ከሴፋክሲያን የቡድን አባላት ጋር የተደረገ ቆይታ

👉”የመልሱን ጨዋታ የሚያቀልልን ውጤት እናስመዘግባለን” የሱፍ ከሬይ

👉”እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገሮች የመጫወት ልምድ ስላለን ብዙም አንቸገርም” ቻዲ ሃማሚ

👉”አስተናጋጁ ክለብ ጥሩ አቀባበል እና እንክብካቤ ስላደረገልን እናመሠግናለን” የሱፍ ከሬይ

👉”በእርግጠኝነት እናሸንፋለን ፤ በደንብ ተዘጋጅተናል” ቻዲ ሃማሚ

በተጠናቀቀው የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ፋሲል ከነማ ሀገራችንን በኮንፌደሬሽን ዋንጫ የመወከል ዕድል እንዳገኘ ይታወቃል። ክለቡ በመጀመሪያው ዙር የማጣሪያ ጨዋታ የቡሩንዲውን ቡማሙሩ ገጥሞ በድምር ውጤት ያሸነፈ ሲሆን በሁለተኛው ዙር ማጣሪያ ደግሞ ከቱኒዚያው ክለብ ሴፋክሲየን ጋር ተደልድሏል። በነገው ዕለትም በደጋፊዎቹ ፊት የመጀመሪያ ጨዋታውን በባህር ዳር ስታዲየም ያከናውናል።

በተጠናቀቀው የ2021/22 የውድድር ዓመት ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ሴፋክሲየን የመጀመሪያውን ጨዋታ ለማከናወን በትናንትናው ዕለት ባህር ዳር ገብቶ ሁለት የልምምድ መርሐ-ግብሮችን እንዳከናወነ ከሰዓታት በፊት ዘገባ አቅርበን ነበር። በጨዋታው ዋዜማ በተደረገው ልምምድ ላይ ተገኝተን ደግሞ ከክለቡ የአሰልጣኝ ቡድን አባል የሱፍ ከሬይ እና ከቡድኑ አምበል ቻዲ ሃማሚ ጋር ያደረግነውን አጠር ያለ ቆይታ እንደሚከተለው አሰናድተናል።

ስለዝግጅት ጊዜያት…?

“ዝግጅት በጣም ጥሩ ነው። ጉዞው ረጅም ነበር ፤ ግን በዚህ አጋጣሚ አስተናጋጁን ክለብ ማመስገን እንፈልጋለን። በጣም ጥሩ አቀባባል እና እንክብካቤ አድርገውናል። በቂ የዕረፍት እና የዝግጅት ጊዜ ነበረን ፤ ለጨዋታውም ተዘጋጅተናል።” የሱፍ ከሬይ

“ዝግጅት በጣም ጥሩ ነበር በዘንድሮው ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የመጀመሪያ ጨዋታችን ነው። ጥሩ ውጤት እናመጣለን ብለን እናስባለን።” ቻዲ ሃማሚ

ስለ ተጋጣሚያቸው ፋሲል ከነማ…?

“ነገ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ከእነሱ ጋር የምንጫወተው ፤ ባለፈው ዓመት ውድድር ምርጥ ጊዜ እንዳሳለፉ እናውቃለን። ዘንድሮም በጥሩ ብቃት ነው እየጀመሩ ያሉትና ባሉበት ደረጃ ጥሩ መሆናቸውን እናውቃለን።” የሱፍ ከሬይ

በዝግጅት ወቅት ጠንካራ ጨዋታዎችን ስለማድረጋቸው…?

“ዝግጅት ከጀመርን ብዙ ጊዜ አስቆጥረናል። ብዙ  የወዳጅነት ጨዋታዎችንም አድርገናል። ከሦስት ሳምንታት በፊት ጨዋታዎች ላይ ስለነበርን ቡድኑ ለጨዋታው በደንብ ተዘጋጅቷል።” የሱፍ ከሬይ

“ዕድለኞች ነን በቱኒዚያ ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ እና የፍጻሜ ጨዋታዎችን አድርገናል። ጥሩ ውጤትም ነበረን ፤  የቱኒዚያ ዋንጫንም ማንሳት ችለናል ከጨዋታ አልራቅንም ነበር።”  ቻዲ ሃማሚ

ስለቡድኑ ወቅታዊ ሁኔታ….?

“ቡድኑ ሙሉ ነው። የምናጣው ተጫዋች የለም ፤ ሁሉም ተዘጋጅቷል።” የሱፍ ከሬይ

ስለ አየር ሁኔታው እና ስለ መጫወቻ ሜዳው…?

“ምንም ችግር የለብንም። አፍሪካ ውስጥ ብዙ ቦታዎች ላይ ተጫውተናል። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገሮች ላይ የመጫወት ልምዱ አለን። 90 ደቂቃ ያለንን ነገር እንሰጣለን ፤ ጥሩ ውጤትም እናገኛለን ብለን እናስባለን። የመጫወቻ ሳሩ በጣም ምርጥ የሚባል አይደለም ግን ቀድመን ስላወቅን ብዙ አያስቸግረንም።” ቻዲ ሃማሚ

ከነገው ጨዋታ ምን እንጠብቅ…?

“ስፖርታዊ ጨዋነት የተሞላበት ጨዋታ እንደሚሆን እንጠብቃለን። የመልሱን ጨዋታ የሚያቀልልን ውጤት ይዘን እንደምንወጣም ተስፋ እናደርጋለን። በሁለቱም በኩል መልካም ጨዋታ እንዲሆን እመኛለሁ።” የሱፍ ከሬይ

“በእርግጠኝነት እናሸንፋለን። በደንብ ተዘጋጅተናል።” ቻዲ ሃማሚ