የፋሲል ከነማ የቱኒዚያ ጉዞ ወቅታዊ መረጃዎች

ፋሲል ከነማዎች በሳምንቱ መጨረሻ ላለባቸው የካፍ ኮንፌዴሬሽን የሁለተኛ ዙር ማጣሪያ የመልስ ጨዋታ ወደ ቱኒዚያ የሚያደርጉትን ጉዞ አስመልክቶ ወቅታዊ መረጃ እናጋራቹሁ።

የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ 2ኛ ዙር ቅድመ ማጣሪያ ላይ የደረሱት ዐፄዎቹ የመጀመርያ ጨዋታቸውን ባሳለፍነው እሁድ ከቱኒዚያው ክለብ ሴፋክሲያን ጋር በባህር ዳር ስታዲየም አከናውነው ያለ ጎል አቻ መለያየታቸው ይታወሳል።

ፋሲሎች ዛሬ ማለዳ የመጨረሻ የሀገር ቤት ልምምዳቸው በባህር ዳር ሰርተው ያጠናቀቁ ሲሆን በጉዳት ላይ ከሚገኘው ሱራፌል ዳኛቸው በስተቀር ሁሉም የቡድኑ አባላት በልምምዱ ላይ ተሳትፎ ማድረጋቸው ታውቋል። ከደቂቃዎች በኋላ አዲስ አበባ እንደሚገቡ የሚጠበቁት ዐፄዎቹ በመዲናዋ ማረፊያቸውን ካደረጉ በኋላ ለሊት 10 ሰዓት የቱኒዚያ ጉዛቸውን የሚያጀምሩ ይሆናል።

የቡድኑ አባላት በግብፅ በኩል ትራንዚት በማድረግ መዳረሻቸውን ቱኒዚያ ሲያደርጉ ተጫዋቾችን ጨምሮ ከ30 በላይ የልዑክ ቡድን ወደ ስፍራው እንደሚያቀናም ተመላክቷል። ቅዳሜ የመልስ ጨዋታቸውን እስከሚያደርጉ ድረስ በቡድኑ ዙርያ የሚኖሩ አዳዲስ መረጃዎች እየተከታተልን እንደምናቀርብም ከወዲሁ መግለፅ እንወዳለን።