ፕሪምየር ሊግ ትኩረት | ጎሎች ፣ ድንቅ ጎሎች ፣ የመጨረሻ ደቂቃዎች ድራማ…

14 ጨዋታዎች በድምሩ 41 ጎሎች ፣ በርከት ያሉ ድንቅ ጎሎች እንዲሁም የመጨረሻ ደቂቃዎች ድራማዎችን በማስመልከት የጀመረው የ2015 የውድድር ዘመን አጀማመሩ አስገራሚ ሆኗል። በተከታዩ ፅሁፋችን በጥቂቱ በሁለቱ ሳምንታት ስለተመለከትናቸው ጎሎች የተወሰኑ ሀሳቦችን ለማንሳት ወደናል።

እግርኳስ ለተወሰኑ ዕድለኞች ስራ ለተቀረው ብዙሀኑ ደግሞ መዝናኛ ነው። በእግርኳስ ለመዝናናት ደግሞ ጎሎች እና የመጨረሻ ደቂቃዎች ድራማዊ ክስተቶች ቀዳሚዎቹ ተመራጮች ናቸው። እግርኳስ እንደሌሎች የኳስ ስፖርቶች ከፍተኛ ጎሎች የሚቆጠሩበት አይደለም ፤ በአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች ላይ የተሰሩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በጨዋታዎች በአማካይ የሚቆጠሩ የጎሎች መጠን ከሁለት እስከ ሦስት ስለመሆናቸው ያሳያሉ። በቀደመው ዘመን በርካታ ጎሎች የሚቆጠሩባቸው ጨዋታዎች የተለመዱ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ግን እግርኳስ በደረሰበት ደረጃ የጎሎች መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ ይገኛል።በእንግሊዝ እግርኳስ ባለፉት 130 ዓመታት በተመዘገቡ ውጤቶች ላይ በተሰራ አንድ ጥናት በቅደም ተከተል (1-1 ፣ 1-0 ፣ 2-1) በብዛት የሚመዘገቡት ውጤቶች ስለመሆናቸው ያሳያል።

በመሆኑም በዚህ ደረጃ በጨዋታዎች የሚቆጠሩ የጎሎች መጠን እየቀነሰ በመጣበት በዚህ ዘመን በጎሎች እና በድርጊቶች የተሞሉ ጨዋታዎች በየትኛውም ወገን አሸናፊነት ቢጠናቀቁ በጥንቃቄ ከተሞሉ እና ያለ ግብ ከሚጠናቀቁ ጨዋታዎች የተሻለ አዝናኝ ስለመሆናቸው አያጠያይቅም። ከዚህ ባለፈም በመጨረሻ ደቂቃ የሚቆጠሩ ጎሎችም እንዲሁ የሚፈጥሩት ስሜት እጅግ የተለየ ከመሆኑ አንፃር የእግርኳስ ማጣፈጫዎች ናቸው። ከቀናት በፊት ጅማሮውን ያደረገው ሊጋችን በሦስቱም መመዘኛዎች እጅግ አዝናኝ የሆኑ ሰባት የጨዋታ ቀናትን አሳልፏል።

ሁለተኛ ሳምንቱ ላይ በደረሰው የዘንድሮው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እስካሁን በተደረጉ ሰባት የጨዋታ ቀናት በድምሩ አርባ አንድ ጎሎች ከመረብ ተዋህደዋል። ይህም በአማካይ በጨዋታ ሦስት ግቦች እንደማለት ሲሆን እስካሁን ከተደረጉ አስራ አራት ጨዋታዎች ብቸኛው ጎል ያልተስተናገደበት ጨዋታ የወላይታ ድቻ እና የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ መሆኑን ከግምት ስናስገባ የሊጉ አጀማመር በንፅፅር በተሻለ የመሸናነፍ ፍላጎት በጎሎች ታጅበው ስለመደረጋቸው መናገር ያስችላሉ። እርግጥ ከጎሎች አንፃር በተለይ ውድድሩ የቀጥታ የቴሌቪዥን ሽፋን ማግኘቱን ተከትሎ የተሻለ ፉክክር ጥራት እና ጎሎች የታጀቡ ጨዋታዎች ከበፊቱ በተሻለ በተለይ በመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች ላይ እየተመለከትን መገኘታችን አንዱ የቀጥታ ስርጭቱ ትሩፋት ብሎ መውሰድ ይቻላል።

