የሁለተኛ ሳምንት የሦስተኛ ቀን ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች

በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛ ሳምንት የሦስተኛ ቀን ጨዋታዎች ዙሪያ ተከታዮቹን መረጃዎች አሰባስበናል።

ሀዲያ ሆሳዕና ከ ሲዳማ ቡና

በሊጉ የመክፈቻ ጨዋታ ሀዲያ ሆሳዕናዎች በመቻል ሽንፈትን አስተናግደው በአንፃሩ ሲዳማ ቡናዎች ደግሞ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርተው ወደዚህኛው የጨዋታ ሳምንት የሚያመሩ ሲሆን ሁለቱም ቡድኖች የመጀመሪያ ሙሉ ሦስት ነጥባቸውን ለማግኘት ጥሩ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በመቻል በተሸነፉበት ጨዋታ በሀዲያ ሆሳዕናዎች በኩል በቀኝ ወገን የነበረው የብርሃኑ በቀለ እና ፀጋዬ ብርሃኑ ጥረት ባለፈ እንደ ቡድን በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ ብዙ መሻሻል የሚገባው ቡድን እንደነበር አስተውለናል። በአንፃሩ ሲዳማ ቡናዎች በድሬዳዋ ከተማው ጨዋታ በሁለት አጋጣሚዎች ጨዋታውን መምራት ቢችሉም ግቦችን አስተናግደው አቻ መለያየታቸው የሚታወስ ሲሆን በጨዋታውም ቡድኑ ከአምናው ጋር የሚመሳሰል የተወሰኑ የመከላከል ችግሮችን አንደነበሩበት ታዝበናል። በመሆኑም አሰልጣኝ ወንድማገኝ ተሾመ ከወዲሁ ይህን ጉዳይ ትኩረት ይሰጡታል ተብሎ ይጠበቃል።

በሲዳማ ቡና በኩል በነገው ጨዋታ ባለፈው ጨዋታ በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ የተወገደው ጊትጋት ጉትን አገልግሎት ብቻ የማያገኙ ሲሆን በአንፃሩ በሀዲያ ሆሳዕና በኩል የመኖሪያ ፍቃዳቸው ያላለቀላቸው ጋናዊያኑ ሪችሞንድ ኦዶንጎ እና ስቴፈን ኒያርኮም ነገ የማይኖሩ ሲሆን በተመሳሳይ ጉዳት ላይ የሚገኘውም ቃለአብ ውብሸትም ከነገው ስብስብ ውጪ እንደሆነ ሲታወቅ ዳግም ንጉሴ ከቅጣት መልስ ነገ ለምርጫ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠናል።

ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሊጉ በስድስት አጋጣሚዎች የተገናኙ ሲሆን ሁለት ሁለት ጊዜያት ሲሸናነፉ ቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተቋጭተዋል።

ይህን 7 ሰዓት ሲል ጅማሮውን የሚያደርገውን የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታን በመሀል ዳኝነት ተካልኝ ለማ ሲመራው ፣ አበራ አብርደው እና እሱባለው መብራቱ በረዳትነት እንዲሁም እያሱ ፈንቴ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ተመድበዋል።

አዳማ ከተማ ከ መቻል

ተቃራኒ መልክ ያለው አጀማመር ያደረጉት ሁለቱ ቡድኖች አዳማ ከተማዎች በመጀመሪያው ሳምንት በፋሲል ከነማ ካስተናገዱት ሽንፈት ለማገገም እንዲሁም ሀዲያ ሆሳዕናን አሸንፈው የመጡት መቻሎች ደግሞ ከፍ ያለ ግምትን አግኝተው በጀመሩት ውድድር ጥሩ አጀማመራቸውን ለማስቀጠል ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ምንም እንኳን በፋሲል በተሸነፉበት ጨዋታ አዳማ ከተማዎች በርከት ያሉ ደቂቃዎችን በጎዶሎ ተጫዋች ቢያሳልፉም ፈጠን ያሉ ቅብብሎችን በመከወን በፍጥነት ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመድረስ የሚሞክር ቡድን እንደነበር አስተውለናል። በአንፃሩ በመጀመሪያው ጨዋታ 8 አዳዲስ ተጫዋቾችን በመጀመሪያ ተሰላፊነት ያስጀመሩት መቻሎች በጨዋታው በቅንጅቱ ረገድ ብዙ እንደሚቀራቸው የተመለከትን ነበር። ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ መልኩ ኳሱን የመቆጣጠር ፍላጎት ቢኖራቸውም ቅብብላቸውን ወደ ግብ ዕድል በመቀየር ረገድም በመጀመሪያው ጨዋታ ደካማ ሆነው ተመልክተናል። በመሆኑም በነገው ጨዋታ በዚህ ረገድ ተሻሽለው መቅረብ ይኖርባቸዋል።

በአዳማ ከተማዎች በቅጣት ምክንያት ከሚያጡት ዊልያም ሰለሞን ውጭ የተሟላ ስብስብን ይዘው ለነገው ጨዋታ የሚቀርቡ ሲሆን በአንፃሩ መቻሎችም ከጉዳት ሆነ ከቅጣት ነፃ የሆነን ስብስብ ይዘው ይቀርባሉ።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በሊጉ ለሃያ ዘጠኝ ያህል ጊዜያት የተገናኙ ሲሆን አስራ ሦስቱ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ ቀሪዎቹን አስራ ስድስት በመሸናነፍ የተጠናቀቁ ጨዋታዎችን ሁለቱ ቡድኖች በዕኩል የተካፈሏቸው ናቸው።

ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት ሲመራው ፣ ሻረው ጌታቸው እና ሲራጅ ኑርበገን ረዳቶች ፣ ባህሩ ተካ አራተኛ ዳኛ ናቸው፡፡

ያጋሩ