በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ከሁለት ቀናት ዕረፍት በኋላ ሲቀጥል ኢትዮጵያ ቡና እና ሀዋሳ ከተማ የሚያደርጉትን ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎችን አሰናድተናል።
በነገው ዕለት 10 ሲል በሚጀምረው የዕለቱ ብቸኛ መርሐግብር በመጀመሪያ ጨዋታቸው ከወላይታ ድቻ ነጥብ የተጋሩትን ኢትዮጵያ ቡናዎችን በተቃራኒው በመጀመሪያ የጨዋታ ሳምንት በአዲስ አዳጊው ለገጣፎ ለገዳዲ የተሸነፉትን ሀዋሳ ከተማዎችን ያገናኛል። ጨዋታውም ሁለቱም ቡድኖች የመጀመሪያ ሙሉ ሦስት ነጥባቸውን ለማስመዝገብ ብርቱ ፉክክር እንደሚያደርጉበት ይጠበቃል።
በአሰልጣኝ ተመስገን ዳና የሚመሩት ቡናማዎቹ በመጀመሪያ ጨዋታቸው 63% የኳስ ቁጥጥር ድርሻ ቢይዙም በጨዋታው የግብ ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ ግን ፍፁም ደካማ ነበሩ። በድቻው ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ መጠነኛ መሻሻሎች ቢኖሩም የቡድኑ ማጥቃት ፍፁም ጠባብ ሆኖ ተመልክተነዋል። የነገውም ተጋጣሚያቸው ሀዋሳ ከተማም በተለይ በሰንጠረዡ ከወገብ በላይ ያሉ ተጋጣሚዎችን ሲገጥም በጥልቀት የመከላከል ፍላጎት ያለው ቡድን እንደመሆኑ የሜዳውን ስፋት በመጠቀም ረገድ ኢትዮጵያ ቡናዎች ተሻሽለው መቅረብ ይኖርባቸዋል። ከዚህም ባለፈ ከመጀመሪያው ጨዋታ በተሻለ የተነጠሉ ይመስሉ የነበሩትን አጥቂዎቻቸውን ይበልጥ በጨዋታ እንቅስቃሴ ላይ እንዲሳተፉ ማስቻልም ይጠበቅባቸዋል።
ሀዋሳ ከተማዎች መርተው በተሸነፉበት የለገጣፎው ጨዋታ ያስተናገዷቸው ሁለት ግቦች በቀጥታ ከተጫዋቾች ስህተት የተነሱ እንደመሆናቸው ቡድኑ ከኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ አውንታዊ ውጤት ይዞ ለመውጣት ካሰበ እነዚህን ስህተቶችን መቀነስ ይኖርባቸዋል። ምንም እንኳን በመጀመሪያው ጨዋታ ነጥብ ቢጥሉም በጨዋታው በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ያሳዩትን እንቅስቃሴ አሳድገው መምጣት የሚችሉ ከሆነ ለኢትዮጵያ ቡና ቀላል ተጋጣሚ እንደማይሆኑ ይጠበቃል።
ሌላኛው በጨዋታው ዙርያ ትልቁ መነጋገርያ የሚሆነው ጉዳይ ባለፉት ዓመታት የሀዋሳ ከተማን ማጥቃት ይዘውሩ የነበሩት እና አሁን ላይ የኢትዮጵያ ቡና ንብረት የሆኑት ብሩክ በየነ እና መስፍን ታፈሰ የቀድሞ ክለባቸውን በተቃራኒ የመግጠማቸው ነገር ሲሆን በተመሳሳይ ተመስገን ዳናም ብዙ ያሳለፈበትን የቀድሞ ቤቱን ለሁለተኛ ጊዜ በተቃራኒ የመግጠሙ ነገር ትኩረት የሚስብ ጉዳይ ነው።
ኢትዮጵያ ቡናዎች ለነገው ጨዋታ በሙሉ ስብስብ የሚቀርቡ ሲሆን በተመሳሳይ ሀዋሳ ከተማዎች ቅጣት ላይ ከሚገኘው የመሀል ተከላካያቸው በረከት ሳሙኤል ውጪ በሙሉ ስብስብ እንደሚቀርቡ ይጠበቃል።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለ46 ጊዜያት የተገናኙ ሲሆን ዕኩል 15 ጊዜያት ሲሸናነፉ ቀሪዎቹ 16 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።
ይህን ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ በመሀል ዳኝነት ሲመሩት ለዓለም ዋሲሁን እና ወጋየሁ አየለ ረዳቶች ሲሆኑ ኢንተርናሽናል ዳኛ ሀይለየሱስ ባዘዘው ደግሞ አራተኛ ዳኛ ናቸው።