ሌላው ትኩረት የሚስበው ጉዳይ ከጎሎቹ ቁጥር ባለፈ በርከት ያሉ የጥራት ደረጃቸው ላቅ ያሉ ጎሎች የመልከታችን እና በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎችም የሚቆጠሩ ጎሎች መጠን እንዲሁ ከፍ የማለታቸው ጉዳይ ነው። ሁለቱም ጉዳዮች ሊጉ ለሊጉ ተመልካቾች የተዝኖት ደረጃ ከፍ ከማድረግ ባለፈ ሊጉን በማስተዋወቅ ረገድ ከሚኖራቸው አዎንታዊ ሚና አንፃር ትኩረት የሚስቡ ናቸው።

በጌታነህ ከበደ ግሩም የቅጣት ምት ጎል በተከፈተው ሊጉ ከስንታየሁ ዋለጬ ድንቅ ከርቀት የተቆጠረች ጎል እስከ ተመስገን ደረሰ መቀስ ምት ድረስ በርከት ያሉ ምርጥ ምርጥ ጎሎችን በሰባቱ የጨዋታ ቀናት ተመልክተናል። በተለይ ደግሞ ከሳጥን ውጭ በቀጥታ ተመተው ተቆጠሩ ጎሎች ቁጥር ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል። ተመስገን በጅሮንድ ፣ ብሩክ ማርቆስ ፣ እስማኤል ኦሮ-አጎሮ ፣ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን ፣ ዮሴፍ ዮሐንስ ፣ ባዬ ገዛኸኝ በእስካሁኑ የሊጉ ጉዞ በውድድር ዘመኑ ማብቂያ ላይ “ለዓመቱ ምርጥ ጎል” ዕጩ መሆን የሚችሉ አስገራሚ ጎሎችን ከሳጥን ውጪ ማስቆጠር ችለዋል። እርግጥ መሰል ጎሎችን በቡድን አውድ ከመመልከት ይልቅ የግብ አስቆጣሪዎቹ ግላዊ ብቃት እና የመፈፀም አቅም ላይ የተመሰረቱ እንደመሆናቸው ለአስቆጣሪዎቹ ተጫዋቾች የተለየ አድናቆት እንድንሰጥ ያስገድደናል። በተለይ ከርቀት የሚደረጉ አደገኛ ሙከራዎችን አለፍ ሲልም የሚቆጠሩ ጎሎችን መመልከት እንደብርቅ በሚታይበት ሊጋችን በጥቂት ቀናት ልዩነት በዚህን ያህል መጠን ተደጋጋሚ ድንቅ ጎሎችን ከርቀት የመመልከታችን ነገር አጋጣሚ ወይንስ ተሰርቶበት የሚለው ጉዳይ በቀጣዮቹ ጊዜያት መልስ የሚያገኝ ጉዳይ ቢሆንም ለጎሎቹ ሆነ ለአስቆጣሪዎቹ አድናቆት መስጠት ተገቢ ነው።

በተቃራኒው ከሳጥን ውጪ የተቆጠሩ ጎሎች ስለመብዛታቸው ስናነሳ መዘንጋት የሌለበት ጉዳይ ጎሎቹ የተቆጠሩባቸው ቡድኖች ጎሎቹን ያስተናገዱበትም መንገድ እንዲሁ መታየት ይኖርበታል። ጎሎቹን በደንብ ላስተዋለ ጎሎቹን ባስተናገዱት ቡድኖች አጠቃላይ የመከላከል ስርዓት ላይ ያሉ ክፍተቶችን ላስተዋለ በሀገሪቱ ትልቁ የሊግ እርከን ላይ መሰል የመሰረታዊ የመከላከል ፅንሰ ሀሳቦች ተጥሰው ማየት እጅግ የሚያስገርም ነው የሚሆነው።

