የካፍ ኮንፌዴሬሽን የመልስ ጨዋታቸውን በሳምንቱ መጨረሻ የሚያደርጉት ፋሲል ከነማዎች ወሳኝ ተጫዋቻቸውን የማግኘታቸው ነገር ያከተመ ይመስላል።
ባሳለፍነው እሁድ በባህር ዳር ስታዲየም
የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ 2ኛ ዙር ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታቸውን ከቱኒዚያው ሴፋክሲያን ጋር አድርገው ያለ ጎል ያጠናቀቁት ፋሲሎች ለመልሱ ጨዋታ ዛሬ ጉዛቸውን ያደርጋሉ። ስለጉዛቸው ጠቅለል ያለ መረጃ ከቆይታ በኋላ የምናጋራቹ ቢሆንም ሶከር ኢትዮጵያ አሁን ባገኘችው መረጃ የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች ሱራፌል ዳኛቸው ከቡድኑ ጋር አብሮ የመጓዙ ነገር አጠራጣሪ መሆኑ ተመላክቷል።
በመጀመርያው የእሁዱ ጨዋታ አስቀድሞ መጠነኛ ጉዳት አጋጥሞት ለጨዋታው የመድረሱ ነገር ሲያጠራጥር ቢቆይም በ59ኛው ደቂቃ ተቀይሮ በመግባት መጫወት የቻለው ተጫዋቹ ሜዳ ላይ መቆየት የቻለው ግን ሃያ ደቂቃ ብቻ ነበር ፤ ቀኝ ታፋው ላይ ከበድ ያለ ጉዳት አስተናግዶ ተቀይሮ ሊወጣ ችሏል። ከዚህ ጉዳት መነሻነት የተለየ ነገር እስካልተፈጠረ ድረስ ሱራፌል ዳኛቸው የጤናው ሁኔታ መሻሻል ባለማሳየቱ ወደ ቱኒዚያ ከሚያቀናው ስብስብ ውጭ እንደሆነ አውቀናል።