ከፍተኛ ሊግ | ሀላባ ከተማ አዲስ አሰልጣኝ ሾሟል

በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ ተደልድሎ በደረጃ ሰንጠረዡ ስድስተኛ ላይ ተቀምጦ የፈፀመው ሀላባ ከተማ አዲስ አሰልጣኝ ቀጥሯል፡፡

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ረዘም ያለ የተሳትፎ ታሪክ ካላቸው ክለቦች መካከል የሚጠቀሰው ሀላባ ከተማ ከአሰልጣኝ ቾንቤ ገብረህይወት ጋር ከተለያየ በኋላ ለዘንድሮው የ2015 የውድድር ዘመን አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር ባወጣው ማስታወቂያ መሠረት የተቀመጠውን መስፈርት አሟልቷል ያለውን አሰልጣኝ ራህመቶ መሀመድን አዲሱ አሰልጣኝ አድርጎ መሾሙን ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ በላከው መረጃ አመላክቷል፡፡

የተጫዋቸነት ዘመኑን በአዳማ ከተማ እና ሙገር ሲሚንቶ ያደረገው እና ወደ አሰልጣኝነት ሙያው ከመጣ በኋላ በባቱ (ዝዋይ) ከተማ ረዳት አሰልጣኝ እንዲሁም ደግሞ የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ በመሆን በተለያዩ ጊዜያት ያገለገለው ራህመቶ በመቀጥለም በመቂ ከተማ እንዲሁም ደግሞ በሞጆ ከተማ ዋና አሰልጣኝ በመሆን ሰርቷል፡፡ በ2011 ነገሌ አርሲን አሰልጥኖ የነበረው እና በተጠናቀቀው ዓመትም በድጋሚ አርሲ ነገሌን እየመራ በከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ ላይ ክለቡን አስደናቂ ጉዞን እንዲያደርግ ያስቻለው አሰልጣኙ በቅርቡ የኦሮሚያ ከ17 ዓመት በታች ቡድንን እንዲሁም ደግሞ በሴካፋ ተሳታፊ የነበረውን የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ቡድን ረዳት አሰልጣኝ ሆኖ ካገለገለ በኋላ በይፋ የሀላባ አዲሱ አሰልጣኝ ሆኗል፡፡