አሁን ባለው የእግርኳስ አረዳድ ቡድኖች በሁሉም የጨዋታ ምዕራፎች የተሻለ ስለመሆን አብዝተው በሚጨነቁበት በዚህ ዘመን እነዚህ ከርቀት የተቆጠሩ ጎሎች በጥቅሉ ቡድኖቻችን ከኳስ ውጪ (Against the ball) ያላቸው ዝግጁነት እና አፈፃፀም ላይ በደንብ መሻሻል እንደሚገባቸው የሚያመላክቱ ናቸው። ቡድኖች ኳስን በሚያጡበት ቅፅበት ሆነ ዘለገ ላለ የጨዋታ ሂደት ከኳስ ውጪ በሚሆኑባቸው አጋጣሚዎች በምን መልኩ ነው ምላሽ የሚሰጡት የሚለው ጉዳይ ትኩረትን ይሻል።

ከመነሻው ኳሱን በሚያጡበት ወቅት ኳሱን ዳግም ለማግኘት ያላቸው አደረጃጀት ሆነ ተነሳሽነት ፣ ወደ መከላከል ቅርፃቸው ለመግባት የሚወስድባቸው ጊዜ ርዝመት እንዲሁም በመከላከል ቅርፅ ውስጥ በአንድ ቦታ ከመከማቸት ባለፈ በተደራጀ መልኩ ኳስ የያዘው ሰው ላይ ጫና የማሳደር ክፍተቶች ጎሉን የሚያስቆጥሩት ተጫዋቾች እንዴት በቂ የማሰብያ ጊዜ እና ቦታ እንዲያገኙ እንዳስቻላቸው መመልከት ይቻላል። ከዚህ ባለፈም በተወሰኑት ጎሎች ላይ የግብ ጠባቂዎች የቦታ አያያዝ እና አጠባበቅ ላይ የተመለከትናቸው ክፍተቶች ለጎሎቹ የራሳቸውን ድርሻ ተወጥተዋል። እርግጥ የተቆጠረ ጎሎች ላይ ተነስቶ ሀሳቦችን መሰንዘር እጅግ ቀላል ቢሆንም በሌሎች የጨዋታ ሂደቶችም መሰል ችግሮች የሚስተዋሉ የመሆናቸው ነገር ቡድኖች ከጎሎቹም ባሻገር ከላይ ባነሳናቸው ሀሳቦች ላይ ስለመሻሻል ሊሰሩ ይገባል እንላለን።

ከዚህ ሌላ ጎሎች እየተቆጠሩበት ስለሚገኙትም ደቂቃ ጥቂት ማለት ይኖርብናል። በሰባቱ የጨዋታ ቀናት በተደረጉት አስራ አራት ጨዋታዎች አስር ያህል ግቦች በጨዋታዎች የመጨረሻ አስር ደቂቃዎች ላይ ተመዝግበዋል። ይህም በአጠቃላይ እስካሁን ከተቆጠሩት 41 ጎሎች ውስጥ ለ25% የቀረበ ድርሻ አላቸው ማለት ነው። ከቁጥሮቹ ባለፈ ከአስሩ ጎሎች ስድስቱ በቀጥታ የጨዋታን ውጤት (Game State) የቀየሩ ትልቅ ዋጋ የነበራቸው ጎሎች መሆናቸው ይበልጥ ትኩረትን የሚስብ ነው።

2015 የውድድር ዘመን ከተጀመረ ገና ጥቂት ቀናት ቢቆጠሩም እጅግ ማራኪ በሆነ ጎሎች እና የጨዋታን መልክ በቀየሩ የመጨረሻ ደቂቃ ጎሎች ታጅቦ ቀጥሏል። ይህም መግቢያችን ላይ እንዳልነው አዳዲስ ተመልካቾች ለመሳብ እየጣረ ላለው ሊጋችን ይበልጥ እሴት የሚጨምርለት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ለ30 የጨዋታ ሳምንታት የሚዘልቀው ውድድሩ በዚህ መልኩ ይቀጥላል ወይ የሚለው ጉዳይ ግን በቀጣይ ጨዋታዎች ይጠበቃል።

ያጋሩ