በሱዳን አስተናጋጅነት የሚደረገው የሴካፋ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ውድድር ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን የሚመሩ አሰልጣኞች ታውቀዋል፡፡
በሱዳን አስተናጋጅነት የሚደረገው የሴካፋ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ውድድር በሰባት ሀገራት መካከል ከጥቅምት 12 – 23 ድረስ ይከናወናል፡፡ በዚህ ውድድር ላይ የሚካፈለው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድንን የሚመሩ ዋና እና ረዳት አሠልጣኞች መሾማቸውንም ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡
የኢትዮጵያ ቡና አንበል በመሆን የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ያነሳው እና ወደ አሰልጣኝነቱ ካመራ በኋላ በደብረ ብርሃን ከተማ እንዲሁም ባለፈው ዓመት ደግሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ20 ዓመት በታች አሰልጣኝ የነበረው ዕድሉ ደረጀ የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ሆኖ ተሹሟል። በቅዱስ ጊዮርጊስ የተከላካይ ስፍራ ላይ በመጫወት በርከት ያሉ ዋንጫዎችን ያነሳው እና እግር ኳስን ካቆመ በኋላ የቅዱስ ጊዮርጊስ ከ20 እና ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆኖ በማገልገል ላይ የሚገኘው ሳምሶን ሙሉጌታ (ፍሌክስ) እና በአዳማ ከተማ ወጣት ቡድን ውስጥ ረጅም ዓመታትን ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ቡድኖችን በማሰልጠን ተስፈኛ ወጣቶችን ያፈራው አፈወርቅ ከበደ ሌላኛው የረዳት አሰልጣኝ ቡድን አባል መሆን ችሏል፡፡
ሱማሊያ እና ሩዋንዳ ራሳቸውን በማግለላቸው እንዲሁም ኤርትራ መሳተፏን ባለመግለጿ እና ኬኒያ በፊፋ በመታገዷ ምክንያት ውድድሩ አስተናጋጇ ሱዳንን ጨምሮ ዩጋንዳ ፣ ጅቡቲ ፣ ብሩንዲ እና ታንዛኒያ መካከል ይደረጋል። በውድድሩ ላይ አሸናፊ የሆነው ሀገራት የአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ላይ የሚሳተፍ ይሆናል፡፡