ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | የ2ኛ ሳምንት ምርጥ 11

በተስተካካይ መርሐ-ግብር ከተያዘው የወላይታ ድቻ እና ፋሲል ከነማ  ጨዋታ ውጪ በተደረጉ የ2ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች ላይ የታዩ ምርጥ ተጫዋቾችን እንደሚከተለው መርጠናል።

የተጫዋች አደራደር ቅርፅ – 3-4-1-2

ግብ ጠባቂ


ጀማል ጣሰው – ወልቂጤ ከተማ

ወልቂጤ ከተማ በባህር ዳር ላይ ባሳካው ድል ውስጥ ግብ ሳይቆጠርበት መውጣቱ ትልቅ አስተዋፅኦ ነበረው። በዚህ ረገድ ሦስት የመጨረሻ ግብ ለመሆን የቀረቡ ኳሶችን ያዳነው ግብ ጠባቂው ጀማል ንቃት እና ከስህተቶች የራቀ ግብ አጠባበቅ የ1-0ው ውጤት እንዳይቀየር ትልቅ ሚና ነበረው።

ተከላካዮች


ሚሊዮን ሰለሞን – አዳማ ከተማ

መቻል ከወገብ በላይ ባለው የተጨዋቾች ጥራት አዳማ 2-0 በረታው ጨዋታ ላይ የአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅት የሚኖሩ ውሳኔዎች አስፈላጊው ነበሩ። ለዚህም ሚሊዮን አስፈላጊው ቦታ ላይ በመገኘት ኳሶችን ያቋርጥ የነበረበት መንገድ ቡድኑን በሚገባ ጠቅሟል።

ፀጋአብ ዮሐንስ – ሀዋሳ ከተማ

በመጀመሪያው የለገጣፎ ጨዋታ ግለሰባዊ እና መዋቅራዊ ስህተቶች የነበሩበት የሀዋሳ የተከላካይ ክፍል በዚህ ሳምንት ተሻሽሎ እንዲመጣ የፀጋአብ ብቃት ወሳኝ ነበር። በዐየር ላይም ሆነ በመሬት ላይ የአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ጠንካራ የነበረው ተጫዋቹ በተለይ ፈጣኖቹ የቡና አጥቂዎች በምቾት ጥቃቶችን እንዳይሰነዝሩ ከአጣማሪው ሰለሞን ጋር ጥሩ ሚና ሲወጣ ተመልክተናል።

ፍሪምፖንግ ሜንሱ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከተገመተው በላይ ቻምፒዮኖቹን በፈተነበት ጨዋታ ጋናዊው ተከላካይ የተለመደ ጥሩ አቋሙን አሳይቷል። በመከላከሉ ረገድ ኤሌትሪክ እንደነበረው ብልጫ በርካታ ዕድሎችን እንዳይፈጥር በማድረግ ከነበረው ሚና በላይም እጅግ ወሳኝ የሆነችውን ብቸኛ ግብ በማስቆጠር ለቡድኑ ሦስት ነጥብ አስጨብጧል።

አማካዮች


ሳለአምላክ ተገኘ – ባህር ዳር ከተማ

የጣናው ሞገድ በወልቂጤ ሽንፈተን ያስተናግድ እንጂ ውጤቱን ለመቀልበስ በግላቸው ጥሩ የተንቀሳቀሱ ተጫዋቾች አልጠፉም። የቀኝ መስመር ተከላካይ ሆኖ የተሰለፈው ሳለአምላክ በዚህ በኩል ተጠቃሽ ሲሆን በተለይም በማጥቱ ረገድ በተሻጋሪ ኳሶች ሦስት ለግብ የቀረቡ ዕድሎችን መፍጠር ችሎ ነበር።

አብዱልባሲጥ ከማል – ሀዋሳ ከተማ

በመጀመሪያው የሀዋሳ ጨዋታ ተሳትፎ ያላደረገው አብዱልባሲጥ በዚህ ሳምንት ቡድኑ ወሳኙን 3 ነጥብ እንዲያገኝ እጅግ ከፍ ያለ ድርሻ ተወጥቷል። ተጫዋቹ ወሳኟን የመጀመሪያ ጎል በድንቅ ሁኔታ ከማስቆጠሩ በተጨማሪ ዘለግ ያለ ደቂቃ ከኳስ ውጪ ለነበረው ቡድኑ ሽፋን በመስሳተት ጥቃቶች እንዳይሰነዘሩ በከፍተኛ ታታሪነት ተከላካዮቹን ሲያግዝ ነበር።

ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን – ሀዲያ ሆሳዕና

ሀዲያ ሆሳዕና ከመመራት ተነስቶ የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ድል ሲያገኝ አስደናቂ እንቅስቃሴ ያደረገው ፍቅረየሱስ የምርጥ ቡድናችን አካል ሆኗል። ተጫዋቹ ቡድኑን መሪ ያደረገች ድንቅ ጎል ከማስቆጠሩ በተጨማሪ ፀጋዬ ብርሃኑ ከመረብ ያሳረፈውን ኳስ አመቻችቶ አቀብሏል።

ተመስገን ደረሰ – አርባምንጭ ከተማ

አርባምንጭ ከተማ ምንም እንኳን በጨዋታ ሳምንቱ በመድን ሽንፈት ቢያስተናግድም በግሉ ዋነኛ ኃላፊነቱ የሆነውን ግብ ማስቆጠር ሲወጣ የነበረው ተመስገን ከዚህ በፊት በሚጫወትበት የመስመር ተመላላሽ ቦታ ላይ በምርጥ ቡድናችን አስገብተነዋል። ተመስገን ቡድኑን ወደ መሪነት የወሰዱ ግቦችን ከማስቆጠሩ በተጨማሪም የመጀመሪያው የአሸናፊ ጎል እንዲገኝ የበኩሉን ተወጥቷል።

ተፈራ አንለይ – ለገጣፎ ለገዳዲ

በአዲስ አዳጊዎቹ ለገጣፎዎች ሁለተኛ ድል ለማስመዝገብ ተቃርበው በነበረበት ጨዋታ ተፈራ በልዩነት ታይቷል። በመጀመሪያው ጨዋታ ቀዳሚ አሰላለፍ ውስጥ ያልነበረው የጨዋታ አቀጣጣዩ የቡድኑን ግብ ክህሎቱን ባሳየ አኳኋን ሲያመቻች በለገጣፎ የማጥቃት ሂደቶች ላይ ዋና ተሳታፊ በመሆን ተጨማሪ ያለቀለት የግብ ዕድልም ሲፈጥር ታይቷል።

አጥቂዎች


ኪቲካ ጅማ – ኢትዮጵያ መድን

በቋሚነት በሀገራችን ከፍተኛ የሊግ እርከን የመጀመሪያ ተሳትፎውን ያደረገው ኪቲካ እጅን አፍ ላይ የሚያስጭን ብቃት በማሳየት ቡድኑ ለተዐምርነት በቀረበ ሁኔታ ባገኘው ድል ተጠቃሽ ነበር። በዚህም ማሸነፊያ በሆኑት አራቱም ግቦች ላይ አንዱን በማስቆጠር ሦስቱን አመቻችቶ በማቀበል ስሙን በጉልህ አፅፎ ወጥቷል።

ባዬ ገዛኸኝ – ሀዲያ ሆሳዕና

ሌላኛው በሀዲያ ድል ጎልቶ የወጣው ተጫዋች ባዬ ገዛኸኝ ነው። ፈጣኑ አጥቂ በሲዳማው ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ እምብዛም በእንቅስቃሴዎች ሲሳተፍ ባንመለከተውም በሁለተኛው አጋማሽ ግን የማጥቃት እንቅስቃሴው አውራነቱን በሚገባ ሲያሳይ ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ ከተቆጠሩት አራት ጎሎችም አንዱን ሲያስቆጥር አንዱን አመቻችቶ በማቀበል እንዲሁም በአንዱ በመጨረሻ እንቅስቃሴ ተሳትፎ ጣፋጩ የቡድኑ ድል እንዲገኝ አስችሏል።

አሠልጣኝ


ይታገሱ እንዳለ – አዳማ ከተማ

አምና ወደ ዋና አሰልጣኝ መንበር የመጡት የቀድሞው የአዳማ ከተማ ተወዳጅ ተጫዋች መቻልን 2-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል። በተደራጀ አጨዋወት ክፍተቶችን በመዝጋት የተጋጣሚያቸውን ጥንካሬ በመቋቋም ፈጣን ጥቃቶችን የመሰንዘር የጨዋታ ዕቅዳቸው ሰምሮላቸው ግብ ሳይቆጠርባቸው ጨዋታውን ማገባደዳቸው የሳምንቱ ምርጥ አሰልጣኝ ብለን እንድመርጣቸው አድርጓል።

ተጠባባቂዎች

ፍሬው ጌታሁን – ድሬዳዋ ከተማ
ዳግም ንጉሴ – ሀዲያ ሆሳዕና
ጀሚል ያቆብ – አዳማ ከተማ
አብነት ደምሴ – ኢትዮ ኤሌክትሪክ
ኦኬይ ጁል – ለገጣፎ ለገዳዲ
ብሩክ ማርቆስ – ሀዲያ ሆሳዕና
ተመስገን በጅሮንድ – ወልቂጤ ከተማ
አሜ መሐመድ – አዳማ ከተማ