መረጃዎች | 10ኛ የጨዋታ ቀን

በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ነገ ከቀትር በኋላ የሚደረጉ የሦስተኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አጠናክረናል።

ወላይታ ድቻ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

በመጀመሪያው የጨዋታ ሳምንት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ተጫውተው ነጥብ የተጋሩት ወላይታ ድቻዎች የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ድል ለማግኘት ነገ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ይጠበቃል። በባህር ዳሩም ሆነ በቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ ባለቀ ሰዓት ግብ ተቆጥቶባቸው ሦስት ነጥብ ያስረከቡት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በበኩላቸው የናፈቃቸውን ድል ወላይታ ላይ ለማሳካት ጠንክረው እንደሚጫወቱ ይታሰባል።

በሁለተኛው ሳምንት ከፋሲል ከነማ ጋር እንዲጫወቱ መርሐ-ግብር ተይዞላቸው የነበሩት ድቻዎች ተጋጣሚያቸው አህጉራዊ ውድድር ስላነበረበት የጨዋታ ሳምንቱን በእረፍት አሳልፈዋል። ድቻ በዘንድሮውም የውድድር ዓመት የአጨዋወት ለውጥ ሳያደርግ እንደቀረበ በቡናው ጨዋታ በሚገባ የተመለከትን ሲሆን የማጥቃት ኃይሉን ግን ማሳደግ እንደሚጠበቅበት ተስተውሏል። እርግጥ ቡድኑ በረጃጅም እና የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ጥቃቶችን ለመሰንዘር ቢጥርም የመጨረሻው ሲሶ ላይ የአፈፃፀም እንከኖች በጥቂቱ ነበሩበት። ምናልባት በአቀራረብ ደረጃ ይህንኑ ምርጫ ተከትሎ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ሲጠበቅ ጎል ላይ ያላውን ክፍተት ግን በእረፍቱ ቀን እንዳስተካከለ ይታሰባል።

አዲስ አዳጊዎቹ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በበኩላቸው ከላይ እንደገለፅነው ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች በአስቆጪ ሁኔታ ጨዋታዎችን ሲያጡ ታዝበናል። ከኳስ ጋር ጊዜ ለማሳለፍ የሚጥረው ቡድኑ ድቻ ከኳስ ቁጥጥር ጋር በተገናኘ ፍላጎቱ እምብዛም ስለሆነ የጨዋታውን የኃይል ሚዛን በኳስ ቁጥጥር ወደ ራሱ ለማምጣት ሊጥር ይችላል። ይህ ቢሆንም ግን ቡድኑ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ካለበት የመዘናጋት ክፍተት በተጨማሪ በሁለቱ ጨዋታ በድምሩ 27 የግብ ሙከራዎችን ማስተናገዱ ከኳስ ውጪ ያለው አደረጃጀት መጠነኛ ክፍተቶች እንዳሉበት ይጠቁማል። ይህንንም ነገ አሻሻሎ ካልቀረበ ራሱን በድጋሜ ለፈተና ሊዳርግ ይችላል።

ወላይታ ድቻ የመስመር አጥቂው ቢኒያም ፍቅሬ አሁንም ከጉዳቱ ባለማገገሙ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ደግሞ አጥቂው ሔኖክ አየለ ህመም በማስተናገዱ በነገው ጨዋታ እንደማይጠቀሙዋቸው ተጠቁሟል።

ቡድኖቹ ከዚህ ቀደም 10 ጊዜ ተገናኝተው ኤሌክትሪክ 3 ጊዜ ሲያሸንፍ ድቻ 2 አሸንፏል። በአምስቱ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። እኩል ስድስት ጎልም አስቆጥረዋል።

ይህንን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት እያሱ ፈንቴ የመምራት ኃላፊነቱ ሲሰጠው አበራ አብርደው እና ለዓለም ዋሲሁን ረዳት ኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ ደግሞ አራተኛ ዳኛ ሆነው እንዲያገለግሉ ተመድቧል።


