ፋሲል ከነማ ከቱኒዚያው ሴፋክሲያንን ጋር ያለ ጎል ካጠናቀቀበት ጨዋታ ፍፃሜ በኋላ አሰልጣኝ ኃይሉ ነጋሽ እና የሴፋክሲያን የአሰልጣኞች ቡድን አባል አካል የሆነው የሱፍ ከሬይ ድህረ ጨዋታ አስተያየትን ሰጥተዋል፡፡
“በመልሱ ጨዋታ ያሉንን ክፍተቶች አርመን የተሻለ ነገር ይዘን ለመምጣት እንጥራለን” አሰልጣኝ ኃይሉ ነጋሽ
ስለ ጨዋታው እና ሜዳ ላይ ስለ ነበረው እንቅስቃሴ…
“ጨዋታውን እንደጠበቅነው ቡድኑ ታክቲካል ዲሲፕሊን እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ረጃጅም ኳሶችን እንደሚጫወቱ እንጠብቅ ነበር። ያንን መሰረት ያደረገ ነው ዝግጅት አድርገን የነበረው ነገር ግን ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች አለመጠቀም 0ለ0 እንድንወጣ አድርጎናል፡፡ በሳይኮሎጂ ደረጃ ልጆቹ ላይ የፈጠረው ነገር የለም ግን ሜዳችን ላይ ያለንን ነገር ጨርሰን መሄድ እና ከጉጉት አንፃር እንጂ ሌላ የተለየ ነገር የለም፡፡ በመልሱ ጨዋታ ያሉንን ክፍተቶች አርመን የተሻለ ነገር ይዘን ለመምጣት እንጥራለን፡፡
የተገኙትን ዕድሎች በአግባቡ ያለ መጠቀም…
“ብዙ ጊዜ ተጫዋቾች አሸነፈን እዚህ ጨርሰን እንሄዳለን የሚል ጉጉት ስለነበራቸው የማጥቃት ዕድሉ ላይ ትንሽ የመቻኮል ነገሮች ነበሩ፡፡ መጀመሪያም ጎል መሳት ያገኘነውን አጋጣሚ ያለመጠቀም ደግሞ ትንሽ እየወረድን እንድንመጣ አድርጎናል፡፡ እነዚህን ስህተቶች አርመን ለቀጣዩ ጨዋታ የተሻለ ነገር ይዘን እንቀርባለን ብለን እናስባለን፡፡
ሱራፌል ዳኛቸው ተቀይሮ ገብቶ በጉዳት ተቀይሮ ስለ መውጣቱ…
“ከጉዳት ነው የመጣውን እናውቃለን፡፡ ግን መጠነኛ መሻሻሎች ስለነበሩት ለዛም ነው በመጀመሪያው ቋሚ ያላሰለፍነው። ጥሩ ስሜት እንደሚሰማው ከህክምና ባለሙያው ስለደረሰን ለማየት ሞክረናል ፤ ግን በሽታው አገርሽቶበት ሊወጣ ችሏል፡፡ እንግዲህ ብዙ ልጆች ስላሉን እነርሱን ተክተን በቀጣይ ላለው ጨዋታ እንዘጋጃለን፡፡
ፍቃዱ አለሙን ተክቶ ጋይራ ጁፍ ተቀይሮ ያለመግባቱ…
“ከፍቃዱ ይልቅ አማካይ ላይ ነው ሳሳስተን የነበረው። ምክንያቱም እነርሱ ወርደው ስለሚጫወቱ ኳስ የሚያቀናጅ ነው እንጂ ፊት ላይ ፍቃዱ የተሻለ ነበር። እንደውም ማድረግ ከሚገባው ሄዶ ነበር ፤ ግን መሀል ላይ ሰዎችን ስላጣን ማድረግ ያለብንን አላደረግንም፡፡
መሀል ሜዳው መስተካከል ስላልቻለበት ምክንያት…
“ወርዶ ለሚጫወት ቡድን ብዙ መሮጥ ያስፈልግሀል፡፡ ብዙ ቦታዎችን መፍጠር ይጠበቅብሀል እና ብዙ ስለሮጥን ድካም ይኖራል እና ከእዛ የተነሳ ተጫዋቾችን አጥተናቸዋል፡፡”
“ለቀጣዩ ጨዋታ ጥሩ ውጤት አግኝተናል” የሱፍ ከሬይ የሴፋክሲያን የአሰልጣኝ ቡድን አባል
ስለ ጨዋታው …
“ጨዋታው ጥሩ ነበር ስፖርታዊ ጨዋነት የተሞላበት ጨዋታ የነበረ ሲሆን አቻ ወጥተናል። ለቀጣዩ ጨዋታ ጥሩ ውጤት አግኝተናል። በሁለቱም ቡድኖች በኩል ፉክክር የታየበት ፈታኝ ጨዋታ ነበር አቻም በቂ ውጤት ነው።
ፋሲል ከነማን እንደጠበቁት ስለማግኘታቸው…
“ትናንት እንዳልኩት ጠንካራ ቡድን ነው። በተለይ በሜዳው እና በደጋፊው ፊት ፈታኝ ነበር። ላላቸው ብቃት እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ።
በሁለቱም አጋማሽ ስላስተዋሉት ልዩነት…
“አብዛኛው ከአካል ብቃት ጋር የተያያዘ ነው። የነበረው የአየር ሁኔታ ለቱኒዚያውያን ተጫዋቾች ፈታኝ ነበር ፤ በሁለተኛው አጋማሽ ይበልጥ እሱ አስቸግሮናል።
ስለ ፋሲል ከነማ ደጋፊዎች እና ስለሜዳው…
“አስደናቂ ደጋፊዎች ናቸው። ሙሉ ደቂቃ ቡድናቸውን ሲያበረታቱ ነበር ስታዲየሙ ውስጥ ጥሩ ነበሩ። ሜዳውም ተመችቶናል በጣም ደስ ይላል ለጨዋታ የሚመች ሜዳ ነው። ስታዲየሙ በጣም ደስ ይላል ጥሩ ብቃት ያየንበት ጨዋታም ነበር ፤ ያለው ነገር ደስ ይላል።
በውጤቱ ደስተኛ ስለመሆናቸው…
“አቻ ውጤት አያስደስትም። ግን የመጀመሪያ ዙር እንደመሆኑ ለኛ ጥሩ ውጤት ሊሆን ይችላል።
በመልሱ ጨዋታ ምን እንጠብቅ…
“ዛሬ እንዳየነው ከሆነ ፈታኝ ጨዋታ ነው የሚሆነው። በቀጣይ ሴፋክሲያን (ቱኒዚያ) ላይ እንጠብቃችኋለን። ለሁለቱም ቡድኖች በስፖርታዊ ጨዋነት የተሞላ ጥሩ ጨዋታ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ።”