ወላይታ ድቻ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ በመጀመሪያው አጋማሽ ባስቆጠሩት አንድ አንድ ጎል አንድ ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል።
ፋሲል ከነማ አህጉራዊ ውድድር ላይ እየተሳተፈ በመሆኑ የሁለተኛ ሳምንት ጨዋታቸውን ያላደረጉት ወላይታ ድቻዎች በመጀመሪያው የጨዋታ ሳምንት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር አቻ ከተለያዩበት ፍልሚያ ያሬድ ዳዊትን ብቻ በአበባየሁ አጂሶ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል። በተቃራኒው ባለቀ ሰዓት ግብ አስተናግደው በወቅቱ የሊጉ ዋንጫ ባለቤት የተረቱት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በበኩላቸው ሽንፈት ካስተናገዱበት የሁለተኛ ሳምንት ጨዋታ ኢብራሂም ከድር እና ሔኖክ አየለን በሚኪያስ መኮንን እንዲሁም አላዛር ሽመልስ ተውጠው ጨዋታውን ቀርበዋል።
ድቻ እና ኤሌክትሪክ በሁለት የተለያየ የጨዋታ መንገድ እየተንቀሳቀሱ ፍልሚያውን ጀምረዋል። በዚህም ኢትዮ ኤሌክትሪክ ኳሱን በመቆጣጠር ለመጫወት ሲሞክር ወላይታ ድቻ ደግሞ ቀጥተኛ አጨዋወት በመከተል ከጨዋታው አንዳች ነገር ለማግኘት ታትሯል። ድቻዎች በ4ኛው ደቂቃም ጌቱ ኃይለማርያም በአደገኛ ቦታ የተሳሳተውን ኳስ ቃልኪዳን ዘላለም ቀምቶ በሞከረው አጋጣሚ የመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ጥቃት ሰንዝረዋል። ከስድስት ደቂቃዎች በኋላም የቀኝ መስመር ተከላካዩ በረከት ወልደዮሐንስ ፈጣን የመስመር ላይ ሩጫ አድርጎ ሁለተኛ ሙከራ ሰንዝሮ ተመልሷል።
የአሠልጣኝ ክፍሌ ተጫዋቾች ኳሱን ቢቆጣጠሩትም በመጨረሻው የሜዳ ክፍል እምብዛም ስል አልነበሩም። ይባስ በ19ኛው ደቂቃ ጌቱ ኃይለማሪያም ቃልኪዳን ዘላለም ላይ በሰራው ጥፋት የፍፁም ቅጣት ምት ተሰጥቶባቸው አጋጣሚውን ራሱ ቃልኪዳን መትቶ ግብ አስቆጥሮባቸዋል። ከደቂቃ በኋላም ቃልኪዳን ከሳጥን ውጪ ሌላ ጥቃት ሰንዝሮባቸው ነበር። ይህ ቢሆንምግን ለተቆጠረባቸው ጎል ፈጣን ምላሽ ሰጥተዋል። በዚህም ከወደቀኝ ካደላ ቦታ የተገኘውን የቅጣት ምት ፀጋ ደርቤ አሻምቶት አብነት ደምሴ በግንባሩ ጎል አድርጎት አቻ ሆነዋል።
ግብ ካስቆጠሩ በኋላ ተቀዛቅዘው የታዩት ወላይታ ድቻዎች ከወገብ በላይ የተረጋጋ አጨዋወት መከተል ተስኗቸው ጫናዎች በዝቶባቸዋል። በ30ኛው ደቂቃ ፀጋ ደርቤ ፍጥነቱን ተጠቅሞ እንዲሁም በ37ኛው ደቂቃ ስንታየሁ ወለጬ ከሳጥን ውጪ ጥሩ ሙከራ ሰንዝረው ወደ ተመሪነት ሊቀይሯቸው ነበር። ነገርግን ሁለቱም ሙከራዎች የግራውን ቋሚ ታከው ወጥተዋል። አጋማሹም ተጨማሪ ግብ ሳይስተናገድበት አቻ ተጠናቋል።
