በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የሁለተኛ ዙር ማጣርያ የመጀመሪያ ጨዋታ ሴፋክሲያንን ያስተናገዱት ፋሲል ከነማዎች 0-0 ተለያይተዋል።
በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ እና የግብ ዕድል በመፍጠሩ በኩል ፋሲል ከነማዎች የተሻሉ የነበሩ ሲሆን ጨዋታው በጀመረ አንድ ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሴፋክሲያኖች መሪ ሊሆኑ የሚችሉበት አጋጣሚ አግኝተው ነበር። በዚህም ከግራ መስመር ሁሴን ዓሊ ያሻማውን ኳስ በግንባሩ ለመግጨት ምቹ ቦታ ላይ የነበረው አሽራፍ ሀበሲ ኃይል ባልነበረው ኳስ ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል። 3ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ገዛኸኝ ከግራ መስመር ያቀበለውን ኳስ ተቀብሎ ከተጋጣሚ ሳጥን አጠገብ የነበረው በዛብህ መለዩ ድንቅ ሙከራ ቢያደርግም የላዩን አግዳሚ ገጭቶ ተመልሶበታል። ይህም አፄዎቹን ያስቆጨ የመጀመሪያ አጋጣሚ ነበር።
አፄዎቹ በተደጋጋሚ ከተጋጣሚ የግብ ክልል በቀላሉ መድረስ ሲችሉ 11ኛው ደቂቃ ላይ ሽመክት ጉግሳ ከቀኝ መስመር ያቀበለውን ኳስ በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያሳይ የነበረው ሀብታሙ ገዛኸኝ ከግራ መስመር ግሩም ሙከራ ቢያደርግም በጨዋታው ጥሩ ብቃት ሲያሳይ የነበረው የሴፋክሲያኑ ግብ ጠባቂ አይመን ዳህማን በሚገርም ፍጥነት ወደማዕዘን ሊያስወጣው ችሏል።
ወደራሳቸው የግብ ክልል ጥቅጥቅ ብለው በመጫወት በሚያገኙት ኳስ በመልሶ ማጥቃት የግብ ዕድል መፍጠር የመረጡት ሴፋክሲያኖች በ25ኛው እና 29ኛው ደቂቃ ላይ የተሻለ የግብ ማግባት ሙከራ ሲያደርጉ በቅደም ተከተል አብደላህ አምሪ ያሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ አሽራፍ ሀበሲ ከቀኝ መስመር ወደ ግብ የሞከረውና ሁሴን ዓሊ ከግራ መስመር ያቀበለውን ኳስ ያገኘው አብደላህ አምሪ ያደረጉትን ሙከራ ግብ ጠባቂው ሳማኪ ሚኬል መመለስ ችሏል።
አፄዎቹ በተደጋጋሚ ከተጋጣሚ የሜዳ ክልል መድረስ ሲችሉ 36ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር ዓለምብርሃን ይግዛው ሲያሻማ መሐመድ ናስራኦው በእጁ በመንካቱ የተሰጠውን የቅጣት ምት ታፈሰ ሠለሞን ከቀኝ መስመር ሲያሻማ ሀብታሙ ገዛኸኝ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገው ያልታሰበ ሙከራ የላዩን አግዳሚ ታክኮ ወጥቶበታል። በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት ዓለምብርሃን ይግዛው ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ሀብታሙ ገዛኸኝ በተመሳሳይ በግንባሩ ገጭቶ ድንቅ ሙከራ ቢያደርግም ግብ ጠባቂው በድንቅ ብቃት መልሶታል። ይሄም በዐፄዎቹ በኩል ሌላኛው አስቆጪ ሙከራ ነበር።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው እጅግ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል ሴፋክሲያኖች ነጥቧን አስጠብቀው ለመውጣት ሲሞክሩ በአፄዎቹ በኩል ነጻ የግብ ዕድል ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል። 57ኛው ደቂቃ ላይ የሴፋክሲያኑ ማህሙድ ሆርቤል በቀኝ መስመር የተገኘውን የማዕዘን ምት ለአሽራፍ ሀበሲ ሲያቀብል አሽራፍ ሀበሲ ያደረገውን ግሩም ሙከራ ግብ ጠባቂ ሊያስወጣበት ችሏል። መሀል ላይ የግብ ዕድል ለመፍጠር የተቸገሩት አፄዎቹ ሱራፌል ዳኛቸውን በታፈሰ ሰለሞን ቀይረው ቢያስገቡም ሱራፌል ከጉዳቱ ባለማገገሙ እና ለጨዋታው ዝግጁ ባለመሆኑ ያሰቡት ዕቅድ ሳይሰምርላቸው ቀርቷል።
64ኛው ደቂቃ ላይ የሴፋክሲያኑ ግብጠባቂ ያሻማውን ኳስ ያገኘው መናፍ ዐወል ወደ ወደ ኋላ በመግጨት ለግብ ጠባቂው ሲያቀብል በተፈጠረው አለመግባባት ኳሱ መረቡ ላይ ያርፋል ተብሎ ሲጠበቅ የላዩን አግዳሚ ገጭቶ ሊወጣ ችሏል። ከዕረፍት መልስ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተቃራኒው የግብ ዕድል ለመፍጠር የተቸገሩት አፄዎቹ የተሻለውን ሙከራ ያደረጉት 70ኛው ደቂቃ ላይ ሲሆን በግራ መስመር የተገኘውን የማዕዘን ምት ሱራፌል ዳኛቸው ሲያሻማ ፍቃዱ ዓለሙ በግንባሩ በመግጨት ሙከራ ቢያደርግም ግብጠባቂው በቀላሉ ይዞታል።
በጨዋታው ልዩነት ለመፍጠር የሞከረው ግን ጉዳቱን ተቋቁሞ መጫወት ያልቻለው ሱራፌል ዳኛቸው ለ23 ደቂቃዎች ብቻ ሜዳ ላይ ቆይቶ 81ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ ሊወጣ ችሏል። ወደመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ሴፋክሲያኖች ደቂቃ ለመግደል የሚያደርጉት ጥረት ተጨምሮ ጨዋታውም እጅግ አሰልቺ እየሆነ ሲሄድ የተሻለ የግብ ሙከራ ሳንመለከትበት ያለግብ አቻ ተጠናቋል።
የመልሱ ጨዋታ በመጪው ቅዳሜ ቱኒዚያ ላይ ይደረጋል።