ከፍተኛ ሊግ | ጌዲኦ ዲላ የቀድሞው አሰልጣኙን ዳግም ሾሟል

በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በከፍተኛ ሊጉ ምድብ ሀ ተደልድሎ የነበረው ጌዲኦ ዲላ የቀድሞው አሰልጣኙን በድጋሜ ማግኘቱ ታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ በተጠናቀቀው የ2014 የውድድር ዘመን በምድብ ሀ ተደልድሎ በደረጃ ሰንጠረዡ 9ኛ ላይ ተቀምጦ ያጠናቀቀው እና ወደ አንደኛ ሊግ መውረዱ ተረጋግጦ የነበረው ጌዲኦ ዲላ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ወራጅ ክለቦች በከፍተኛ ሊጉ እንዲቀጥሉ ትዕዛዝ ማስተላለፉን ተከትሎ በሊጉ የመቀጠል ዕድል ማግኘቱ የሚታወቅ ሲሆን አሁን ደግሞ የቀድሞው አሰልጣኙ ደረጀ በላይን በድጋሜ መቅጠሩ ተረጋግጧል፡፡

በከፍተኛ ሊጉ የማሰልጠን ልምድ ካላቸው አሰልጣኞች መካከል የሚጠቀሱት የቀድሞው የሰበታ ከተማ ፣ ጅማ አባቡና ፣ ወልቂጤ ከተማ እና ሀላባ ከተማ አሰልጣኝ የነበሩት አሰልጣኝ ደረጀ በላይ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን አጋማሽ በፕሪምየር ሊጉ የሰበታ ከተማ ረዳት አሰልጣኝ ሆነው በቀድሞው ክለባቸው የሰሩ ሲሆን ለዘንድሮው የውድድር ዘመን ደግሞ ከ2011 ጀምሮ በኮቪድ-19 ምክንያት የከፍተኛ ሊግ ውድድር እስኪቋረጥ ድረስ አሰልጥነውት የነበረውን ጌዲኦ ዲላን በዋና አሰልጣኝነት ለአንድ ዓመት በድጋሚ ለማገልገል በይፋ ፊርማቸውን አኑረዋል።