀመሪያ ጨዋታችን ነው። ኢትዮጵያ ግን ሁለተኛ ጨዋታዋ ነው። የመጀመሪያውን ጨዋታ ስለተሸነፈች ጫና ውስጥ ሆና ነው የገጠመችን። ይህ ቢሆንም የመጀመሪያውን አጋማሽ ሁለት ለሁለት ተለያይተናል። በመጀመሪያው አጋማሽ ጥቃቅን ስህተቶችን ሰርተን ነበር ግቦች የተቆጠሩብን ፤ በሁለተኛው አጋማሽ ግን ብስለት የተሞላበት አጨዋወት ተከትለን ጥሩ ለመንቀሳቀስ ሞክረናል። ባለቀ ሰዓትም ግብ አስቆጥረን በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታችን ድል አድርገናል። በአጠቃላይ ታዳጊዎችን እንደመያዛችን ጥሩ ተንቀሳቅሰናል። ተጫዋቾቹ ከዚህ በፊት ምንም ጨዋታ አድርገው ስለማያውቁ የተወሰነ ተደናግጠው ነበር ፤ ከዛሬ በኋላ ግን የጨዋታ ልምድ እያገኙ ስለሚሄዱ ይሄ ድንጋጤ እንደሚቀረፍ አስባለው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጠንካራ ፍልሚያ እንድናደርግ ስላደረገን አመሰግናለው።

በዛሬው ጨዋታ ስለነበራቸው ዕቅድ?

የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ ጨዋታ አይቼ ነበር። ዛሬ ግን አራት አምስት ተጫዋቾችን ለውጠው ነው ወደ ሜዳ የገቡት። የጨዋታ መንገዱም ከሱማሊያው ፍልሚያ የተለየ ነበር። እኛም በጨዋታው ላይ የኢትዮጵያን አቀራረብ እያየን ለውጦችን አድርገን ተሳክቶልን ወጥቷል። በተለይ የተጫዋቾች ለውጦቻችን ፍሬያማ ነበሩ። ጨዋታውንም በእንቅስቃሴ እያየን ቀይረን ባስገባናቸው ተጫዋቾች በማሸነፋችን ደስተኞች ነን።

ስለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እንቅስቃሴ?

ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድኖች ጋር ብዙ ጊዜ ተጫውተናል። ዓምና በ23 ዓመት በታች የሴካፋ ውድድርም ሆነ የዋናውን ቡድን ገጥመናል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የጨዋታ መንገድ አጫጭር ኳሶችን ማብዛት ነው። ይሄንን እናውቃለን። ይህንንም ተከትሎ አግሬሲቭ ለመሆን ሞክረናል። ኳሶችን እያጨናገፍን በቶሎ ወደ ወደ ሳጥን ለመውሰድ ነበር ስንጥር የነበረው። ግን ቡድኑ ጥሩ የሚጫወት ቡድን ነው።