ሪፖርት | ፈረሰኞቹ የጎል ፌሽታቸውን ቀጥለዋል

ሲዳማ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስን ያገናኘው የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ በፈረሰኞቹ 5-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በሁለተኛው ሳምንት በሀዲያ ሆሳዕና አስደንጋጭ ሽንፈት በኋላ ሲዳማ ቡናዎች መክብብ ደገፉ ፣ መሐሪ መና ፣ አንተነህ ተስፋዬ ፣ ደግፌ ዓለሙ እና ጎድዊን ኦባጃን በፊሊፔ ኦቮኖ ፣ ጊት ጋትጉት ፣ ሰለሞን ሐብቴ ፣ አማኑኤል እንዳለ እና አቤል እንዳለ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል። የሊጉ ተከታታይ ሁለት ጨዋታን በድል የተወጡት ፈረሰኞቹ በበኩላቸው ደስታ ደሙ ፣ ሄኖክ አዱኛ እና ጋቶች ፓኖምን በምኞት ደበበ፣ ሱሌይማን ሀሚድ እና ናትናኤል ዘለቀ በመተካት ለፍልሚያው ቀርበዋል።

በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ዶ/ር ኃይለየሱስ ባዘዘው መሪነት ተጋጣሚዎች ወደ ሜዳ ሲገቡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ለታላቁ የእግርኳስ ሰው ፍቅሩ ኪዳኔ ያላቸውን አክብሮት ለመግለፅ የመታሰቢያ አበባ ጉንጉን በአንበላቸው አማካኝነት ይዘው ወደ ሜዳ ገብተዋል። ከቀናት በፊት በሞት የተለዩን ፍቅሩ ኪዳኔ በአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት ታስበው ጨዋታው እንዲጀምር ሆኗል።

ረጋ ባለ የእንቅስቃሴ መንፈስ በጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በሲዳማ ቡና በኩል በውጤት ቀውስ ውስጥ እንደመገኘታቸው መጠን በጥንቃቄ አጨዋት ክፍተቶችን ለመፈለግ አስበው ቢጫወቱም በዚህ ሂደት የቆዩት አስር ደቂቃ ብቻ ነበር። ኳሱን ተቆጣጥረው በመስመሮች በኩል ጎል ለማግኘት የፈለጉት ፈረሰኞቹ በ10ኛው ደቂቃ ከሳጥን ውጪ የተሰጠውን ቅጣት ምት በረከት ወልዴ ወደ ጎልነት በመቀየር ቡድኑን ቀዳሚ ሆኗል። የአምናው ጥንካሬው የከዳቸው ሲዳማ ቡናዎች በድጋሚ እጃቸውን ለቅዱስ ጊዮርጊስ በመስጠት ሁለተኛ ጎል ለማስተናገድ ተገደዋል። በ17ኛው ደቂቃ ሰለሞን ሀብቴ ቢንያም በላይ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ ወደ ጎልነት በመቀየር የቡድኑን የጎል መጠን ወደ ሁለት አድርሶታል።

ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው ለመመለስ መንቀሳቀስ የጀመሩት ሲዳማዎች የመጀመርያ የጎል ሙከራቸውን በ30ኛው ደቂቃ ከቆመ ኳስ በያኩቡ መሐመድ የግንባር ምት ማግኘት ችለውም ነበር። ወደ ጎል በመድረስ ወደ ጨዋታው ለመግባት ያሳዩት ፍላጎት በ33ኛው ደቂቃ ወደ ጎልነት ተቀይሮላቸዋል። ከቀኝ መስመር የተሻገረውን ኳስ ምኞት ደበበ ይገዙ ቦጋለ ላይ ጥፋት በመሰራቱ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ይገዙ ወደ ጎልነት ቀይሮታል። በዚህች ጎል የተነቃቁት ሲዳማዎች ጫና ፈጥረው በመጫወት የአቻነት ጎል ፍለጋ ቢጥሩም የሰላ ሙከራ ማድረግ ተስኗቸው ቆይቷል። ይልቁንም ሌላ ራስ ምታት ለዕረፍት መዳረሻ በጭማሪ ደቂቃ ሁለት ተጨማሪ ጎሎች ተስተናግዶባቸው እንዳያንሰራሩ አድርጓቸዋል።

ወደ ፊት በመሄድ ያገኟቸውን የጎል አጋጣሚዎች ያለ ዕርህራሄ ተጠቅመው የሚመለሱት ፈረሰኞቹ ዳዊት ተፈራ በጥሩ ዕይታ ሳጥን ውስጥ ያቀበለውን ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሦስተኛ ጎል ሲያስገኝ ከሁለት ደቂቃ በኋላ የሲዳማን መከላከል ሲበትነው የዋለው ቸርነት ጉጉሳ የተሰራበትን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ ሐት-ትሪክ የሰራበትን አራተኛ ጎል ለፈረሰኞቹ አስቆጥሯል። በዚህም ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ በውድድር ዓመቱ ሁለተኛ ሐት – ትሪክ መስራት ችሏል።

ከዕረፍት መልስ ፈረሰኞቹ በሰፊ የጎል ልዩነት የሚመሩ በመሆናቸው ያለጫና የጨዋታው እንቅስቃሴ በተገቢው ሁኔታ ተቆጣጥረው በመዝለቅ 65ኛው ደቂቃ አምስተኛ ጎላቸውን ማግኘት ችለዋል። በዕለቱ አስደናቂ እንቅስቃሴ ያደረገው ቸርነት ጉግሳ ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ተቀይሮ የገባው አማኑኤል ገ/ሚካኤል ጎል አግብቶ ለራሱ የውድድር ዓመቱን የመጀመርያ ጎል አግኝቷል። በተዝናኖት ተረጋግተው ማጥቃታቸውን የቀጠሉት ፈረሰኞቹ በቀሩት ደቂቃዎች ተጨማሪ ጎሎች ሳይጨምሩ ሲዳማ ቡናዎችም ልዩነቱን ለማጥበብ ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ጨዋታው 5-1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ አጠናቀዋል።

ውጤቱን ተከትሎ ፈረሰኞቹ በሦስት ጨዋታ አስራ ሦስት ጎሎች አስቆጥረው በዘጠኝ ነጥብ ሊጉን ሲመሩ በአንፃሩ ሲዳማ ቡናዎች በሦስት ጨዋታ አስራ አንድ ጎል ተቆጥሮባቸው የሊጉ ግርጌ ላይ ለመቀመጥ ተገደዋል።

ያጋሩ