ሲዳማ ቡና ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

የተረጋጋ አጀማመር ያላደረገው ሲዳማ ቡና ከዓምናው ምርጥ ብቃቱ ከቀጠለው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የሚያደርጉት የነገ 10 ሰዓት ፍልሚያ ተጠባቂ ነው። በተለይ ሲዳማ ቡና ከሽንፈት መልስ ወደ አዎንታዊ መንገድ ለመምጣት እንዲሁም ቅዱስ ጊዮርጊስ በያዘው የውጤት ጎዳና ለመዝለቅ የሚደረገው እንቅስቃሴ ቀልብን እንደሚስብ ይታሰባል።

ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ሁለት ለሁለት ተለያይተው ዓመቱን የጀመሩት ሲዳማዎች ባሳለፍነው ሳምንት ግን አስደንጋጭ የ4ለ1 ሽንፈት በሀዲያ ሆሳዕና አስተናግደዋል። በጨዋታው ቡድኑ ቀዳሚ ሆኖ ቢመራም በሁለተኛው አጋማሽ የነበረው ጨዋታን የመቆጣጠር ብቃት እጅግ የሚያስወቅሰው ነበር። በተለይ በመከላከል ቅርፅ ግለሰባዊ እና መዋቅራዊ ግድፈቶችን እየፈፀመ በእጁ የገባውን ሦስት ነጥብ አሳልፎ ሰጥቷል። በነገው ጨዋታም ከዚህ የውጤት ድባቴ ወጥቶ በምን ያህል ደረጃ ምላሽ ይሰጣል የሚለው ሲጠበቅ ከምንም በላይ ግን በጨዋታው የታየው የመከላከል ስህተት አይምሬ ለሆኑት የቅዱስ ጊዮርጊስ አጥቂዎች ምቾት እንዳይሆን መጠንቀቅ ዋነኛ አላማ ነው።

በደረጃ ሰንጠረዡ ብቻ ሳይሆን በብዙ መስፈርቶች ከሊጉ ክለቦች የበላይ የሆነው የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከጣፋጮቹ ሁለት ድል በኋላም በጥሩ ስሜት የነገውን ጨዋታ እንደሚከውን ይታሰባል። ከግብ ጠባቂ እስከ አጥቂ በግል እና በቡድን ጥሩ ስብስብ የያዘው ጊዮርጊስ በቶሎ አዲስ እና ነባር ተጫዋቾቹን አዋህዶ ለተጋጣሚ ፈተና መሆኑ የሚያስደንቀው ነው። እርግጥ በኢትዮ ኤሌክትሪኩ ጨዋታ ቡድኑ እስከ 93ኛው ደቂቃ ግብ ማስቆጠር ባይችልም በእንቅስቃሴ ረገድ ግን ለመጥፎ የሚዳርገው ብቃት አላሳየም። ነገም በዚሁ ብቃቱ የሚገኝ ከሆነ ለሲዳማዎች የራስ ምታት እንደሚሆን ሲታሰብ በተቃራኒው ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ከሚጥር ቡድን ጋር መጫወቱ ግን ፈተና እንደሚሆንበት መገመት ይቻላል።

ሲዳማ ቡና በነገው ጨዋታ የተከላካዩ ጊትጋት ኩት ከቅጣት መመለስ እፎይታ የሚሰጠው ሲሆን አምበሉን ሳላዲን ሰዒድ ግን በጉዳት አለማግኘቱ መጥፎው ዜና ነው። ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን ሙሉ ስብስቡን ለጨዋታው ማዘጋጀቱ ተጠቁሟል። ከሲዳማ ጋር በተገናኘ ሌላ ዜና ከሀዲያው የ4ለ1 በኋላ የክለቡ ቦርድ ከአሰልጣኙ ጋር ጠንካራ ውይይት ማድረጋቸው ተሰምቷል።

ተጋጣሚዎቹ 24 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 13 በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን 7 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተው ሲዳማ ቡና 2 ጊዜ አሸንፏል። በ23ቱ ግንኙነት ጊዮርጊስ 32 ግቦችን ሲያስቆጥር ሲዳማ ደግሞ 11 ጊዜ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል።

ኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው በዋና ዳኝነት የ10 ሰዓቱን ጨዋታ ሲመራው ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ይበቃል ደሳለኝ እና ሻረው ጌታቸው በረዳት ተካልኝ ለማ በበኩሉ በአራተኛ ዳኝነት ተሳትፎ እንደሚያደርጉ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።