የማዳጋስካር ዳኞች የነገውን ጨዋታ ይመራሉ

በባህር ዳር ስታዲየም ፋሲል ከነማ ከ ቱኒዚያው ሴፋክሲያን ጋር የሚያደርጉትን ወሳኝ ጨዋታ የማዳጋስካር ዜግነት ያላቸው ዳኞች ይመሩታል፡፡

የካፍ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ የሁለተኛው ዙር ማጣሪያ መርሐ-ግብሮች ከዛሬ ጀምሮ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት መደረግ ይጀምራሉ፡፡ በውድድሩ ላይ ሀገራችንን ወክሎ ተሳትፎን እያደረገ የሚገኘው ፋሲል ከነማ ነገ 10 ሰዓት በደጋፊው ፊት የቱኒዚያውን ክለብ ሴፋክሲያንን በሜዳው ይገጥማል፡፡ ይህን የነገ የሁለቱን ክለቦች ጨዋታ የሚመሩ ዳኞች ከማዳጋስካር ሲሆኑ የጨዋታው ታዛቢ ደግሞ ከደቡብ ሱዳን ተመድበው ባህርዳር ዲላኖ ሆቴል ማረፊያቸውን አድርገዋል፡፡

ማዳጋስካር ካሏት ኤሊት ዳኞች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው አንዶፌትራ ራኮቶጃኦና በመሀል ዳኝነት ጨዋታውን ሲመራው ሊዮኒየል አንድሪያንቴናይና እና ዲምቢኒያኒያ አንድሪአቲያናሪቬሎ በረዳነት እንዲሁም አብዱል ካኖሶ በአራተኛ ዳኝነት ተመድበዋል። ደቡብ ሱዳናዊው ሴቢት ቤጊ ራሳስ ደግሞ የጨዋታው ታዛቢ መሆናቸው ታውቋል፡፡