“በቻልነው መጠን ያህል በሚገባ ተዘጋጅተናል” አሰልጣኝ ኃይሉ ነጋሽ

በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ጨዋታ የቱኒዚያውን ክለብ ሴፋክሲያንን የሚገጥመው ፋሲል ከነማ አሰልጣኝ ኃይሉ ነጋሽ ስለ ወሳኙ ጨዋታ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

በነገው ዕለት ዕሁድ በካፍ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ የሁለተኛው ዙር መርሐግብር ተካፋይ የሆነው ፋሲል ከነማ የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታን ሳያደርግ በቀጥታ ወደ ሁለተኛው ዙር ከተሻገረው የቱኒዚያው ክለብ ሴፋክሲያን ጋር በባህር ዳር ዓለምአቀፍ ስታድየም ልክ 10 ሰዓት ሲል ያስተናግዳል፡፡ ቡድኑ በዛሬው ዕለት የመጨረሻ ልምምዱን በዐፄ ቴዎድሮስ ስታድየም የሰራ ሲሆን ከልምምዱ መጠናቀቅ በኋላም የነገውን ወሳኝ ጨዋታ አስመልክቶ አሰልጣኝ ኃይሉ ነጋሽ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ተከታዩን አጠር ያለ ቆይታን አድርገዋል፡፡

ስለተደረገው ዝግጅት እና ስለ ተጫዋቾች ጤንነት …

“ዝግጅታችን በጣም ጥሩ ነው፡፡ የሊጉን አንድ ጨዋታ ተጫውተናል። ስለዚህ ከዛ ክፍተቶቻችን ተነስተን በክፍተቶቻችን ልምምዶችን ሰርተን ለነገው የኮንፌዴሬሽኑ ጨዋታ ጥሩ ዝግጅት አድርገናል ብዬ አምናለሁ፡፡ መጠነኛ ጉዳት ነበረው ሱራፌል የጡንቻ መሸማቀቅ ባቱ አካባቢ በዚህም ነበር የመጀመሪያው የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ላይ ያልተጠቀምኩበት ምክንያቱም የሪከቨር ታይሙን እንዳያጣ ብለን ነው ፤ ምክንያቱም እስከነ ጉዳቱ ቢገባ ለቀጣይም ስለምናጣው። ከአዳማ በነበረን ጨዋታ ላይም ሁለት ልጆች ጉዳት ነበረባቸው ትንሽ የአምሳሉ ጠንከር ያለ ጉዳት ነው። የአስቻለው ግን መጠነኛ ጉዳት ነበረበት ቢሆንም ግን ለአሁኑ ጨዋታ አስቻለው እና ሱራፌልን እንጠቀምባቸዋለን፡፡

ስለ ተጋጣሚው ሴፋክሲያን…

“እንቅስቃሴያቸውን ለማግኘት አልቻልንም፡፡ ያው የእነርሱ የሊግ ውድድር ገና አልጀመረም። ትንሽ የወዳጅነት ጨዋታዎች ላይ ነበር የነበሩት። በመጀመሪያው ዙር ማጣሪያም አልተሳተፉም ፤ እኛ ነን የተጫወትነው። ዞሮ ዞሮ ግን እኛ ይሄኛውን ጨዋታ በሜዳችን በደጋፊያችን ፊት በዓየሩም በሁሉም ነገር ታግዘን ያለንን ከመቶ ፐርሰንት በላይ ተጠቀምን የምንችለውን ያህል አቅምን ተጠቅመን በሜዳችን ለመውጣት ነው ዝግጅት እያደረግን የነበረው፡፡

ከቡማሙሩ ጨዋታ ቡድኑ ላይ ስለ ነበረው ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች…

“የብሩንዲው ቡማሙሩ እና የቱኒዚያ ሁሉም ክለቦች ልዩነት አላቸው፡፡ እነዚህ የሰሜን አፍሪካ ቡድኖች ብዙ ጊዜ ታክቲካል ዲሲፕሊን ናቸው። የመስመር ኳሶች ላይ ፐርፌክት ናቸው። የቆሙ ኳሶችም ላይ በጣም ጥሩ ስለሆኑ ከእነዛ ተነስተን ነው ልምምዶቻችንን ለመስራት የሞከርነው። እንግዲህ በቻልነው መጠን ያህል በሚገባ ተዘጋጅተናል ብለን እናምናለን፡፡

ስለ ደጋፊዎች…

“ሁሌም የፋሲል ደጋፊ ከጎናችን ነው ፤ እስከ ዘጠናው ደቂቃ ድረስ ከጎናችን እንደሚሆን ሙሉ ተስፋ አለን፡፡ ደጋፊ ማለት አስራ ሁለተኛ ተጫዋች ማለት ነው። ባለፈውም የሊጉን ጨዋታ ስንጫወት ያለ ደጋፊ ነው የተጫወትነው። ምን ዓይነት ተፅዕኖ እንዳለው አይተናል ደጋፊ ሲኖር ደግሞ የተሻለ በሞራል ልጆች ይንቀሳቀሳሉ ብዬ አስባለሁ። እና ተጨማሪ ኃይል ስለሆነ የተለመደው ድጋፋቸውን ነው የምንጠብቀው ከደጋፊዎቻችን፡፡”