መቻል የስምንት አዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር አጠናቋል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ባሳለፍነው የውድድር ዓመት በደረጃ ሰንጠረዡ አራተኛ ላይ ተቀምጦ የውድድር ጉዞውን የፈፀመው መቻል የስምንት አዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር ሲያገባድድ የወሳኟን አጥቂ ሴናፍ ዋቁማን ጨምሮ በድምሩ የአራት ነባሮችን ኮንትራትም አራዝሟል፡፡

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ጠንካራ ተፎካካሪ ተብለው ከሚጠቀሱ ክለቦች መካከል የሚመደበው የቀድሞው መከላከያ በአሁኑ ስያሜው መቻል በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን የታየበትን ክፍተት ለመድፈን በዘንድሮው የውድድር ጉዞው ላይ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ለመገኘት በማሰብ በአሰልጣኝ መቶ አለቃ ስለሺ ገመቹ እየተመራ ስምንት አዳዲስ ተጫዋቾችን ከተለያዩ ክለቦች ሲያስፈርም በክለቡ የነበሩ የአራት ተጫዋቾችን ውል ደግሞ ለተጨማሪ ዓመት ማራዘሙን ሶከር ኢትዮጵያ ከክለቡ የደረሳት መረጃ ያመላክታል፡፡

ግብ ጠባቂዋ እምወድሽ ይርጋሸዋ ከረጅም ጉዜ በኋላ ከአዳማ ከተማ ጋር በመለያየት መዳረሻዋ መቻል ሆኗል፡፡ ቁመተ ረጅሟ የግብ ዘብ ለቀጣዮቹ ሁለት የውድድር ዘመናት በክለቡ የምትቆይም ይሆናል፡፡ ሌላኛዋ የግብ ዘብ አበባየሁ ጣሰውም ወደ መቻል ተጉዛለች፡፡ ተጫዋቿ በአርባምንጭ ከተማ እንዲሁም የተጠናቀቀውን ዓመት በድሬዳዋ ከተማ አሳልፋለች፡፡

ተከላካዩዋ አረጋሽ ፀጋ ሌላኛዋ የክለቡ ፈራሚ ነች፡፡ የቀድሞው የአርባምንጭ ከተማ ፣ ሀዋሳ እና ድሬዳዋ ተጫዋች ያለፈውን ዓመት በኢትዮ ኤሌክትሪክ ካሳለፈች በኋላ ነው መቻልን መቀላቀል የቻለችው፡፡ ታሪኳ ዴቢሶም ሌላኛዋ ፈራሚ መሆን ችላለች፡፡ በሲዳማ ቡና የእግርኳስ ህይወትን ከጀመረች በኋላ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያለፉትን አምስት ዓመታት የከረመችው ተከላካዩዋ የመቻል አራተኛ ፈራሚ ሆናለች፡፡

ፀጋ ንጉሴ በድጋሚ የቀድሞው ክለቧን ተቀላቅላለች፡፡ በአማካይ ተከላካይ ቦታ የምትጫወተዋ ፀጋ በኢትዮ ኤሌክትሪክ የ2014 የውድድር ዓመት ቆይታዋን አድርጋ በድጋሚ ወደ ቀድሞ ቤቷ ተመልሳለች፡፡ ትሁን አየለ ሌላኛዋ አዲስ የክለቡ ተጫዋች ነች፡፡ በአርባምንጭ ፣ ሀዋሳ እና ድሬዳዋ የምናውቃት የአማካይ ስፍራ ተጫዋቿ መቻልን መቀላቀሏ ዕርግጥ ሆኗል፡፡

አጥቂዋ ምርቃት ፈለቀም የአሰልጣኝ ስለሺ ሌላኛዋ ፈራሚ ሆናለች፡፡ የክለብ ህይወትን በሀዋሳ ከተማ የጀመረችው እና ያለፉትን አራት የውድድር ዘመናት ደግሞ በአዳማ ከተማ የነበረችው ተጫዋቿ እና በሀዋሳ ከተማ እና በባህርዳር ከተማ የምናውቃት ሌላኛዋ አጥቂ ምስር ኢብራሂም የቀድሞው ክለቧን በድጋሚ መቀላቀል ችላለች፡፡

ክለቡ ከአዳዲስ ፈራሚዎቹ በዘለለ የወሳኟ አጥቂ ሴናፍ ዋቁማ ፣ ቤተልሄም በቀለ (ተከላካይ) ፣ ነፃነት ፀጋዬ (ተከላካይ) እና ገነት ሀይሉ (አማካይ) ውላቸው ለተጨማሪ ዓመት ተራዝሞላቸዋል፡፡