ሪፖርት | አዞዎቹ የመጀመርያ ድላቸውን ሲያሳኩ መቻል ተከታታይ ሽንፈት አስተናግዷል

3ኛው የሊጉ የጨዋታ ሳምንት ዛሬ ሲጀምር አርባምንጭ ከተማ በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠሩ ግቦች መቻልን 2-1 ረቷል።

ከሽንፈት የመጡንት ሁለቱን ቡድኖች ባጣመረው በዚህ ጨዋታ መቻሎች በአዳማ ከተረቱበት ስብስባቸው የሦስት ተጫዋቾችን ለውጥ አድርገዋል። ቶማስ ስምረቱ ፣ በኃይሉ ግርማ እና ተሾመ በላቸውን በአሚኑ ነስሮ ፣ ተስፋዬ አለባቸው እና ሳሙኤል ሳሊሶን ተክተው ገብተዋል። አርባምንጭ ከተማዎች ደግሞ በመድን ሽንፈት ካጋጠማቸው ጨዋታ ከተጠቀሙባቸው ተጫዋቾች መካከል ይስሐቅ ተገኝ ፣ አዮብ በቀታ ፣ ሙና በቀለ ፣ ተመስገን ተስፋዬ እና አህመድ ሁሴንን አሳርፈው በአቤል ማሞ፣ ወርቅይታደስ አበበ ፣ በርናንድ ኦቼንግ ፣ አሸናፊ ፊዳ እና አሸናፊ አልያስ በመተካት ወደ ሜዳ ገብተዋል።

በፌደራል ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ የተመራው ጨዋታው በተያዘለት ሰዓት ይጀምራል ቢባልም ለደቂቃዎች ሊገፋ ችሏል። ለመዘግየቱ ምክንያቱ ለአርባምንጭ ከተማ የመጀመርያ ጨዋታውን ለማድረግ በቋሚ አስራ አንድ ውስጥ የተካተተው ግብ ጠባቂው አቤል ማሞ የለበሰውን የ99 ቁጥር መለያ እንዲቀይር ለማድረግ ቢታሰብም ለውጥ ሳያደርግ ወደ ሜዳ መመለስ ችሏል። ጨዋታውም ትንናት በሞት ያጣናቸውን ታላቁ የስፖርት ሰው ፍቅሩ ኪዳኔን በአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት በማሰብ ተጀምሯል።

የመጀመርያዎቹ ሀያ ደቂቃዎች የጠሩ የጎል ዕድሎችን ሳያስመለክተን ቢዘልቅም በመቻሎች በኩል ከጨዋታው አንድ ነገር ይዞ ለመውጣት በመፈለግ በተረጋጋ ሁኔታ ኳሱን ከራሳቸው የሜዳ ክፍል ይዘው በመውጣት ቢሳካላቸውም የመጨረሻው የሜዳ ክፍል ሲደርሱ ኳሱ እየተቆራረጠ በአርባምንጭ ተከላካዮች በቀላሉ ሲመለስባቸው አስተውለናል።

ብዙም ወደ ጎል መድረስ ላይ ያልተመለከትናቸው አዞዎቹ ባልታሰበ አጋጣሚ የጨዋታውን መልክ የሚቀይር ጎል በ23ኛው ደቂቃ ማስቆጠር ችለዋል። አምና ከ20 ዓመት በታች ቡድኑ ያደገው ቡጣቃ ሸመና ከሳጥን ውጪ አስደናቂ ሰንጣቂ ኳስ አቀብሎት አሸናፊ ኤልያስ በጥሩ አጨራረስ አዞዎቹን ቀዳሚ ያደረገች ጎል አስቆጥሯል።

በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ የነበራቸው መቻሎች ጎላቸው ቢደፈርም አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት ሰባት ደቂቃ ወስዶባቸዋል። አቤል ማሞ በትክክል ከግብ ክልሉ ሳያርቀው በመቅረቱ እና በርናንድ ኦቼንግ ኳስ በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ምንይሉ ወንድሙ በማስቆጠር መቻልን በ30ኛው ደቂቃ አቻ አድርጓል።

ከአቻነት ጎሉ በኋላ መቻሎች ብልጫ ወስደው ተጨማሪ ጎል ለማግኘት ጥረት ማድረጋቸውን ቀጥለው በ37ኛው ደቂቃ ከርቀት የተሰጠውን ቅጣት ምት ፍፁም ዓለሙ በጥሩ ሁኔታ ቢመታውም አቤል ማሞ እንደምንም ያዳነበት የጥረታቸው ማሳያ ነበር። በአንፃሩ አርባምንጮች በረጃጅም ኳሶች ወደ ፊት ለመሄድ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ያን ያህል አስፈሪ ባይሆንም የመቻሎችን የመከላከል ክፍተት ተጠቅመው በ44ኛው ደቂቃ ሁለተኛ ጎላቸውን አግኝተዋል። ለመጀመርያው ጎላቸው መቆጠር መነሻ የነበረው ቡጣቃ ሸመና ከተከላካይ ጀርባ የላከውን ተመስገን ደረሰ ኳሱ አየር ላይ እያለ ተስቦ በእግሩ ሁለተኛ ጎል ለቡድኑ ማስገኘት ችሏል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲቀጥል መቻሎች ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ጎል ለማግኘት የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን አጠናክረው ቢቀጥሉም ጥቅጥቅ ብለው የሚካላከሉትን አርባምንጮችን ማለፍ በመቸገራቸው ከሳጥን ውጪ ፍፁም ዓለሙ እና ተስፋዬ አለባቸው አማካኝነት በሚመቱ ኳሶች አደጋ ለመፍጠር ሞክረዋል። አርባምንጮች በአንፃሩ በጥልቀት እየተከላከሉ በሚቋረጡ ኳሶች አሸናፊ ኤልያስን ትኩረት በማድረግ የመቻልን የግብ ክልል ሲያስጨንቁ በመቆየት በጨዋታው ሂደት ወደ ሰባ ደቂቃ መድረስ ችለዋል።

በሁሉም የሜዳ ክፍል የአርባምንጭን መከላከል ለመስበር በሙሉ አቅማቸው የአቻነት ጎል ፍለጋ መቻሎች ብዙ ቢታትሩም ኳስና መረብን የሚያገናኝ ሁነኛ ሰው በማጣት ምንም ሳይፈይዱ ቀርተዋል። የሁለት ጨዋታ ሽንፈታቸውን ለመርሳት እና የድል ረሀባቸውን ለማስታገስ በከፍተኛ ተነሳሽነት ውጤቱን ለማስጠበቅ ሲታገሉ የቆዩት አዞዎቹ ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ ጨዋታውን 2-1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል።

መጀመርያ ሦስት ነጥባቸውን ያገኙት አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ እስካሁን ባሰቡት ልክ ቡድናቸው ባይሄድም የዛሬ እንቅስቃሴያቸው ጥሩ የሚባል ባይሆንም ወደ አሸናፊነት መምጣታቸው ቡድናቸውን ከጫና የሚያላቅቅ ስለ ሆነ ደስተኛ እንዳደረጋቸው ሲናገሩ ተሸናፊው አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በበኩላቸው ቡድናቸው ባሰቡት እና በፈለጉት መልኩ የሄደ ቢሆንም ሦስተኛ የሜዳ ክፍል ላይ የፈጠራ ችግር እና ያለመረጋጋት ነገር ለመሸነፋቸው እንደምክንያት ገልፀው በቀጣይ አስተካክለው እንደሚመጡ ተናግረዋል።