ሁለተኛውን አጋማሽ የተጫዋቾችን ለውጥ አድርገው ወደ ሜዳ የገቡት ወላይታ ድቻዎች በአንፃራዊነት የተሻለ በመንቀሳቀስ የጨዋታውን የኃይል ሚዛን ወደ ራሳቸው አድርገዋል። ገና አጋማሻሹ በተጀመረ በ45ኛው ሰከንድም ስንታየሁ መንግስቱ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መትቶ ቀዳሚ ሊሆኑ ነበር። ይህ ብቻ ሳይሆን በ50ኛው ደቂቃም አበባየሁ አጂሶ ከመስመር ያሻገረውን ኳስ ይሁ አጥቂ ለመጠቀም ጥሮ ለጥቂት ወጥቶበታል። በተቃራኒው ደከም ብለው የታዩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በበኩላቸው በመጀመሪያው አጋማሽ የነበራቸውን የኳስ ቁጥጥር አጥተው ለጫናዎች ራሳቸውን አጋልጠው ታይተዋል። በተለይ አማካይ መስመር ላይ የተወሰደባቸው ብልጫ ጨዋታው እንዲከብዳቸው አድርጎ ታይቷል።
ጨዋታው 60ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ማታይ ሉል ጥፋት ሰርቶ የተገኘውን የቅጣት ምት ተቀይሮ የገባው እድሪስ ሰዒድ አሻግሮት ድቻዎች እጅግ ለግብ ቀርበው የነበረ ቢሆንም አብነት እንደምንም አድኖታል። ከድቻ ጫና በኋላ ኤሌክትሪክም በማጥቃት ምላሽ ለመስጠት ጥሯል። የመጨረሻ ቅብብሎቹ ግን ወደ አደገኛ ዕድልነት ባይቀየሩም ጨዋታው ጥሩ የማጥቃት ምልልስ ኖሮት እንዲታይ አስችሏል። የወላይታ ድቻ የአማካይ ክፍል ብልጫ ግን ከቆሙ ኳሶች ጋር ተደምሮ አደገኛ የግብ ዕድሎችን በብዛት አይፍጠር እንጂ ሜዳ ላይ የተሻለ የማጥቃት ጉልበት ያለው ቡድን ሆኖ እንዲታይ አድርጎታል።
ዘግይተውም ቢሆን የተጫዋች ቅያሪ ያደረጉት ኤሌክትሪኮች ደቂቃ በደቂቃ የነበረባቸውን ጫና እንዲያረግቡ አድርጓቸዋል። 77ኛው ደቂቃ ላይም እጅግ ለግብ የቀረቡበትን አደገኛ አጋጣሚ ፈጥረው ነበር። በዚህ ደቂቃም ከግራ መስመር የተሻገረውን ኳስ ተቀይሮ የገባው አቤል ከመልካሙ በላይ ዘሎ በግንባሩ ሲገጨው ሚኪያስ እግሩ ስር ደርሶ ፈጣኑ የመስመር አጥቂ ኳሱን ከመረብ ጋር ለማገናኘት ቦታ እና ጊዜ ቢያገኝም በአስቆጪ ሁኔታ አምክኖታል። በቀሪዎቹ ደቂቃዎች የጠራ የግብ ማግባት አጋጣሚ ሳይፈጠር ፍልሚያው በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
ቀድመው ግብ አግኝተው የነበሩትን ወላይታ ድቻ የሚመሩት አሠልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ጨዋታው ባቀዱት መንገድ እንዳልሄደ ጠቅሰው የተጫዋቾቹ የጨዋታ ዝግጁነት በሚፈለገው ደረጃ እንዳልሆነ ተናግረዋል። በተቃራኒው የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ አንድ ነጥብ ያገኘው የኢትዮ ኤሌክትሪክ አሠልጣኝ ክፍሌ ቦልተና በበኩላቸው ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ያስተናገዱት ሽንፈት በዐምሮ ደረጃ እንዳወረዳቸው አስረድተው በተቻለ መጠን ከጨዋታው ነጥብ ይዞ ለመውጣት እንደጣሩ እና አዲሱ ስብስብ ጨዋታ በጨዋታ እድገት እያሳየ እንደሆነ ሲናገሩ ተደምጠዋል።