ታላቁ የስፖርት ሰው ፍቅሩ ኪዳኔ ሥርዓተ ቀብር እሁድ ይፈፀማል

ከሀገር ውስጥ አልፎ ዓለም አቀፍ የስፖርት ተቋማትን በኃላፊነት የመሩት ፍቅሩ ኪዳኔ የቀብር ሥነ ስርዓታቸው የሚካሄድበት ቦታ የታወቀ ሲሆን የመታሰቢያ መርሐግብርም ተዘጋጅቷል።

በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ ውስጥ ዘመን አይሽሬ ሥራዎችን በደራሲነት ፣ በጋዜጠኝነት ሙያ እና ዓለምአቀፍ የስፖርት ተቋማትን በኃላፊነት እስከ ህይወት ፍፃሜያቸው ድረስ በትጋት ያገለገሉት ታላቁ የእግርኳስ ሰው ጋሽ ፍቅሩ ኪዳኔ የዕረፍታቸው ዜና በትናት ዕለት መሰማቱ ይታወቃል።

ሶከር ኢትዮጵያ አሁን ባገኘችው መረጃ መሰረት ሥርዓተ ቀብራቸው የፊታች እሁድ ህይወታቸው ባለፈበት ፈረንሳይ ሀገር በፓሪስ ከተማ የሚፈፀም መሆኑን አውቀናል። የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበርም እሁድ ጥቅምት 6 ቀን ከጠዋቱ 03:00 ጀምሮ ፒያሳ በሚገኘው አራዳ ጊዮርጊስ ቅጥር ግቢ ውስጥ የመታሰቢያ መርሐ ግብር ማዘጋጀቱን ሰምተናል። በዕለቱም የተለያዩ ዓለማቀፍ ተቋማት ተወካዮች ፣ ታላላቅ የእግርኳሱ ሰዎች ፣ የክለቡ የቦርድ አመራሮች ፣ የፌዴሬሽኑ ተወካዮች እንዲሁም የክለቡ ደጋፊዎች በተገኙበት ስርዓተ ፀሎት ፣ የአበባ ጉንጉን የማስቀመጥ እና በእግርኳሱ የነበራቸውን አበርክቶ የሚተርክ የተለየዩ መሰናዶዎች እንደሚቀርቡ ተገልፆልናል።

ታላቁ የእግርኳስ ሰው በዕድሜ በቆዩባቸው ዓመታት ዓለምአቀፍ ታላላቅ ሽልማቶችን የተቀዳጁት ሲሆን ባለ ትዳር እና የልጅ አባት ነበሩ። ሶከር ኢትዮጵያ በታላቁ የስፖርት ሰው ህልፈተ ህይወት የተሰማትን ሀዘን ድጋሚ እየገለፀች በእርሳቸው የህይወት ታሪክ ዙርያ በቀጣዮቹ ቀናት ተከታታይ ዘገባዎችን ወደ እናንተ የምናደርስ መሆኑን ታሳውቃለች።

ያጋሩ