ኢትዮ ኤሌክትሪክ የአስር ተጫዋቾችን ዝውውር ፈፅሟል

በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ 2ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ኢትዮ ኤሌክትሪክ የአስር አዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር ሲፈፅም የአስራ አንዱን ውል ደግሞ አራዝሟል፡፡

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ባሳለፍነው የውድድር ዓመት ሳይጠበቅ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ በመፈፀም በደረጃ ሰንጠረዡ ሁለተኛ ላይ ተቀምጦ ዓመቱን የፈፀመው የአሰልጣኝ መሠረት ማኔው ክለብ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ለዘንድሮው የ2015 የውድድር ዘመን በይበልጥ ተጠናክሮ ለመምጣት በማሰብ የበርካታ አዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር ሲፈፅም የነባር ተጫዋቾችንም ውል አራዝሟል፡፡

መሰሉ አበራ በድጋሚ ከአንድ ዓመት በኋላ ወደ ቀደምው ክለቧ ተመልሳለች፡፡ የቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ እና መከላከያ ተከላካይ ኤሌክትሪክን ለቃ የተጠናቀቀውን ዓመት በአዳማ ካሳለፈች በኋላ ቀሪ ውል እየቀራት ከክለቡ ጋር ተለያይታ ማረፊያዋ በድጋሚ ኤሌክትሪክ ሆኗል፡፡

ኤደን ሽፈራው ሁለተኛዋ የክለቡ አዲስ ፈራሚ ነች፡፡ የቀድሞ የደደቢት ፣ የመከላከያ እና አዲስ አበባ የአማካይ ስፍራ ተጫዋች ያለፈውን ዓመት በአዳማ አሳልፋ መዳረሻዋ ኤሌክትሪክ ሆኗል። ህይወት ደንጊሶም ከረጅም ዓመታት የንግድ ባንክ ቆይታ በኋላ ከክለቡ ጋር በመለያየት ማረፊያዋ ኤሌክትሪክ ሆኗል፡፡

የመሀል ተከላካዩዋ መስከረም ካንኮ ሌላኛዋ የቀይ እና ነጭ ለባሾቹ ፈራሚ መሆን ችላለች፡፡ በደደቢት ፣ አዳማ ከተማ እና ያለፈውን ዓመት ደግሞ በመከላከያ ያሳለፈችው ተጫዋቿ አዲሷ የኤሌክትሪክ ፈራሚ ሆናለች፡፡

ትዕግስት ያደታም ሌላኛዋ የአሰልጣኝ መሠረት ማኔ ምርጫ ሆና ኤሌክትሪክን ተቀላቅላለች፡፡ የቀድሞዋ የደደቢት የአማካይ ስፍራ ተጫዋች የሆነችው ትዕግስት ከአምስት ዓመታት በኋላ ከንግድ ባንክ ወደ ኤሌክትሪክ አምርታለች፡፡

በባህርዳር ከተማ እና በጌዲኦ ዲላ የተጫወተችው አጥቂዋ ሰብለወንጌል ወዳጆ ፣ የቀድሞው አርባምንጭ ከተማ ፣ የድሬዳዋ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ የመስመር ተከላካይ ፀሀይነሽ በቀለ ፣ በንግድ ባንክ እና በአዳማ ከተማ ተጫውታ ያሳለፈችው ግብ ጠባቂዋ እየሩሳሌም ሎራቶ ፣ በቅዱስ ጊዮርጊስ እና በንግድ ባንክ መጫወት የቻለችው የመስመር ተከላካዩዋ አለምነሽ ገረመው እንዲሁም የባህርዳር ከተማዋ አማካይ ሜላት ንጉሴም ክለቡን የተቀላቀሉ ተጫዋቾች ናቸው፡፡

ክለቡ ከአዳዲስ ፈራሚዎች በተጨማሪ የ11 ነባሮቹን ውልም አድሷል፡፡ ማርታ በቀለ ፣ ዙለይካ ጁሀድ ፣ ገነት ኤርሚያስ ፣ ትንቢት ሳሙኤል ፣ አይናለም አሳምነው ፣ ምንትዋብ ዮሃንስ ፣ ሰላማዊት ጎሳዬ ፣ ትዕግስት ሀይሌ ፣ ዘለቃሽ አሰፋ ፣ ቤተልሄም አስረሳኸኝ ፣ ፀጋነሽ ተሾመ እና ሀብታም እሸቱን ውል ያራዘሙ ተጫዋቾች ናቸው፡፡