ሦስተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታን የተመለከተ መረጃ

የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሦስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገ ጅማሯቸውን ሲያደርጉ የጨዋታ ሳምንቱ የመክፈቻ ጨዋታ የሆነው የመቻል እና አርባምንጭ ከተማን የተመለከቱ መረጃዎችን አሰናድተናል።

አርባምንጭ ከተማ ከ መቻል

ፍፁም በተለያየ መንገድ ክረምቱን ያሳለፉት ሁለቱ ቡድኖች የሊጉ አጀማመራቸው በተጠበቀው ልክ አልሆነላቸውም። ጥቂት ተጫዋቾችን በማስፈረም የውድድር ዘመኑን የጀመሩት አርባምንጭ ከተማዎች በመጀመሪያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ሽንፈትን ሲያስተናግዱ በተቃራኒው በርከት ያሉ ጥራታቸው የላቁ ተጫዋቾችን ያዘዋወሩት መቻሎች አንድ ሲያሸንፉ በቀሪው አንድ ጨዋታ ደግሞ ሽንፈትን አስተናግደዋል።የነገው 10 ሰዓት ጨዋታም ለሁለቱ ቡድኖች በተለያየ መንገድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጡት ነው ፤ አርባምንጮች የሊጉ የመጀመሪያ የሊግ ነጥባቸውን ፍለጋ እንዲሁም መቻሎች ደግሞ ከመጨረሻው ሽንፈታቸው ለማገገም የሚያደርጉት ጨዋታ እንደመሆኑ የሚጠበቅ ይሆናል።

አዞዎቹ ምንም እንኳን እስካሁን ነጥብ መያዝ ባይችሉም እንቅስቃሴያዎቻቸው ግን ለክፉ የሚሰጡ አልነበሩም። ምንም እንኳን ተስፋ ሰጪ ነገሮችን ቡድኑ ቢያስመለክተንም ይህን ሂደት በሙሉ ዘጠና ደቂቃ በማስቀጠል ረገድ ውስንነቶች እንዳሉበት መዘንጋት የለበትም በ90 ደቂቃ ውስጥ የተለያዩ መልኮችን የሚያሳየው ቡድኑ በሙሉ የጨዋታ ደቂቃዎች በተሻለ ብቃት መጫወት ከመጀመሪያ ነጥቡ ጋር የሚያስታርቀው ይሆናል። ከዚህ ባለፈ ለቡድኑ ማጥቃት የተለየ ነገር ይጨምራል ተብሎ ታሞኖበት አዞዎቹ ቤት የደረሰው ሁለገቡ ተመስገን ደረሰ ወደ ባለፈው ጨዋታ የግብ አካውንቱን መክፈቱ አርባምንጮች በዚህኛው ጨዋታ ከእሱ ብዙ የሚጠብቁ ሲሆን በመድኑ ጨዋታ ከገጠመው ጉዳቱ የማገገሙ ነገር ይበልጥ ደጋፊዎቹን ደስተኛ የሚያደርግ ዜና ሲሆን ከዚህ ቀደም ጉዳት ላይ የነበሩት በላይ ገዛኸኝ እና አንድነት አዳነ እንዲሁም ኤሪክ ካፓይቶ ግን አሁንም አላገገሙም።

እንደ አዲስ እየተገነባ የሚገኘው እና በብዙዎች ዘንድ በትልቁ ለተፎካካሪነት የሚጠበቀው መቻል አሁንም ብዙ ነገሮች እንደሚቀሩት ሁለቱ ጨዋታዎች በቂ ማሳያ ነበሩ። እርግጥ ቡድኑ ለመዋሃድ ገና ጊዜ እንደሚያስፈልገው ቢታመንም ነጥቦችን መያዝ ግን ለድርድር የሚቀርብ አለመሆኑን ተከትሎ ቡድኑ በዚህኛው ጨዋታ ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርግ ይጠበቃል።

በሊጉ በሁለቱ ጨዋታዎች በክፍት ጨዋታ ምንም ግብ ያላስቆጠረው ቡድኑ የኳስ ቁጥጥር ብልጫውን ወደ ግብ እድሎች በመቀየር ረገድ እጅግ ደካማ ሆነው የተመለከትን ሲሆን ቡድኑ ከወገብ በላይ ከያዛቸው ተጫዋቾች ጥራት አንፃር በፍጥነት መፍትሔ ማበጀት ይጠበቅበታል።በመቻል በኩል የቁርጭምጭሚት ጉዳት ካስተናገደው ቶማስ ስምረቱ ውጭ ቀሪው ስብስብ በሙሉ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ መሆኑ ተስምቷል።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለ16 ጊዜያት የተገናኙ ሲሆን መቻል 5 ጊዜ በአንፃሩ አርባምንጭ ከተማ ደግሞ 4 ጊዜ ባለድል መሆን ሲችሉ ቀሪዎቹ 7 ጨዋታዎች ደግሞ በነጥብ መጋራት የፈፀሙባቸው ነበሩ።

10 ሰዓት ላይ ጅማሮውን የሚያደርገውን ይህን ጨዋታ ኤፍሬም ደበሌ በመሀል ዳኝነት የሚመሩት ሲሆን ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ተመስገን ሳሙኤል እና እሱባለው መብራቱ ደግሞ ረዳቶቻቸው ሲሆኑ ኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ በአራተኛ ዳኛነት እንዲመሩ ተሰይመዋለሰ።